መቅድም
ሀዋሳ በተካሄደው የኢሕአዴግ
11ኛ ጉባኤ ዶ/ር ዐቢይ ከ177 ድምጾች ውስጥ 176ቱን በማግኘት የኢሕአዴግ
ሊቀ መንበርነታቸውን አስጠብቀዋል። ዶ/ሩ እንደሚያሸንፉ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሲገምቱ ነበርና ውጤቱ
ብዙም አላስደነቀም። የእርሳቸውን ያህል አቅምና የሞራል ልዕልና ያለው ሰው እስካሁን ድረስ ከኢሕአዴግ ውስጥ አላየንምና! ይልቁንስ
ብዙ ያወያየ የምክትሉ የአቶ ደመቀ ጉዳይ ነበር። እርሳቸውም 149 ድምጽ በማግኘት ወንበራቸውን አስጠብቀዋል። ምርጫውን ተከትሎም
የኢትዮጵያን ሕዝብ በላቀ ደረጃ ለማገልገል እንደተዘጋጁ ሊቀ መናብርቱ ተናግረዋል። በተለይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ካሁኑ ማንነታቸውንና
ምንነታቸውን ፈትሸው ካልተደራጁ በቀጣዩ ምርጫ በኢሕአዴግ ሊሸነፉ እንደሚችሉ ዶ/ር ዐቢይ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። ይህ ትልቅ ጉዳይ ነው! በርካታ ጥያቄዎችን
እንድናነሳ ይጋብዘናል። ለመሆኑ ከዚህ ንግግር በስተጀርባ የተቀመጡ መላምቶች ምንድን ናቸው? በውኑ ዶ/ሩ እንዳሉት ኢሕአዴግ እንደ
ፓርቲ በቀጣዩ ምርጫ ያሸንፋል? ይህ ጽሑፍ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።
ዓላማውም ኢሕአዴግ በቀጣዩ ምርጫ እንደሚያሸንፍ ወይም እንደማያሸንፍ
በእርግጠኝነት ለመናገር ሳይሆን መሪዎች የሚናገሯቸውን ንግግሮች ሁሉ እንደወረደ ከመውሰድ ተቆጥበን ጉዳዮችን ሁሉ በአንክሮ መመርመር
እንደሚገባን ለማመላከት ነው።