Saturday, 11 February 2023

የመንግስትና የቤተ ክርስቲያን ስምምነት እንዴት?

    ጥር 14 ቀን 2015 ዓ/ም የተካሄደው ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሲመት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለመንግስትና ለሀገራችን ኢትዮጵያም ከፍተኛ ውጥረትን አስከትሏል። ቤተ ክርስቲያንም ሿሚዎችንም ተሿሚዎችንም አውግዛ ለየቻቸው። መንግስትም በበኩሉ ሕግ የማስከበር ሥራውን እንዲወጣ ቤተ ክርስቲያን አሳሰበች። ይሁንና መንግስት ለሕገ ወጡ ቡድን ሀሳብና ሞራል በመስጠት እንዲሁም ታጣቂዎችን በማሰማራት ሕገ ወጡ ቡድን አብያተ ክርስቲያናትንና መንበረ ጵጵስናዎችን በኃይል እንዲቆጣጠር ማገዙን ቀጠለ። በመሆኑም ጉዳዩ በዋናነት በመንግስትና በቤተ ክርስቲያን መካከል ሆነ። መንግስት ሕግ የማስከበር ግዴታውን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ ላለፉት ሦስት ሳምንታት ሲወተውት ቆይቷል። የካቲት ሦስት ቀን 2015 ዓ/ም መንግስትና ሲኖዶሱ ለሦስት ሰዓታት የፈጀ ስብሰባ በቤተ መንግስት አካሂደዋል። ይህን ተከትሎ ዛሬ የካቲት አራት ቀን 2015 ዓ/ም ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መግለጫ እንዳመለከተው መንግሥት የቤተ ክርስቲያኒቱን አቋም ሙሉ በሙሉ ተቀብሏል። 

    ይህም ማለት ቤተ ክርስቲያኒቷ በራሷ ቀኖና መሠረት ችግሯን ትፈታለች፣ ተመሰረተ የተባለው ሲኖዶስ ይፈርሳል፣ ሕገ ወጡ ሿሚዎችና ተሿሚዎች በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ጉዳያቸው ይታያል፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተገኙ ክርስቲያኖችን በመግደልና በመደብደብ የተቆጣጠሯቸውን አብያተ ክርስቲያናትንና የሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስናዎችን ለቤተ ክርስቲያን ይለቃሉ፣ በዚሁ ችግር ሳቢያ የታሰሩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈታሉ፣ የተገደሉ፣ የተደበደቡና እንግልት የደረሰባቸውን ለመካስ ሕጋዊ ርምጃ ይወሰዳል፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናትና ምእመናን ያለምንም ችግር እየተዘዋወሩ አገልግሎታቸውን ይሰጣሉ። እነዚህ ስምምነቶች በፍጥነትና በጥራት የሚፈጸሙ ከሆነ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለመንግስትና ለሀገራችን ኢትዮጵያም ታላቅ እፎይታን የሚሰጡ ናቸው። 

    መንግስት በተከታታይ ሲሰጣቸው ከቆዩት ማስፈራሪያ አዘል መግለጫዎች አኳያ እንዲሁም ውጥረትና ጥርጣሬ የሞላበትን ታሪካዊ የመንግስትና የቤተ ክርስቲያንን ግንኙነት ስናጤን ይህ ስምምነት አዲስ ክስተትና ታላቅ የሚባል ድል ነው። የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ ስምምነት ስለሆነ ፋይዳው ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ነው። መንግስታዊ አምባ ገነንነትን እራቁቱን ያስቀረ ተጋድሎ ነውና። እምነት፣ መንፈሳዊ ጥንካሬና ጽናት ያስገኙት ሕኝ የማስከበር ልዕልና ነው። ይህ ደግሞ ሰላምንና አንድነትን የሚያፈቅርን ማንኛውንም ሰው የሚያስደስት ነው። በዚህ ክስተት የሚያዝን ብሎም ለክፉ የሚነሳሳ ካለ የአእምሮ ጤንነቱን መጠራጠር አለበት። 

    መንግስት ባልተለመደ መልኩ ይህን ያህል ርቀት ሄዶ ሊስማማበት የቻለበት ምክንያት በራሱ ለውይይት ጋባዥ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት መንግስትና ቅዱስ ሲኖዶስ ትናንት የካቲት ሦስት ቀን ባደረጉት ሰፊና ጥልቅ ውይይት መሠረት መንግስት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና ቀኖና በደንብ በመረዳቱ በውሳኔው የተስማማ እንደሆነ ይገልጻሉ። ዳሩ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ (ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የብልጽግና ፓርቲ እና የመንግስት ድንበር የተደበላለቀ ስለሆነ በዚች መጣጥፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስትንም ይወክላሉ) ይህን ጉዳይ ከዚህ በፊት አያውቁትም ለማለት የሚያስችል ምክንያት ያለ አይመስለኝም። በበርካታ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ራሳቸውን እንደ ባለሙያ በመቁጠር የሚሰጧቸው ገለጻዎች መሠረታዊ የዕውቀት ችግር እንደሌለባቸው አመላካች ናቸው። አይደለም እሳቸው ማንኛውም ሰው እያንዳንዱ የሃይማኖት ተቋም የራሱ ዶግማና አሠራር እንዳለው ያውቃል። 

    በመሆኑም የነበራቸውን ጠንካራና አስፈሪ አቋማቸውን ሙሉ በሙሉ ቀይረው መስማማታቸውን እንዲገልጹ ያስገደዳቸው ጉዳይ ቢኖር ፍርሃትና ስጋት ነው። የተቀናጁና ተከታታይነት የነበራቸው ሀገርና ዓለም አቀፋዊ ተቃውሞዎች ከፍተኛ ፍርሀትና ስጋት ፈጥረውባቸውል። ፍርሃት ለሥልጣናቸው፣ ከተጠያቂነት ጋር ሊነሳ የሚችል ፍርሃት፣ ፍርሃት ለግል ሕይወታቸው፣ ምናልባትም የኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም እንዳይናጋ ከማሰብ የመነጨ ፍርሃት። በመሆኑም ቀጥለው የተዘረዘሩት ዐበይት ጥረቶች መንግስት ቤተ ክርስቲያን ያቀረበችውን ሀሳብ ሙሉ በሙሉ እንዲቀበል አስገድደውታል ቢባል ብዙም የሚያከራክር አይመስለኝም። 

  • የቅዱስ ሲኖዶስ ፍጹም አንድነትና መንፈሳዊ ቆራጥነት የተሞላበት አመራር
  • የካህናትና የየክፍል ሓላፊዎች ቁርጠኝነት
  • የምእመናን አንድነት፣ ቆራጥነትና ለሲኖዶስ መታዘዝ
  • ምድር አንቀጥቅጥ ሰላማዊ ሰልፎች የሚመስሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄዱ የጾመ ነነዌ ጉባኤዎች 
  • የኢትዮጵያ የሃይማንቶች ኅብረት ለቤተ ክርስቲያን ያሳዩት ድጋፍ
  • የጥበብና የሌሎች ታዋቂ ሰዎች (ኦርቶዶክሶች፣ ሙስሊሞችና ፕሮተስታንቶች) ከቤተ ክርስtiያን ጎን መቆም
  • አንዳንድ ወታደሮች የሰጧቸው ሓላፊነት የተሞላባቸው ድጋፎች 
  • የክልል መንግስታት ያሳዩት ድጋፍ (በኋላ ላይ አቋም ቢቀይሩም)
  • የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጠንካራ መግለጫ
  • የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ 
  • የሩሲያ መንግስትና ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ
  • የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ድጋፍ
  • የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ታሪካዊ ሰላማዊ ሰልፎች 
  • ወቅታዊ መረጃዎችን በማስተላለፍ የመገናኛ ብዙኃን ድርሻ (ከመንግስት ሚዲያዎች በስተቀር)
እነዚህ ሁሉ አካላት ከቤተ ክርስቲያን ጎን የቆሙት መንግስታዊ እብሪትን ከመጸየፍና የሕግ የበላይነት እንዲስፍን ካላቸው ጽኑ አቋም የተነሳ ነው። መንግስት ከሕግ በላይ ሳይሆን ከሕግ በታች ሆኖ ሕግን እንዲያከብርና እንዲያስከብር የሚወተውቱ ነበሩ። እንዲህ አይነት የሃይማኖትና የሀገር አጥር ወይም ገደብ ያላገዳቸው የሕግ የበላይነትን የሚናፍቁ ትብብሮች በቀጣይነት የሚስፋፉ ከሆነ ለሀገር አንድነትና ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽዖ ሊያደርጉ ይችላሉ። መንግስት አምባ ገነን ወይም ሕግ ገነን እንዳይሆን የራሳቸውን ሚና ይወጣሉ። 
    ዳሩ ግን በመንግስትና በቤተ ክርስቲያን መካከል የተደረሰው ስምምነት በታሰበው ልክ ወደመሬት ላይወርድ ይችላል። ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሚኒስትሮቻቸው ቢስማሙም ከፌደራል መሥሪያ ቤቶች እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉት የመንግስት አካላት ውሳኔውን በበጎ ላይመለከቱት ይችላሉ። በተለይም በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የስምምነቱ ተፈጻሚነት አስጊ መስሎ ይታያል። እንዲሁም ሰዎችን ለያይቶና በስውር የማጥቃት ዘመቻ ሊካሄድ ይችላል። በውሳኔው ያልተደሰቱና ትርምስ ለማምጣት የሚፈልጉ ኀይሎች የተቀነባበረ ሴራ ሊኖራቸው ይችላል። በሸኔ ስም ግድያዎችና ሌሎችም ግፎች ለፈጸሙ ይችላሉ። ቅን ልቡና ቢኖር እንኳን በጥራት ለመፈጸም የሚያስችል መንግስታዊ አቅም ቶሎ ላይገኝ ይችላል። እንዲሁም ልዩ ክትትልና ስለላ በአባቶችና በቤተ ክርሲያን ላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይችላል። በመሆኑም መላው የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላትና ኢትዮጵያውያን ሁሉ የስምምነቱን አፈጻጸም በተመለከተ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ እንዲሄዱ ያስፈልጋል። ከእነዚህ ስጋቶች አኳያ ሲታይ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ መራዘሙ አግባብነት አለው። ስምምነቱን የሚጥሱ ማናቸውም አካሄዶች ሲታዩ ወዲያውኑ ተከታትሎ ሰላማዊ ሰልፎችንና ሌሎች ርምጃዎችን ለመውሰድ ያስችላል። 

    ባጠቃላይ ሲታይ የተገኘነው ድል ለኦርቶዶክሳውያን ብቻ ሳይሆን ለመንግስት እንዲሁም በሕግ የበላይነትና በሃይማኖት ነጻነት ለሚያምኑ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ነው። በመንግስትና በቤተ ክርስቲያን መካክል የተደረሰው ስምምነት የሕግ የበላይነትን ያስከበረ ስለሆነ። ይሁን እንጅ ተጋድሎው ተጀመረ እንጅ አላለቀምና በንቃት መከታተልን ይጠይቃል። በተለይም ቅዱስ ሲኖዶስ መንፈሳዊ ጥንካሬውንና አስተዳደራዊ አቅሙን ማጎልበትና ማዘመን፣ ቤተ ክርስቲያንን ሰቅዘው ከያዟትና ለሕገ ወጥ ሲመቱም እርሾ ሆነው ያገለገሉትን መንደርተኝነትና ሌብነትን መዋጋት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የክህነት አሰጣጥ እንዲኖር ማድረግ፣ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኗ የአስተዳደር እርከኖች የሚሠሩ የተወሰኑ አገልጋዮች በሰሞኑ ግርግር አቋማቸው የዋለለባቸው ስላሉ አመለካከት ላይ ያተኮሩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንዲሰጡ ማድረግ፣ ወሳኝነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ጥራት ያለውና ለፖሊሲና ለሌሎችም ውሳኔዎች ግብአት የሚሆን ዕውቀት ለመፍጠር ይቻል ዘንድ የጥናትና ምርምር ማዕከል ማቋቋም፣ እንዲሁም ምእመናን በቋሚነት የሚገለገሉባቸውንና እና የሚያገለግሉባቸውን ምቹ ሁኔታዎች በየደረጃው መፍጠርና አቅማቸውን መገንባት ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። 

                                አንድ ፓትርያርክ፣ አንድ ሲኖዶስ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን!

No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...