ስደት ለምን?
ስደት ከትውልድ አገር በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ወጥቶ በሌላ አገር ለረጅምም ሆነ ለአጭር ጊዜ መኖርን ያመለክታል:: በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ስደተኞች አዳምና ሔዋን ናቸው:: ምንም እንኳን እግዚአብሔር ከምድር አፈር ቢፈጥራቸውም አገራቸው በምሥራቅ በኩል ባለች በኤዶም ገነት ይሆን ዘንድ ፈቃዱ ሆነ:: አዳም በተፈጠረ በ40 ቀኑ ሔዋን በተፈጠረች በ80 ቀኗ ኤዶም ገነት ገቡ:: በዚያም ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከ17 ቀን በደስታ ከኖሩ በኋላ ጠላት ዲያብሎስ በእባብ ተመስሎ አሳታቸው:: የታዛዥነት ምልክት የሆነችውን ያልተፈቀደላቸውን ዕፀ በለስን ስለበሉ እግዚአብሔር ከገነት አስወጣቸው:: በተፈጠሩባት ምድር በድካም እንዲኖሩ ተፈረደባቸው:: ስደት ወደ ምድር:: አዳምና ሔዋን እግዚአብሔርን በማሳዘናቸውና ገነትን በማጣታቸው ሐዘን ላይ እያሉ ክፉ ልብ የነበረው (1ዮሐ 3: 11 - 12) ልጃቸው ቃየን በቅናት ተነሳስቶ ወንድሙን አቤልን ገደለው:: በእግዚአብሔር አምሳያ የተፈጠረውን ሰውን በመግደል የመጀመሪያው ሰው ሆነ:: ከቤተሰቡና ከእግዚአብሔር ቁጣ የሚያመልጥ መስሎት ኖድ ወደተባለ አገር ተሰደደ:: እድሜ ልኩን ተቅበዝባዥ ሆነ:: ባጠቃላይ ሲታይ የዚህ ቤተሰብ አባላት ማለትም አዳም ሔዋንና ቃየን መራር ለሆነ ስደትና መከራ የተዳረጉት በራሳቸው ኃጢአት የተነሳ ነው::