ኢትዮጵያ ካሏት ብርቅዬ እሴቶች ውስጥ የዘመን አቆጣጠር ሥርዓቷና ተያይዘው የሚከናወኑት ተግባራት ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው:: አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓላማና ተስፋ በመሰነቅ በደመቀ ሁኔታ ያከብሩታል:: የተሻለ ለመስራት ቃል ይገባሉ:: ከአጉል ልምዶችና ከጎጅ ስብዕና ለመላቀቅ እቅድ ይነድፋሉ:: ዳሩ ግን ብዙውን ጊዜ እቅዶች የግል ህይወትን ማለትም ሥራን: ትዳርን: ቤተሰብን: ትምህርትንና ጤናን የተመለከቱ ናቸው:: ሰብአዊ: ህገ መንግስታዊና ተፈጥሮአዊ መብቶቻቸው ሲጣሱ ከማየትና በር ዘግቶ ከማማት በስተቀር በእቅድ ይዘው ለውጥ ለማምጣት ሲጥሩ የሚታዩ እምብዛም ናቸው:: በአዲስ ዓመት ራሳችንን ከማንኛውም አላስፈላጊ ጫና ነጻ ለማውጣት ስናቅድ አንታይም:: ይህም አምባና ብሄር ገነንነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የራሱን ድርሻ እያደረገ ነው::