Saturday, 11 May 2019

ማኅበራዊ ፍትሕን ለማስፈን እንረባረብ!



ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ/ም! ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ከ107 ወደ 100 ወረደ.። የቀድሞ ሰባት ፓርቲዎች ራሳቸውን ሰውተው (አክስመው የሚለው ጥሩ ቃል አይመስለኝም) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማበራዊ ፍት(ኢዜማ) የተሰኘ ብሔራዊ ፓርቲ መስረተዋል። የኢዜማ አመሰራረትና አቋም ቀልብ ይስባል! አንደኛ ከወረዳ የመነጨ የአባላት መሠረት አለው። ሁለተኛ የአመራር አባላት በምርጫ ተሰይመዋል። ሦስተኛ ፕሬዚዳንታዊ ሥልጣንን ለመመለስ ይሠራል። አራተኛ ትክክለኛ የፌደራል አወቃቀርንም ይከተላል። አምስተኛ ብሔራዊ የፖለቲካ ቁመና ይኖረዋል። ባጠቃላይ ሲታይ ለብዙ ጊዜ ግንባር፣ መድረክ፣ ኅብረት፣ ቅንጅት፣ ንቅናቄ፣ ወዘተ በሚሉ እንቅስቃሴዎች ሲቃኝ የነበረው ባተሌው ፖለቲካችን ቢያንስ አዲስ ስምና ርዕይ ይዞ መጥቷል። ይህን እውን ለማድረግ ርብርብ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልብ ሊመሰገኑ ይገባል። እንኳን ደስ አላችሁም ልንላቸው ይገባል!


የኢዜማ መቋቋም ዘርፈ ብዙ አንደምታዎች ይኖሩታል። የብሔር ፖለቲካ ብቸኛ መንገድ እንዳልሆነ ግንዛቤ ይወሰዳል። በሀገር ወዳዱ ዘንድ ሁሉ አዲስ የፖለቲካ መነቃቃት ይፈጥራል። ምናልባትም አስተዋጽዖ ለማድረግ ፍላጎት እያለው ግራ በመጋባትና በመጠራጠር ከመሀል ወይም ከዳር ሆኖ ለሚመለከት ሁሉ ጥሩ እድል ይፈጥራል። ሌሎች 100 ፓርቲዎች ኢሕአዴግን ጨምሮ መስዋእትነት ከፍለው ውህደት እንዲፈጽሙ ይጋብዛቸዋል። አዲስ ፓርቲ ለማቋቋም ሀሳቡ ያላቸው ደግሞ ቢያንስ በይሉኝታ ሀሳባቸውን እንዲሰርዙ ያስገድዳቸዋል። መንግስትና ገዥው ፓርቲ ፈርጠም ያለ እውነተኛ ተፎካካሪ ፓርቲ እንደተወለደ በመገንዘብ አገልግሎታቸውን ይበልጥ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲያደርጉ ይጋብዛቸዋል። ኢትዮጵያዊነት ሁሉም ነገዶች የሚጠለሉበት ጃንጥላ ስለሆነ ስጋትና ጥርጣሬን ያስወግዳል። ብሎም በክልሎች መካከል ከወሰን ጋር በተያያዘ ሊኖር የሚችለውን አላስፈላጊ የእርስ በርስ ንትርክን መፈናቀልን መገዳደልን ያስቀራል። ከተለያዩ  ነገዶች የተመሰረቱ ቤተሰቦች በአንድነትና በፍቅር ይጸናሉ።  

ይሁንና ኢዜማ ከመክሰም ወይም ከመከፋፈል ድኖ ማኅበራዊ ፍትሕን በኢትዮጵያ ለማስፈን እጅግ ልዩ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ ያስፈልገዋል። አባላቱን እያበዛ የሰፊውንም ሕዝብ ልብና አእምሮ እየማረከ መሄድ ግድ ይላል። እስካሁን ድረስ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሄዱበትን ውጤት አልባ ጉዞ ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ካሁኑ አትራፊ መንገዶችን መለየትና መከተል ያስፈልጋል። ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተናብቦ ተቻችሎ መጓዝ ያስፈልገዋል። ከዚህ በፊት እንደተለመደው መሪዎች ብቻቸውን የፓርቲን ፍጻሜ የሚወስኑ መሆን የለባቸውም። ኢዜማ ራሱን አደራጅቶ ለቁም ነገር በቅቶ ኢትዮጵያን እንዲታደግ የፓርቲው አመራርና አባላት ድርጅታቸውን የሚቆጣጠሩበት የሚገመግሙበት የሚመሩበት ሥርዓት መለየትና ሥራ ላይ ማዋል ይገባቸዋል። ሀገሩን የሚወድ ሰፊው ሕዝብም ፓርቲውን ለመደገፍም ሆነ ለመውቀስ የሚጠቀምበት ግልጽ መስፈርት ሊኖረው ይገባል። የፓርቲው አባላትና ሀገሩን የሚወድ ዜጋ ሁሉ ኢዜማ ዘመን ተሸጋሪ ፓርቲ እንዲሆን የበኩላቸውን ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ጉዳዩ ሀገር የማዳን እንጅ የአንድ ፓርቲ ጉዳይ አይደለም። እርስዎም ኢዜማን እየደገፉ እየተቹም የዜግነት ግዴታዎን ይወጡ። ማኅበራዊ ፍትሕ በፓርቲ አመራሮችና አባላት ብቻ ሊሰፍን አይችልምና!  

በቀጣይነት ለየት ያሉ ትንታኔዎች ይቀርባሉ!  

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!    

1 comment:

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...