Saturday, 12 July 2014

አገራዊ ስሜት ለምን ይጎድለናል? የመጨረሻ ክፍል

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ቀዝቃዛ ስሜት እንዳለውና በቂ ተሳትፎ እንደማያደርግ በመደምደም የችግሩን መንስኤዎች ወይም ምክንያቶች በተከታታይ ጽሁፎች ማቅረብ ጀምሬአለሁ:: ክፍል አንድ አገራዊ ስሚት ምን ማለት እንደሆነ ካብራራ በኋላ ብዙው ኢትዮጵያዊ በብሄራዊ ጉዳዮች የመሳተፍ ዝንባሌና ፍላጎት እንዲሁም ሥነ-ልቡናዊ አቅም እንደሌለው አትቷል:: ክፍል ሁለት ደግሞ ባህላዊ አስተምህሮቶቻችን ፖለቲካዊ አገራዊ ጉዳዮችን በንቃት እንዳንከታተል ተጽዕኖ እንዳደረጉብን አብራርቷል:: እንዲሁም ብዙ ሰዎች ተሳትፎ ቢያደርጉ መንግስት በህይወታቸው: በቤተሰባቸውና በሥራቸው ላይ መከራ እንደሚያመጣባቸው በማመን "ዝምታ ወርቅ ነው"ን እያዜሙ እንደሚኖሩ አትቷል:: በዚህ የመጨረሻ ክፍል ደግሞ  ስለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የበኩላችንን አስተዋጽዖ እንዳናደርግ ያደረጉንን ሌሎች እንቅፋቶች ለመዘርዘር እሞክራለሁ:: 

ገዥው ፓርቲና መንግስት      

በኢትዮጵያ ታሪክ መንግስትና ገዥ ፓርቲ በወጉ ተለይተው የታዩበት ዘመን የለም:: ኢሠፓ ማለት መንግስት: መንግስት ማለት ኢሠፓ ማለት ነበር:: አሁን ደግሞ  ኢሕአዴግ ማለት መንግስት: መንግስት ማለት ኢሕአዴግ ማለት ነው:: ቢሆንም ግን ሁለቱ አካላት ፍጹም የተለያዩ መሆን እንዳለባቸው እንዳንረሳ  ገዥው ፓርቲና መንግስት የሚል ርዕስ መርጫለሁ:: 

የኢሕአዴግ መንግስት የዜጎችን ንቃተ ኅሊናና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማጎልበት ሲገባው ሁሉም ዜጋ በራሱ አገር አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር አድርጓል:: እንዲያውም በክፍል አንድና ሁለት እንዲሁም ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት በቂ ፖለቲካዊ አገራዊ ስሜት እንዳይኖር ካደረጉት ምክንያቶች ወይም መንስኤዎች ሁሉ ይህኛው ወሳኝ እንደሆነ  እሞግታለሁ:: መንግስት በሚከተሉት መንገዶች ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳዮች ነቅተው እንዳይሳተፉ አድርጓል:: 
  • በተንኮል የታሸ የብሄር ፖለቲካ እንደመርህ በመያዙ በበርካታ ወገኖች ላይ ብዥታና ጥርጣሬ ፈጥሯል:: የብሄር ፖለቲካ ግለሰቦች ላይ የማይደርስ የቡድን መብትን ይሰብካል:: የቡድን መብትን  ወደግለሰብ መብትተርጉመው ተጨባጭ ለውጥን የሚያመጡ ተቋማት የሉም:: እንዲኖሩም አይፈለግም:: በመሆኑም መንግስት 'ነጻ አውጥቼሃለሁ' ብሎ የሚፎክርለት የእያንዳንዱ ብሄር አባል አሁንም ርጥብና ከባድ የጭቆና ቀንበር ትክሻው ላይ ተጥሎበታል:: በጥቂት የyeብሄሩ ልሂቃንና በመንግስታዊ መገናኛ ብዙኅን የሚለፈፈው ዴሞክራሲና እድገት የት እንዳለ አብዛኛው ህዝብ አያውቅም:: ስለአገራዊ ኢትዮጵያዊ ጉዳዮች ጥያቄ ማንሳትማ የረቀቀ ነገር ነው የሚመስለው:: አንዳንድ ጥያቄዎችና ውይይቶች ቢኖሩም በየክልሉ ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ታጥረው ቀርተዋል:: 
  • ያለምንም ችግር በብሄራዊ ጉዳዮች መሳተፍ የሚቻለው መንግስት የሚሰራውን ሁሉ ያለምንም ትችት መቀበል ሲቻል ብቻ እንደሆነ በአንድም በሌላም መንገድ ይነገራል:: መንግስትን መደገፍ ወይም የገዥው ፓርቲ አባል መሆን የሚያስገኘውን ጥቅማ ጥቅም ከካድሬዎች መስማት የተለመደ ነው::   
  • በአንጻሩ ደግሞ  መንግስትን መቃወም ወይም መተቸት አክራሪነት ወይም ጽንፈኝነት ወይም ያለፈውን ሥርዓት ናፋቂነት እንደሆነ ተወስዶ  ከሥራ ለመባረር ወይም ከደረጃ ዝቅ ብሎ ለመስራት: ለእስራት: ለድብደባ: ለስደትና ለሞት እንደሚያበቃ ህዝቡ ዕለት ከዕለት እያየው ነው::
  • ቁልፍ የመንግስት የኃላፊነት ሥራዎች ባልተማሩና ራእይ በሌላቸው ሰዎች መያዛቸው በሠራተኛው መካከል ሊኖር የሚገባውን የሃሳብ  ልዩነትና  ጤናማ ክርክር አጥፍቷል:: እነዚህ አይነት ኃላፊዎች አብዝተው የሚጨነቁት ለፍትህ: ለሰው ልጅ መብትና እድገት ሳይሆን ሊነሱ የሚችሉ ትችቶችን ለማፈንና ለማጥፋት  ነው::
  • ይባስ ብሎ ሁሉም የመንግስት ሠራተኛ የኢሕአዴግ አባል እንዲሆን በይፋ ይነገረዋል:: አዲስ የሚቀጠሩ ሠራተኞች ከኮንትራታቸው ጋር የአባልነት ፎርም ይሰጣቸዋል:: አባልነትን ያልፈለገ ከምንም አይነት ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲርቅ ይመከራል:: አባልነትን ያልፈለገ ወይም መቃወም የጀመረ የውጭ አገር የትምህርት እድል: የደመዎዝ ጭማሪና የደረጃ እድገት እንዲሁም የሥራ ዝውውር አያገኝም:: ይህ ጫና አብዛኛው ሠራተኛ ለብሄራዊ ጉዳዮች ጀሮ ዳባ ልበስ ብሎ እንዲኖር አስገድዶታል:: 
  • የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችንና የሙያ ማኅበራትን በማዳከምና መሰል ተቋማትን በተለጣፊነት በመፍጠር ለአንድ አገር ልዕልና ሊኖር የሚገባውን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ክፉኛ አቀጭጯል:: 
  • ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ክፉኛ አዳክሟል:: በካድሬዎች እንዲመሩ ተደርጓል:: ምሁራን አንገታቸውን ደፍተው እንዲኖሩ የቀለም አባት ብቻ እንዲሆኑ ሥራ ተሰርቷል:: የትምህርት ጥራት በአሳሳቢ ሁኔታ አሽቆልቁሏል:: ተመራቂዎች የእውቀትና የጥበብ እንዲሁም የማስተዋል ሰዎች እንዳይሆኑ ተደርጓል:: ተመራቂዎች የመጡበትን ብሄርና ክልል ብቻ እያሰቡ እንዲጨቃጨቁና አገራዊ ስሜትን እንዳያጎለብቱ ተደርጓል::  

   የተቃዋሚ ኃይሎች 

አንዳንዶች ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠሩና ለሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ መንግስትን ብቸኛ ተጠያቂ ያደርጋሉ:: ለእኔ ግን መንግስት በዋናነት ሊጠየቅ ይገባዋል እንጅ ብቸኛው አካል አይደለም:: ሁሉም አካል ደረጃው ይለያይ እንጅ ለችግሮቻችን ተጠያቂ ነው:: አገራዊ ስሜት እንዳይጎለብትና በቂ ተሳትፎ  እንዳይኖር በተቃዋሚ ጎራ ያሉ ወገኖችም ድርሻ አላቸው:: የተቃዋሚ ኃይሎች ስል ከገዥው ፓርቲ በአንጻሩ የቆሙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን: ድርጅቶችን: ጦማሪዎችን: ጸሃፊዎችንና መድረኮችን ነው:: እነዚህ አካላት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የራሳቸውን ተጽእኖ በተለያዩ  መንገዶች እያደረጉ ነው:: ቀጥለው የተዘረዘሩት ዋናዎቹ ናቸው:: 

  • በንግግሮቻቸውና በጽሁፎቻቸው ጥላቻ ስድብና የበቀል ስሜት ስለሚታይ ህዝቡን ለመልካም ተሳትፎ  በቀላሉ አይጋብዝም:: እሳት የሚተፉ ብዕሮች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የጎላ ነው:: መንግስትንና ባለሥልጣናትና መርገም: መሳደብ: ማብጠልጠል ብቻ የትም አላደረስንም:: የትም አያደርሰንምም:: ኢሕአዴጎችን ሆዳም: ባንዳ: ገዳይ: ደንቆሮ ወዘተ ብንላቸው ራሳችንን በህዝባችን ከማስገመት ውጭ ምንም ጥቅም የለውም:: በተለይ አንዳንድ ጦማርያንና ጸሃፊዎች ለዚህ የተፈጠሩ ይመስላል:: በስድብና በርግማን የሚማረክ ህዝብ ወይም የሚሸነፍ መንግስት የለም::  
  • አምባገነን ሥርዓት ኢትዮጵያን እንዳንገላታት ቢሰብኩም ራሳቸው በስብሰባዎቻቸው: በግል ህይወታቸውና ሥራዎቻቸው ዘንድ ኢ-ዴሞክራት የሆኑ አሉ:: የራሳቸውን ሃሳብ እና ቅርብ ወገን ብቻ የሚወዱና ሌሎችን በነገር የሚገርፉ: ለጋራ ውሳኔዎች የማይገዙ: ፍትህና ነጻነትን የሚጋፉ አካላት ህዝቡን አሳምነው ትርጉም ወዳለው ፖለቲካዊ ተሳትፎ  ለማምጣት እንዴት ይቻላቸዋል? 
  • የፖለቲካ ፓርቲዎች አላስፈላጊ ብዛታቸውና መናበብ አለመቻላቸው ትክክለኛ የለውጥ ሐዋርያ ስለመሆናቸው በህዝቡ ዘንድ ጥርጣሬን ፈጥሯል:: ዘርን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ ድርጅቶች እንዴት ብሄራዊ ስሜትን በቀላሉ ሊፈጥሩ ይችላሉ? 
  • ብዙዎች የተቃዋሚ ኃይሎች ከፍተኛ የሆነ የአቅም ውሱንነት አለባቸው:: አብዛኞቹ በአመራር ላይ ያሉ ሰዎች የፖለቲካ ሥራቸውን የሚሰሩት በትርፍ ጊዜቸው ነው:: ይባስ ብሎ አንዳንድ ሰዎች ብዙ ኮሚቴዎች ውስጥ አመራር ወይም አባል ሆነው ለመስራት ይሞክራሉ:: ጥረቱ የሚደነቅ ቢሆንም ሁሉም ሰው አመርቂ በሆነ ሁኔታ በሁሉም ኮሚቴዎች ገብቶ መስራት አይቻለውም:: የአቅም ውሱንነት ስላለ:: በመሆኑም በጥንቃቄ የተዘጋጀ እቅድና ህዝቡን መሰረት ያደረገ ትግል ለማካሄድ አዳጋች ነው:: በምርጫ ሰሞን የሚደረግ የዘመቻ ሥራ ውኃ ሊያነሳ አልቻለም:: ይህ ሁሉ ተደማምሮ ህዝቡ በአገራዊ ጉዳዮች ያገባኛል ስሜት እንዳይያዝ አድርጓል:: 
  • ወቅታዊ ሁኔታዎችንና እውነታን ያላገናዘቡ ንግግሮች ህዝቡ ጭራሽ ለፖለቲከኞች ጆሮውን እንዳይሰጥ እያደረጉ ነው:: የብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን መግለጫ የተከታተለ ሰው የሚረዳው ነገር አለ:: መንግስት ሊወድቅ እየተንገዳገደ እንደሆነና በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለውጥ እንደሚመጣ በድፍረት ለዓመታት ሲናገሩ ነበር:: ይህ አይነት ፕሮፓጋንዳ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል:: ፓርቲዎች የተናገሩትን የማይፈጽሙ አቅም አልባ  እንደሆኑ ህዝቡ ግንዛቤ ይወስዳል:: ለእነሱ ያለውን አመኔታ ይንደዋል::
  • አንዳንዶች ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ የሚገርም ግንዛቤ አላቸው:: ልክ እንደ ገዥው ፓርቲ የትናንት ታሪካችንን ሙሉ በሙሉ በመጥፎ  አይን የሚያዩና ከዛሬው ትውልድ ለትናንት በደል ካሳ የሚሹ አሉ:: ትግላቸው ከትናንት እንጅ ዛሬ በገሃድ ከሚያንገላታቸው ጭቆናና ድህነት ጋር አይደለም:: ይህም በህዝብ ዘንድ ሊኖር የሚገባውን ተሳትፎ አቀጭጯል::           

ድርጅታዊ አቋም  

ብዙ ሰዎች ደግሞ በአገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለመሳተፍ አቅሙና ፍላጎቱ ቢኖራቸውም ድርጅታዊ እገዳ አለባቸው:: የሚሰሩባቸው ወይም አባል የሆኑባቸው ድርጅቶች ወይም ማኅበራት ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ገለልተኛ እንደሆኑ መተዳደሪያ  ደንባቸው ያስጠነቅቃል:: በዚህም የተነሳ አባላት ከሚሰጣቸው መደበኛ ሥራ ውጭ ሌሎች ጉዳዮች ላይ በይፋ እንዲሳተፉ አይመከርም:: የሃይማኖትተቋማትና መንግስታዊ ያልሆኑ የእርዳት ድርጅቶች ለዚህ አይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው:: ጥቂት አባላት የሚመጣባቸውን ጫና ታግሰው የልባቸውን መናገርና መጻፍ ቢችሉም ብዙው መንጋ ግን ጸጥ ብሎ  መኖርን መርጧል:: የሚያሳዝነው ግን ድርጅትን ወክሎ መናገርና በግል ራስን ሆኖ መናገርን ለይቶ አለማየት ነው:: አንዳንድ ጸሃፊዎች ጽሁፋቸው የግል አመለካከታቸውን እንጅ የሚሰሩበትን ድርጅት እንደማይወክል ያስጠነቅቃሉ:: ይህን ቢያደርጉም መንግስት የሚሰሩባቸውን ድርጅቶች ለማስፈራራት ለማገድና ለመቅጣት ምክንያት ይሆነዋል:: ድርጅቶቻቸውም በጸሃፍት ሠራተኞቻቸው የተነሳ በመንግስት ጥርስ ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉ በገደምዳሜ ይነግሯቸዋል:: ይህም ጸሃፊዎች ከፖለቲካዊ ተሳትፎአቸው እንዲታቀቡ ወይም መንግስትን በማይስቡ ለስላሳ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ያስገድዳቸዋል:: 

ማጠቃለያ

ትርጉም ባለው መልኩ አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ተሳትፎ  ማድረግ ያልቻልንባቸውን ምክንያቶች ወይም መንስኤዎች ለመዘርዘር ሞክሬአለሁ:: ሌሎች ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም ለእኒ ዋናዎቹ ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ አለመኖር: የአቅም ማነስ: የተሳሳቱ ባህላዊ አስተምህሮቶች: ፍርሃትና ስጋት: አፋኝና አስጨናቂ የመንግስት አገዛዝ: አርአያ ሊሆን የሚችል የተቃውሞ  ፖለቲካዊ እስቅስቃሴ አለመኖር: እንዱሁም ገለልተኛ ድርጅታዊ አቋም ናቸው::  ህዝብን ለላቀ ንቃተ ኅሊና ለማብቃት የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እነዚህን ተግዳሮቶች በጥንቃቄ መመልከትና ለነሱም መፍትሄ መሻት ይኖርባቸዋል: የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ መንግስት ህዝብ የሚፈልገውን ለውጥ እስከሚያመጡ ድረስ ቁጭ ብሎ መጠበቅ አላዋጣም:: አያዋጣምም:: እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ተፈጥሮአዊና ሰብአዊ መብቶቹን በጥንቃቄ አውቆ ማንኛውም አካል ከሚያደርሰው ጭቆናና ጫና ራሱን ነጻ ማውጣት አለበት:: እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን መብት የማያስነካ ነብር መሆን አለበት:: ይህ ነብርነት በቤተሰብ: በጓደኛ: በዘመድ: በሥራ ባልደረባና አለቃ: በጎረቤት: በመንግስት: በሃይማኖትተቋማት: በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በሌሎችም አካላት ለሚደረግ ማንኛውም አይነት ጭቆና ወይም የመብት ጥሰት መሆን አለበት:: 

No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...