ሰባት ዓመት ገደማ ነው:: ባህር ዳር ከተማ ፓፒረስ ሆቴል ሻይ ቡና እያልኩ በሆቴሉ የመዋኛ ቦታ ዙሪያ እንደትል የሚርመሰመሱ ህጻናትና አዋቂ ሰዎችን እመለከታለሁ:: በሰዎች ብዛትና በመዋኛ ቦታው ስፋት አለመመጣጠን እየተገረምኩ ሳለ ድንገት የጦር ወሬ የተሰማ ይመስል ህዝቡ ሁሉ መሯሯጥ ጀመረ:: የሆቴሉ ሥራ አሥኪያጅና ሌሎች ሠራተኞች ዋናተኞችንና ሌሎች ተስተናጋጆችን ማዋከብ ጀመሩ:: ሁሉም ሰው ሆቴሉን ባስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ ይለማመጣሉም ያመናጭቃሉም::
እኔም ባላሰብኩት ሰዓት እንድወጣ በመገደዴ እየተናደድኩም ሠራተኞች ይቅርታ እንዲጠይቁም በዓይኔ እየተማጸንኩ ወደ ዋናው በር ጉዞዬን ቀጠልኩ:: ሌላው በሁኔታው የተበሳጨ ተስተናጋጅ «ለምን ቀደም ብላችሁ አልነገራችሁንም? እንዴት እንደ ቆሻሻ ጠርጋችሁ ትጥሉናላችሁ» እያለ መደንፋት ጀምሯል:: የሆቴሉ ሠራተኛ ጸጉሩን ፎከት እያደረገ በትህትና ማስረዳት ጀመረ::
እኔም ባላሰብኩት ሰዓት እንድወጣ በመገደዴ እየተናደድኩም ሠራተኞች ይቅርታ እንዲጠይቁም በዓይኔ እየተማጸንኩ ወደ ዋናው በር ጉዞዬን ቀጠልኩ:: ሌላው በሁኔታው የተበሳጨ ተስተናጋጅ «ለምን ቀደም ብላችሁ አልነገራችሁንም? እንዴት እንደ ቆሻሻ ጠርጋችሁ ትጥሉናላችሁ» እያለ መደንፋት ጀምሯል:: የሆቴሉ ሠራተኛ ጸጉሩን ፎከት እያደረገ በትህትና ማስረዳት ጀመረ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለት ሞተር ሳይክል የሚነዱ ሰዎች ከሆቴሉ በር ላይ በሚገርም ፍጥነትና ቅልጥፍና ተከሰቱ:: ሞተራቸውን አጥፍተው ከሆቴሉ በመውጣት ላይ ያሉ ሰዎችን በቀኝ እጃቸው ወደፊት ይጠርጓቸው ጀመር:: ከሚወጡት ሰዎች የመጨረሻው በመሆኔ የወጠምሻውን ትኩረት መሳብ ቻልኩ:: በፈረጠመ እጁ ትክሻዪን ይዞ ወረወረኝ:: ከፊት ለፊት ቆማ ከነበረችው የዲኬቲ ኢትዮጵያ መኪና ላይ እጆቼን በማሳረፍ ከከፋ ውድቀት ዳንኩ:: ወዲያውኑ ጥራታቸው የሚማርክ ኮብራዎች (እባቦች አላልኩም መኪኖች እንጅ) ተከታትለው ወደ ሆቴሉ ገቡ:: ፕሮጀክት ሊመርቁ የመጡ ክቡር ፕሬዚደንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስን አጅበው:: የዚያ ሁሉ ግርግርና ወከባ ምሥጢር ተገለጠልኝ:: «ቀደም ብዬ ባውቅ እኮ ራሴን በተገባ ፍጥነት መሰወር እችል ነበር» እያልኩ ወደፊት ቀጠልኩ::
ይህ እንግዲህ መቅድም መሆኑ ነው ዋናው ጉዳይማ ቀጥሎ ያለው ነው::
ክቡር ፕሬዚደንት ግርማ ሥልጣናቸውን እየጨረሱ ነው:: በመጪው ጥቅምት ወር አዲስ መሪ ይሰጠናል:: አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በአዲስ ዓመት ለኢትዮጵያ ህዝብ ለመሰጠት ዝግጁ እንደሆነ ደጋግሞ ነገረን:: ብዙዎቻችንም እጩውን ኃይሌን እንደማንቀበል ተናገርን:: ተበሳጨንም:: አንዳንዶቻችንማ የሰውየውን የማሰብና የመናገር ተፈጥሮአዊ ነጻነትና መብት በመደምሰስ የተሳደብንም አለን:: የሱ ስም ሲነሳም የሚያቅለሸልሸን
አንጠፋም::
ጥያቄው መሆን ያለበት ግን «የፕሬዚደንቱ ሥልጣንና መብት እስከምን ድረስ ነው?» የሚለው ነው:: ያገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስለሚመረጠው ሰው ብዙም እንዳናስብ ያስገድደናል:: ኃይሌ ቀርቶ አጼ ቴዎድሮስ ከሙታን መካከል ተነስቶ ቢሾም ምን ዋጋ አለው? በርግጥ መይሳው የሚያሰራው ነገር ከሌለ ቢያንስ ራሱን ከዙፋኑ ይሰውራል ያጠፋል:: የምንወደው ሰው ፕሬዚደንት ቢሆን ሥልጣን ከሌለው ምን ዋጋ አለው?
ይህም ቢሆንም ግን የሚመረጡት መሪዎች የመሪ መንፈስና ብቃት አይኑራቸው ማለት አይደለም:: ፕሮጀክት ለመመረቅ: ዲፕሎማቶችን ለመቀበልና ለመሸኘት: እንዲሁም ስለአዲስ ዓመት ሲባል ለተወሰኑና ለታደሉ እስረኞች ይቅርታ ለማድረግ ወዘተ ንቃትና ሙቀት ያለው መሪ ያስፈልጋል:: በዚያው ላይ ሲያዩትም ውጭ አገር ሲሄድም የማያሳፍር ቢሆን ይመረጣል::
ለኔ ግን አዲሱ መሪያችንን በተመለከተ በጣም ብዙ ጉዳዮችን ማየት አለብን:: ከግለሰቦች ይልቅ እነዚህ ጉዳዮች ላይ መወያየቱ ለአእምሮም ለታሪክም የተመቸ ነው:: መሪ ለመሆን የሚያስፈልጉ መስፈርቶችና ከባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ እንወያይ:: ዋና ዋናዎቹን ቀጥዬ ላቅርባቸው:: እነዚህ ጉዳዮች ላለፉት
ሁለት ዓስርት ዓመታት ገዝፈውና አንዱን ከሌላው ከፋፍለው ታይተዋል:: እናም ጉዳዮችን ፍርጥርጥ አርጎ መወያየቱ ጠቃሚ እንጅ ጎጅ
አይደለም::
ወንድ ወይስ ሴት?
እስካሁን ድረስ መሪዎቻችን ወንዶች ናቸው:: አሁን ግን ሴት ፕሬዚደንት ብትኖረን ለየት ያለ ስሜት ሊሰማን ይችላል:: ለዚህ ብቻ ሳይሆን ሴቶች ለየት ያለ ዝንባሌና ችሎታ አላቸው:: በተለይ ችግር አፈታትና ነገር አተናተን ላይ:: በዚያው ላይ ዘመኑ እኩልነትን ሰባኪ ነው:: ስለዚህ ምረጥ ብባል ሴት መሪ ለኢትዮጵያ እመኛለሁ:: ይህ ከሆነ ለአብዛኛው ሴቶች ጥሩ አርአያ ይሆናል:: ሴቶች በፖለቲካው ዘርፍ ከፍ ከፍ ማለት አለባቸው ብዬ አምናለሁ::
ጎልማሳ ወይስ አዛውንት?
መሪ ሲባል ያዛውንቶች ሥራ አድርገው የሚወስዱ አይታጡም:: ለኔ ግን መሪዎች በፍጥነት ማሰብና መራመድ የሚችሉ መሆን አለባቸው:: ከፊት ቢያስቀድሙት ከኋላ ቢያስከትሉት የማያሳፍር መሆን አለበት:: ይህም ሲባል ሮጦ ያልጠገበ ጎረምሳ ተሾሞ «ፈረሱም ያው ሜዳውም ያው» ይበለን ማለቴ አይደለም:: ስጠቀልለው መሪዎች ከ40 እስከ 60 ዓመት የእድሜ ክልል ያሉ ቢሆኑ ይመረጣል::
ቀጣዩ መሪ ሙስሊም ወይስ ክርስቲያን ይሁን? ለኔ መሪው ከማንኛውም ሃይማኖት
ተከታዮች ቢመረጥ ችግር የለውም:: ችግር የሚኖረው የመሪ ሥልጣኑን ተመርኩዞ የራሱን እምነት ለማስፋፋት ሲጥር ነው:: ኦርቶዶክስ ሆነ ተሃድሶ ፕሮቴስታንት ሆነ ካቶሊክ ሙስሊምም ቢሆን ላገሩ የሚታትርና ለህግ ተገዥ ከሆነ ችግር የለውም::
የትምህርት ወይስ የማስተዋል ደረጃ?
መሪው ምሁር ይሁን ወይስ ጨዋ? ልክ ነው ምሁር ማለት ምን ማለት እንደሆነ መተንተን ቀላል አይደለም:: የሆነው ሆኖ ብዙ ጊዜ ምሁር ሲባል ማስትሬት ወይም ዶክትሬት ድግሪ ያለው እንደማለት ነው:: ግን ድግሪ ሳይኖረው ሊቅና ጠቢብ የሆነ ሰው ሞልቷል:: ድግሪ ኖሮት ደግሞ ከንቱ የሆነ ሰው አለ:: በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትምህርት ጥራትና ጥቅም አሰቃቂ ደረጃ ላይ ደርሷል:: ከፍተኛ ድግሪ ያለው ሞልቷል:: ስለዚህ ጥያቄው መሆን ያለበት ሰውዬው አስተዋይና ጠቢብ ነው ወይ እንጅ ተምሯል ወይ አይደለም:: በመሆኑም ቀጣዩ መሪያችን አርቆና አቅርቦ አሳቢ ታጋሽና ይቅር ባይ ራእይ ያለውና ህዝብ ወዳጅ መሆን አለበት::
ኢትዮጵያ ቋሚ ትዕይንት የሆነች የብሄረሰቦች ሙዚየም ናት:: ማናኛውም አቅሙና ችሎታ ያለው ዜጋ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ መሪ የመሆን እድል አለው:: ይህም ማለት ቀጣዩ መሪ ከየትኛውም ብሄረሰብ ቢሆን የሚገርም መሆን የለበትም:: እንዲያውም በታሪክ አጋጣሚ መሪ የመሆን እድል ያላገኙ ሰዎች ከአናሳ ብሄረሰቦች መሾሙ ፍትሃዊ ነው:: ለፖለቲካ ፍጆታ
የሚደረግ ሹመት ግን በብሄረሰቦች መቀለድ እንጅ ለነሱ ማሰብ አይደለም:: ይህ ማለት ግን ለያንዳንዱ ሥራ የብሄር ፖለቲካ እንደልቅ ማለት አይደለም:: መስፈርቱን ካሟላ ማንም ከየትኛውም ብሄር መሪ ቢሆን ግድ የለኝም::
ፕሬዚደንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ, Google pic
ፕሬዚደንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ, Google pic
ከዲያስጶራ ወይስ ከአገር ቤት?
ኢትዮጵያውያን በሁሉም የፈረንጅ አገር ሞልተናል:: በያለንበት ሆነን አገር ቤት ለሚከናወን ጉዳይ ያገባናል ባይ ነን:: ዶላር እንልካለን ቤት እንሰራለን ኢንቨስተር ሆነናል:: ብዙ የተማሩና ልምድ ያላቸው በውጭ ይኖራሉ:: ስለዚህ የመሪነቱም ቦታ ውጭ ካሉ ኢትዮጵያውያን ቢያዝ ምንም አይደለም ሊያስብል ይችላል:: እኔ ግን በዚህ ሃሳብ ደስተኛ አይደለሁም:: አገር ቤት ያለ ሰው ችግሩንም መከራውንም እለት እለት ቀማሽ ነው::: ለውጥ እንዲመጣም የሚችለውን ያደርጋል:: ከአገር ቤት መሪ ቢሾም ተመሪውን በሚገባ ያውቃል:: መሪ ለመሆን መሰደድ እንደማያስፈልግም ሊያመላክት ይችላል:: ዲያስጶራው በአቅም ግንባታ ዘርፍ ቢያተኩር የበለጠ ውጤታማ ይሆናል::
ቀጣዩ መሪስ ማን ይሆን,Goodle pic
ቀጣዩ መሪስ ማን ይሆን,Goodle pic
ይህ ሃሳቤ እንግዲህ ፍጹም ምናባዊ ነው:: መራጩ አስመራጩ ሿሚው ያው የኢሕአዴግ መንግስት ነው:: ይህ መንግስት ደግሞ ያይኑ ቀለም ያማረውን ብቻ ይሾማል:: ስንት በአይናቸው ማማር ብቻ የተሾሙ ሚኒስቴሮች ዳይሬክተአሮችና ዲፕሎማቶች እንዳሉን ጠንቅቀን እናውቃለን:: ቢሆንም ግን ምኞታችንንና መሆን ያለበትን ከመናገር ለአፍታም አንቦዝንም:: ዝም ማለት ባለው አድካሚ አሰራር ከመተባበርና ከመደሰት ብዙም አያንስም:: የእውነቱን እንናገር:: የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው እውነተኛ መሪ እንጅ ተመሪ መሪ አይደለም::
"የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው እውነተኛ መሪ እንጅ ተመሪ መሪ አይደለም::" ይህ አባባል ደስ ይለኛል: ግን ይህ መቼ ነው የሚሆነው????????????????
ReplyDeleteIt is an amazing article.Dr Teklu
ReplyDelete