ለመጀመሪያ ጊዜ በሰላማዊ ሰልፍ የተሳተፍኩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 6 ኪሎ ግቢ ተማሪ እያለሁ ነበር:: በአራት ዓመት የትምህርት ቆይታዬ በርከት ያሉ ሰልፎች ተካሂደዋል:: አንዳንዴ የምግብ ጥራት ማሽቆልቆሉን በመቃወም ሌላ ጊዜ ነጻነትን ፍትህንና ዴሞክራሲን እንዲሁም የመሬት ክፍፍልን በመቃወም:: ምግብን በተመለከተ የተቀናጁ ሰልፎች አጀማመራቸው ምግብ-ነክ ይሁን እንጅ መደምደሚያቸው ፖለቲካ ነበር:: ድንገት ከሰልፉ መካከል አንዱ ተነስቶ "ፍትህና መብት ይከበር" ካለ ተሜ ወዲያው ተቀብሎ ያስተጋባዋል:: አንዳንዶች ደግሞ በራሳቸው ተነሳሽነት ቀድሞ የተዘጋጀ የጽሁፍ መፈክር ብቅ ያደርጋሉ:: በአቅራቢያቸው ያለ ተሜ እያነበበ ያስተጋባዋል:: ሌላው ይቀበለዋል:: የአንገት ስር እስኪወደር ድረስ ይፎከራል:: ስሜት እየጋለ ይሄዳል:: የተሰላፊው ቁጥር የሚጨምረው ሰልፉ ከተጀመረ ከበርካታ ደቂቃዎች በኋላ ነው:: መጀመሪያ ላይ ፈራ ተባ እያሉ ከዳር ሆነው የሚመለከቱ ይበዛሉ.: በኋላ ድንገት ሰልፉን የሚቀላቀሉ ይበዛሉ::