ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ/ም! ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተፎካካሪ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ከ107 ወደ 100 ወረደ.። የቀድሞ ሰባት ፓርቲዎች ራሳቸውን ሰውተው (አክስመው የሚለው ጥሩ
ቃል አይመስለኝም) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የተሰኘ ብሔራዊ ፓርቲ መስረተዋል። የኢዜማ አመሰራረትና አቋም ቀልብ ይስባል! አንደኛ ከወረዳ የመነጨ
የአባላት መሠረት አለው። ሁለተኛ የአመራር አባላት በምርጫ ተሰይመዋል። ሦስተኛ ፕሬዚዳንታዊ ሥልጣንን ለመመለስ ይሠራል። አራተኛ
ትክክለኛ የፌደራል አወቃቀርንም ይከተላል። አምስተኛ ብሔራዊ የፖለቲካ ቁመና ይኖረዋል። ባጠቃላይ ሲታይ ለብዙ ጊዜ ግንባር፣ መድረክ፣
ኅብረት፣ ቅንጅት፣ ንቅናቄ፣ ወዘተ በሚሉ እንቅስቃሴዎች ሲቃኝ የነበረው ባተሌው ፖለቲካችን ቢያንስ አዲስ ስምና ርዕይ ይዞ መጥቷል።
ይህን እውን ለማድረግ ርብርብ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልብ ሊመሰገኑ ይገባል። እንኳን ደስ አላችሁም ልንላቸው ይገባል!