ከጥቂት ወራት ወዲህ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረ ከሳቡ ወሳኝ ጉዳዮች ውስጥ የዐማራ
መደራጀት ዋናው ሳይሆን አልቀረም። ይህን ጉዳይ በተመለከተ በርካታ ጽሑፎችና ንግግሮች ተደርገዋል። ዐማራው እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነገድ መደራጀትና ራሱን ከተቀነባበረ ጥፋት
ማዳን እንዳለበት የሚሞግቱ በርካቶች ናቸው። አሳማኝ የመከራከሪያ ነጥቦችንም አንስተዋል። በአንጻሩ ደግሞ ዐማራው በኢትዮጵያዊነት እንጅ በነገዱ መታገል መዘዙ ብዙ እንደሆነ ያስጠነቀቁ አሉ። ከሁለቱም ወገኖች አንዳንዶች ነጥቦቻቸውን በምክንያት ወይም በመረጃና በማስረጃ
መደገፍ ሲሳናቸው አፍ አውጥተው ሌሎች ጸሐፍትን ሲሳደቡና «ወያኔ ነህ» «ጸረ ዐማራ ነህ» እያሉ ሲያሸማቅቁ ታይተዋል። ከነዚህ ከተሳዳቢዎችና ከአሸማቃቂዎች በስተቀር ለሌሎች ጸሐፍት ከፍ ያለ አክብሮትና
ምሥጋና አቀርባለሁ። መሠረት ያላቸው ውይይቶችና ክርክሮች ለሚደረገው ትግል ግልጽነትንና መናበብን ይፈጥራሉና!
እኔም በበኩሌ ኢትዮጵያዊነትን መርሁና የስብዕናው
አካል እስካደረገ ድረስ ዐማራው በነገዱ መደራጀት መብቱ እንደሆነ ለዐማራውም ለሌላውም ኢትዮጵያዊ እንደሚጠቅምም «የወቅቱ ፖለቲካዊ አሰላለፍና ፋይዳው» በሚል ርዕስ ሞግቻለሁ (ጽሑፉ Ethiomedia, Zehabesha, እና ESADF ላይ ወጥቶ ነበር)። ውድ አንባቢዎቼም ገንቢና መካሪ አስተያየቶችን ልከውልኛል። ዳሩ ግን በጽሑፌ ውስጥ ያልተካተቱ ግን ብዥታ የፈጠሩ ነጥቦች ተነስተዋል። እነዚህን ጉዳዮች ለማጥራትና ከፍ ያለ መናበብ ለመፍጠር ይህችን ጽሑፍ ሳበረክት በደስታ ነው። የዐማራውን ተጋድሎ ለመደገፍ እንደ መስፈርት ሊያገለግሉ የሚችሉ ነጥቦችን አንስቻለሁ። በዚች ጽሑፍ የተነሱትና የተብራሩት ጉዳዮች የወቅቱን የዐማራውን ተጋድሎ ለሚመሩና ለሚደግፉ እንዲሁም ለሌላውም ውድ ኢትዮጵያዊ
ወገኔ እንደሚበጁ አምናለሁ። ጽሑፉ የተንዛዛና አሰልቺ እንዳይሆን በጥያቄና መልስ
መልኩ ተዘጋጅቷ።
ዐማራ ከኢትዮጵያ ሊገነጠል ይችላል?
ለዐማራው ማኅበረሰብ ዐማራነትና ኢትዮጵያዊነት የስብዕናው ምሰሶዎችና መሠረቶች ናቸው። አንዱ ከሌላው ተለይቶ አይታይም። ዐማራ ተገንጥሎ የራሱን መንግስት መመስረት ለአንድ ሰከንድ እንኳ የሚታሰብ አይደለም። በመሆኑም ዐማራነትን ከኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያዊነትን ከዐማራነት ለመለየት መሞከር ጸጉር ስንጠቃ ነው።
በርግጥ ቁጥራቸው የማይታወቁ ግን ጥቂት የሚባሉ ወገኖቻችን ዐማራው እስከ መገንጠል
የሚያደርስ ትግል ውስጥ እንዲገባ የሚያምኑ አሉ። ምናልባት ከዚህ አቋም ያደረሳቸው ዐማራው ላይ የደረሰውና በመድረስ ላይ ያለው የግፍ ብዛት ሊሆን ይችላል። ይህ እንኳን ባይሆን ሃሳባቸውን በነጻነት የማንሸራሸር መብታቸው ግን መከበር አለበት።
ባጠቃላይ ሲታይ ዐማራው ኢትዮጵያዊነትን እንዲረሳ ማሳመን ማለት ሕወሓትን ኢትዮጵያዊነትን
በሙሉ ልብ እንዲቀበል ማሳመንን ያህል የከበደ ነው። ይህ መረጃም ማስረጃም ከማያስፈልጋቸው እውነታዎች ውስጥ አንዱ ነው። የሚታይ የሚነበብ የሚዳሰስ ነው። በመሆኑም የዐማራውን ትግል የሚደግፍ ወይም ለመደገፍ ያሰበ ሁሉ ኢትዮጵያዊነት መነሻም
መድረሻም መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።
ትግል በዐማራነት እስከ መቼ ይቀጥላል?
ይህም ሆኖ የዐማራው ተደራጅቶ መታገል የሚደገፈው ወይም የሚያስፈልገው
ኢትዮጵያ ውስጥ አስተማማኝ፣ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊና ከሕግ በታች የሆነ መንግስት ተቋቁሞ ሁሉንም ነገዶች በእኩልነትና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ማስተናገድ እስኪጀምር ድረስ ቢሆን የተመረጠ ነው። በዐማራነት መደራጀት በራሱ ችግር ከሆነ ችግሩን የፈጠረው ያለው መንግስት ነው። ዐማራው ከደረሰበት ብርቱ ችግር በመነሳት በፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ከተሞከረው
ፈር ቀዳጅ እንቅስቃሴ ውጭ ያደረገው መደራጀት የለም። 25 ዓመት ሙሉ በዐማራነት ላለመደራጀት ወስኖ የኖረ ማኅበረሰብ ነው። አሁን ግን ምርጫው የመኖርና ያለመኖር ስለሆነ እየተደራጀ ነው። ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ችግር ከተፈታና ዐማራውና ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው
‘ቀና ብለው መሄድ’ ከቻሉ በነገድ መደራጀት አያስፈልግም። ያን ጊዜ ሁሌም እንደተለመደው በአስተሳሰብ ላይ ብቻ የተመሠረት ፖለቲካዊ ሱታፌ በቂ ይሆናል። ሌሎችም በነገድ የተደራጁ ድርጅቶች ተመሳሳይ አቋም መያዝ ያስፈልጋቸዋል። ፕሮፌሰር አሥራት እንዳሰመሩበት የዐማራ ተጋድሎ ለሁሉም ወገን እኩል የሆነ አርቆ አሳቢ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ ነው።
የዐማራው ተጋድሎና የሌሎች ኢትዮጵያዊ ነገዶች ተጋድሎ እንዴት ይዛመዳሉ?
የዐማራው ተጋድሎ ያስፈለገው የራሱን ከዚያም የሌሎችን ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ መብትና
ነጻነት እውን ለማድረግ ነው። የሌሎችንም ኢትዮጵያዊያን ነገዶች መብትና ታሪካዊ ተሳትፎ ወይም ድርሻ እውቅናን ይሰጣል። እጅግ ተባብሮም ይሠራል። መገንጠልም ይሁን አንድነት የሚወሰነው በዐማራው ወይም በተወሰኑ አካላት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በመሆኑም የሌሎችን ነገዶች ትግል የዐማራው ተጋድሎ ማበረታታት መደገፍ ያስፈልገዋል። መሬት ላይ ያለው ነባራዊው ሁኔታ የሚያሳየውም ይህን ነው። ዐማራው፣ ኦሮሞውና ደቡቡ በትግላቸው አንዱ ሌላውን ሲያበረታቱ ሲመሰጋገኑ እያየን ነው። ይህ መንፈስ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ግን ወሳኝነት አለው።
የዐማራው ተጋድሎ ከአንድነት ኃይሉ ጋር እንዴት ይዛመዳል?
በመጀመሪያ ደረጃ አንድነት ወይም ኢትዮጵያዊነት የሚል ስም ለተወሰኑ አካላት ብቻ
መስጠት ተንኮል ነው። ሌሎች በነገድ የተደራጁት ሁሉ አንድነትን ወይም ኢትዮጵያዊነትን እንደማይቀበሉ የሚያመለክት ነውና! ዐማራነትና አንድነት
ወይም ኢትዮጵያዊነት መለያየት የማይችሉ የስብዕና ክፍሎች እንደሆኑ ከላይ ተጠቁሟል። በአፋር፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ፣ በኦሮሞ ወዘተ ነገዶች ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችም አንድነትን ወይም ኢትዮጵያዊነትን መዳረሻቸው ያደረጉ አሉ። በርግጥ ጥቂቶች የመገንጠል እሳቤ ሊኖራቸው ይችል ይሆናል።
ለማንኛውም የዐማራው ተጋድሎ ከሌሎች ነጻነት ከሚናፍቃቸው ወገኖች ሁሉ ጋር ተናቦ
መሥራት ይኖርበታል። የዐማራውን ተጋድሎ አስፈላጊነት ለማሳየት በኢትዮጵያዊነት ወይም በአንድነት ስም የሚንቀሳቀሱ አካላትን መሞገት፣ ማሳጣት፣ መታገል፣ አይጠበቅበትም። የአንድነት ኃይሉም በምንም መልኩ የዐማራውን ተጋድሎ ማሳነስ፣ ማኮሰስ፣ ማፈን፣ መግታት ወዘተ አይጠበቅበትም። አንዱ ለሌላው እጅግ አስፈላጊ ወገኑ እንደሆነ ማመንና በሚገርም መናበብና መተባበር መሥራት አለባቸው።
ሥልጣንንና የግል ጥቅምን በመጠየፍ አንዱ የሌላው ግብዓትና ደጀን እየሆነ ትግሉን
ማፋፋም ያዋጣዋል። አንዱ ሌላውን እንደ ተፎካካሪ ተቀናቃኝ መመልከት የለበትም። የአንድነት ኃይሉን የሚመሩ ወይም የሚደግፉ ዐማራ
ኢትዮጵያዊያን አሉ። ያሉበትን ድርጅት እየተው የግድ የዐማራውን ተጋድሎ መቀላቀል አይጠበቅባቸውም። በያሉበት ሆነው አቅም የፈቀደላቸውን ማበርከት ይችላሉ። ይህ አልሆን ብሎ በሁለቱ ወገኖች መካከል ክርክር ጭቅጭቅ ከቀጠለ ግን ሕዝቡ የራሱን
እርምጃ ይወስዳል እየወሰደም ነው።
የዐማራው ጠላት ማን ነው?
በመሠረቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ድህነት፣ ዘረኝነት፣ አምባገነንነት እና የመሳሰለው ሁሉ ነው። ይህን ደግሞ በአካል የገለጠው የተረጎመውም አሁን ያለው መንግስት ነው። በመሆኑም መንግስትን እንደ ጠላት መቁጠር ከተጀመረ ከርሟል። ለዐማራውም ጠላቱ ይህው ነው። የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ከመመስረቻ ማኒፌስቶው ጀምሮ በበራሪ ወረቀቶች፣ በንግግሮች፣ በሽለላዎች፣ በሥርዓተ ትምህርት ሳይቀር ዐማራን ጭራቅ አድርጎ አስቀምጧል። በተግባርም ለቁጥር ያዳገተ ግፍ መከራ በተቀነባበረ መልኩ አድርሶበታል። ይህ ነው የዐማራው ጠላት እንጅ ሰፊው ውድ የትግራይ ሕዝብ አይደለም።
በመሆኑም የዐማራው ተጋድሎ በጽሑፎችም ይሁን በንግግሮች እስካሁን ድረስ እያደረገ እንዳለው ወያኔን ከትግሬ በግልጽ መለየት ይጠበቅባቸዋል። ዐማራ ሆኖ ዐማራውን የሚያሳድድ እንዳለ ሁሉ ትግሬ ሆኖ ትግሬንም ዐማራንም የሚያሳድድ አለ። ፍረጃ በነገድ ሳይሆን በድርጅት ይልቁንም በግለሰብ ደረጃ ብቻ መሆን አለበት። ትኩረትን ከሕወሓት ከፍተኛ አመራርና ከዋና ዋና ባንዳዎች ላይ ብቻ ማድረግ እጅግ ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ ነው ሰፊ ሕዝባዊ ድጋፍና ብሄራዊ አንድነት ሊገኝና ለጸና የሚችለው!
ከዐማራው ተጋድሎ አመራር ምን ይጠበቃል?
የዐማራው ተጋድሎ እና አመራር ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ወሬውና ሽለላው ደግሞ በውጭው ዓለም ተናኝቶ ይገኛል። አገር ቤት ያለው በጎበዝ አለቃነት የሚመራው አካል ንግግሩ ቋንቋው ሥራ ብቻ ነው። ስለሠራውና እየሠራው ስላለው ጀብዱ የሚያወራበት ጊዜም እቅድም የለውም። እስከአፍንጫው የታጠቀን ሠራዊት በአሮጌ ክላሽ ያርበደብዳል። ለሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች የራስ ምታት ሆኗል። በውጭው ዓለም ያለው ሁሉ ግን ደጋፊ ቢሆን ነው። ደጋፊ ደግሞ ማውራት ያለበት ከደጋፊ እንጅ ከአመራር በሚጠበቅ ቋንቋ መሆን የለበትም። የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ስንገመግም ግን የምናገኘው እውነታ የተለየ ነው። ትግሉ ያለው ኢንተርኔት ላይ ወይም ከኢትዮጵያ ውጭ በሚመስል መልኩ ይወራል። አመራሩ «እኔ ነኝ» የሚሉም ድምጾች እየተሰሙ ነው።
ለነጻነት የሚደረገው ትግል መራራና እልህ አስጨራሽ ነው። ለድል ለመብቃት ሕዝብን ደጀን አድርጎ መነሳት እጅግ አስፈላጊ ነው። የሕዝብን ድጋፍና አመኔታ ለማግኘት ደግሞ ትግሉን የሚመሩም የሚያስተባብሩም፣ በይፋ የሚደግፉም አካላት ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ባህላቸው ማድረግ አለባቸው።
ለምሳሌ በውጭው ዓለም ዐማራ ተኮር ድርጅቶች ወይም እንቅስቃሴዎች ስንት እንደሆኑ፣ እነማን እንደመሰረቷቸውና እንደሚመሯቸው፣ ግባቸውና ዓላማቸው ምን እንደሆነ፣ የትግል ስልታቸው ወዘተ በግልጽ አይታወቅም። ይህም የድርጅቶችን አቋም በደንብ መርምሮ ድጋፍ እና ወይም ተቃውሞ ለመስጠት አስቸጋሪ
አድርጎታል። በርግጥ የአባላትን ማንነት ይፋ ማድረግ ከደህንነት አኳያ አይጠቅምም። የአመራር አባላት ግን በደንብ መታወቅ አለባቸው። ሕዝብ የማወቅ መብትና ፍላጎት አለው። ከዚህ በኋላ በህቡእ ለመምራት መሞከር የትግሉን ዘመን ማራዘም መከራንም ማብዛት
ነው። «የፈራ ይመለስ!» እንደተባለው
የፍርሃት ቆፈን ያለቀቀው ተራ አባል እንጅ አመራር መሆን የለበትም።
ሌላው ትግሉ ከአመራር አባላት ኢትዮጵያዊ ጨዋነትንና ጀግንነትን ይፈልጋል። ከስሜትና ከአሉባልቶ የጸዳና በመረጃና በማስረጃ ትንታኔ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ አብዝቶ ይፈለጋል። የሥራ ባልደረባን በማጭበርበርና በማታለል በመምታትና በማስመታት ከፍ ለማለት የሚሞክር
ካለ ዝቅ እንዲል መደረግ አለበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ በፖለቲካው መስክ የነቃ ተሳትፎ ከማያደርግባቸው ምክንያቶች አንዱ ምናልባትም ዋናው ይህው የግል ሕይወትና
ገጽ ግንባታ ላይ ያተኮረ የፖለቲካ አመራሮች ችግር ሳይሆን አይቀርም። «ወጣቶች ናችሁ ልምድ
የላችሁም» በሚል ሰበብ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን መሸፋፈን ለማንም የሚበጅ አልሆነም። ይህ ትውልድ ግን የጨለማ ጉዞ እንደማይፈልግ በግልጽ እያሳየ ነውና የአመራር አባላት
የላቀ ሞራል ይዘው ይገኙ ዘንድ ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment