ሃሰን ዑመር አብደላ በሚል የብዕር ስም ጦቢያ መጽሔት ላይ ይጽፉ የነበሩ አቶ ዩሱፍ ያሲን ”አሰባሳቢ ማንነት ባንድ ሃገር ልጅነት፣የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ” በሚል ርዕስ ያዘጋጁትን መጽሐፍ ከሦስት ሳምንት በፊት የኦስሎ ነዋሪዎች ባዘጋጁት ፕሮግራም ላይ አስመርቀዋል:: በወቅቱም ከኦስሎና አካባቢዋ እንዲሁም ከሌሎች የአውሮፓ ሃገራት የመጡ ኢትዮጵያውያን በብዛት ተገኝተዋል:: ሰዓት አልበቃ እስኪል ድረስ ሞቅ ደመቅ ያሉ ውይይቶች መጽሐፉን በተመለከተ ተካሂደዋል:: ጥያቄዎችና ትችቶች ተነስተዋል:: ምስጋናዎችና አድናቆቶችም እንዲሁ:: ለተነሱ ወሳኝ መስለው ለታዩ ጉዳዮች ጸሐፊው አጠር አጠር ያሉ ግን ሞቅ ደመቅ ያሉ መልሶችንና እይታዎችን አቅርበዋል:: የጋለውን ውይይት ከተመለከቱ በኋላም መጽሐፉ ከአሁኑ ዓላማውን እየመታ እንደሆነ ተናግረዋል:: ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ ውይይቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልና መግባባት ላይ እንዲደርስ አጠንክረው አሳስበዋል::