ሰላማዊ ትግልን አልፎ አልፎ በሚደረግ ሰላማዊ ሰልፍና በየአምስት ዓመቱ በሚመጣ ምርጫ መሳተፍ የምንወስነው ከሆነ ይህ የትግል ስልት ውጤት የለውም:: ዳሩ ግን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚነግሩን ሰላማዊ ትግል እጅግ ሰፊ ግን ተደጋጋፊ ስልቶችን ያካትታል:: ይህ ከግምት ውስጥ ሲገባ ወደ አንድ ድምዳሜ ይወስደናል:: ሰላማዊ ህዝባዊ ትግል በኢትዮጵያ አንዱዓለም አራጌ እንደገለጸው ገና ያልተሄደበት መንገድ ነው:: እስካሁን ፖለቲካዊ ለውጥ ያልመጣው አማራጭ የሰላማዊ ትግል ስልቶች ተቀነባብረውና በቀጣይነት ሥራ ላይ ስላልዋሉ ነው::
ምን ይደረግ ?
ሰላማዊ ትግል ውጤታማ ይሆን ዘንድ በርካታ ቅድመ ሁኔታዎች
መሟላት አለባቸው:: የአገራችንን ሁኔታ ስንገመግም
አንድ ሃቅ እናገኛለን:: ይህም ማንኛውንም አይነት ፖለቲካዊ
እንቅስቃሴ ለማድረግ መሪዎች እንደሚያስፈልጉ ነው:: ትግሉን የሚያስተባብር ኃይል በጊዜው በተነሱ የለውጥ ዘመቻዎች ሁሉ ነበር:: ጃንሆይንና መንግስታቸውን ለመጣል የተማረው ወገን ከዚያም ደርግ ለውጡን አስተባብሯል:: የደርግ መውደቅም አሁን ባለው
ገዥ ፓርቲና በሌሎች ተመርቷል:: በ97ቱ ምርጫ ቅንጅትና ኅብረት
አስተባብረዋል:: አሁንም ቢሆን ህዝቡ በንቃት
ለመብቱ እንዲታገል የሚያስተባብረው ኃይል ይጠብቃል.: ባህላችን ለመሪዎች ልዩ ግምት ይሰጣልና:: በሌሎች አገሮች እንደታየው ህዝቡ በራሱ ተነስቶ መንግስትን ሊጋፈጥ የሚችልበት እድል እጅግ የመነመነ ነው:: ለመናገር በሚከብድ ጭቆናና
ድህነት ውስጥ እያለ ዝምታን የመረጠው የሚመራው ስለጠፋ ነው:: የሚታመንና ብቃት ያለው መሪ ካገኘ ህዝቡ የራሱን ድርሻ ይወጣል:: በ1997 ህዝቡ ለቅንጅት የሰጠው ትብብር አብይ ምስክር ነው:: ታዲያ በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ ትግሉን ማን ሊመራው ይችላል?
የህዝቡን ልብና ኅሊና ያገኘ መሪ ወይም ፓርቲ ትግሉን
በፍጥነት ይመራዋል:: ችግሩ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች
ከመብዛታቸው ባሻገር በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተቀባይነት ያለው ማግኘት ከባድ ሆኗል:: ፓርቲዎች ተደራድረው ወደ አንድነት ወይም ውህደት የሚመጡበት እድልም ውሱን ነው:: በአሁኑ ወቅት መኢአድና አንድነት
ድርድር ላይ እንደሆኑ ይነገራል:: ጥረቱ የሚሳካላቸው ከሆነ ወደፊት
የተሻለ ሥራ ይጠበቃል:: ሁለቱ ቢዋሃዱም እንኳን ትግሉ
በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ተፋፍሞ ስለመቀጠሉ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም:: ብሄርን መሰረት ያደረጉ ፓርቲዎች የየራሳቸውን አካባቢዎች አጥረው ይዘዋልና:: ስለዚህ በብሄርና በቋንቋ የማይወሰን አደረጃጀት ሰላማዊ ትግሉን ይበልጥ ሊያፋጥነው ይችላል:: ጥያቄው ይህ አይነት አደረጃጀት
ወይም ኃይል ከየት ይመጣል የሚል ነው::
አስተባባሪ ግብረ ኃይል
ከላይ እንደተጠቆመው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት እንዲፈጥሩ መጠበቅ የሚከብድ
ይመስላል:: ያለው ብቸኛ አማራጭ እያንዳንዱ ፓርቲ የራሱን ምንነትና ማንነት እንደያዘ የጋራ ፕሮጀክቶችን መንደፍ ነው:: ይህም ማለት ፓርቲዎች ስማቸውንና የራሳቸውን ፕሮግራም እንደያዙ በጋራ ሊሰሯቸው የሚገቡ ጉዳዮችን አብሮ መለየትና መስራት
ነው:: ሁሉም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ባይቻል አብዛኛው ተገናኝቶ
መወያየትና ሁሉንም የሚወክል አስተባባሪ ግብረ ኃይል ማቋቋም ወሳኝ ነው:: ግብረ ኃይሉ
ለውጥ እስኪመጣ ትግሉን በበላይነት ይመራል::
አመቺና ውጤታማ የትግል ስልቶችን ለይቶ ለሁሉም ፓርቲና
ለህዝቡ በተለያዩ መንገዶች ይፋ ያደርጋል:: የሚመረጡት የትግል ስልቶች
በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በአንድ ጊዜ ሥራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል:: ተፈጻሚነታቸውን ይከታተላል:: የቋንቋና የባህል ልዩነት ስላለ እያንዳንዱ ፓርቲ የራሱ አባላትና ደጋፊዎች የሚበዙበትን አካባቢ በዋናነት ሊያስተባብር
ይችላል:: ዋናው ነገር የሚመረጡት የትግል
ስልቶች (ለምሳሌ የተቃውሞ ሰልፍ: ማእቀብ ማድረግ: ማግለል: ወዘተ) በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አንድ
ላይ መደረጋቸው ነው:: ይህ ከሆነ የተቃዋሚው ጎራ
ይበልጥ እየተባበረ እንደሄደ ህዝብ እና መንግስት ያውቃሉ:: አስገዳጅና አማራጭ ኃይል እንዳለም አመላካች ይሆናል:: በሁሉም ቦታ አንድ ላይ የሚደረጉ ትግሎች የፖሊስንና የካድሬውን ስምሪት ያሳሳዋል:: ይህም ሊከሰት የሚችለውን የተለመደ
ዱላና አፈና በእጅጉ ይቀንሰዋል:: መንግስት የፍርሃት መጠኑን
እንዲጨምርና ህዝብን እንዲያዳምጥ ያስገድደው ይሆናል::
ለአስተባባሪ ግብረ ኃይል የሚመረጡ ሰዎች ብቃትና ዝግጁነት ያላቸው መሆን አለባቸው:: ህዝብን የማስተባበር ልምድ
ያላቸው: ለጥቅምና ለዛቻ የማይንበረከኩ: የመናገርና የማሳመን ችሎታ ያላቸው: ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በህዝቦቿ እንደምትገነባ
የሚያምኑ: እያንዳንዱ ዜጋ ለትግሉ አስተዋጽዖ
ማድረግ እንደሚችል የሚያምኑና የሚያበረታቱ: ከስሜትና ወገንታዊነት እርቀው እውነትንና አመክንዮን በመጠቀም የሚመሩ: የሥልጣን ጥም ያላቃጠላቸው: መስዋእትነት ለመክፈል የተዘጋጁ: በሙስና የማይጠረጠሩና በህግ መብታቸው ያልታገደ: እንዲሁም ተራራ ወጥተው ወንዝ ተሻግረው መስራት የሚችሉ ቢሆን ትግሉ በአለት ላይ እንደተገነባ ቤት መውደቂያ
አይኖረውም:: አስተባባሪዎችን መንግስት ሊያስራቸው
ስለሚችል ተጠባባቂ መሪዎች አስቀድመው ከየፓርቲው ተመርጠው ዝግጁ መሆን አለባቸው::
ለህዝብ ቆሜአለሁ የሚል ትክክለኛፓርቲ በሚከተሉት መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ
ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ይኖረዋል ተብሎ ስለሚታሰብ አስተባባሪ ግብረ ኃይሉ በቀጣይነት የሚደረጉ ሰላማዊ ትግሎች እነዚህንና ሌሎችንም
ጥያቄዎች ያማከሉ እንዲሆኑ ማድረግ ይችላል የሚል እምነት አለኝ:: በሌላ አባባል
የሰላማዊ ትግሉ ዓላማ የኢትዮጵያውያንን መብትና ነጻነት ማምጣትና ሁሉንም በአንድነት አቅፋ የምትሄድ ፍጹም ዲሞክራሲያዊት አገር
መገንባት ነው:: ይህን ዓላማ ለማሳካት ቀጥለው የተዘረዘሩትንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ማንሳትና
ለነሱም አጥጋቢ መልስ ማግኘት ወሳኝነት አለው::
- ህገ መንግስቱን የሚጻረሩ ህጎች መመሪያዎችና ደንቦች ይሻሩ
- ነጻና ገለልተኛ የፍትህ ሥርዓት ይቋቋም
- ምርጫ ቦርድ ከመንግስት ተጽእኖ ይላቀቅ
- ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ሽብርተኛነት አይደለም መንግስታዊ ሽብርነት ይቁም
- ፓርቲዎች በነጻ የመሰብሰብና ሰልፍ የመውጣት መብታቸው ይጠበቅ
- የፖለቲካ እስረኞች ያለቅድመ ሁኔታ ይፈቱ
- መንግስት በሃይማኖት ተቋማት የሚያደርገውን ጫና ያቁም
- በሙስና የተጨማለቁ ባለሥልጣናት ለፍርድ ይቅረቡ
- የመከላከያ ፖሊስና ደኅንነት መስሪያ ቤቶች ብሄራዊ ተዋጽኦ ይኑራቸው
- ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ይደረግ
- የሽግግር መንግስት ተመስርቶ ትክክለኛና ነጻ ምርጫ ይካሄድ ወዘተ
የትግል ስልቶች
ለመነሻ ያህል ወይም ለምሳሌ ይሆን ዘንድ አስተባባሪ ግብረ ኃይሉ ቀጥለው የተዘረዘሩትን የትግል ስልቶች ደረጃ በደረጃ ሥራ ላይ ሊያውል ይችላል::
- ጥርት ያለ የትግል ቅደም ተከተልና ስልት በጋራ መንደፍ: ፕሮግራሙንም በተለያዩ ቋንቋዎች ማዘጋጀትና ለህዝብና ለፓርቲ አባላት ማሳወቅ
- የትግሉን መጀመር ለማብሰርና ቆራጥነት ያለው አስተባባሪ ግብረ ኃይል እንተመሰረተ ለማሳየት ህዝብን ሳይጨምር የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ሥራ አመራሮች ሥራ አስፈጻሚዎችና ሌሎች የፓርቲዎች የቢሮ ሠራተኞች ያሉበት ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ ማካሄድ: በሰልፉ ላይ እያንዳንዱ ፓርቲ አርማውንና በጋራ የሚዘጋጁትን መፈክሮች መያዝ
- መንግስት በሰልፉ ወቅት የሚጠየቁትን ጥያቄዎች በተመለከተ መልስ የሚሰጥበት የተወሰነ ጊዜ ገደብ ማስቀመጥ
- ሰልፉን በቪዲዮ ቀርጾ በማህበራዊ ሚዲያዎች መልቀቅ በጽሁፍም ማዘጋጀትና መበተን
- መንግስት በተሰጠው ጊዚ ውስጥ አጥጋቢ መልስ ካልሰጠ በዋና ዋና ከተሞች (ለምሳሌ በአዲስ አበባ: በናዝሬት: በአዋሳ: በጅማ: በዲላ: በነቀምት: በደሴ: በባህር ዳር: በጎንደር: በመቀሌ: በደብረ ማርቆስ: በአሰላ: በሐረር: በድሬዳዋ: በሰመራ: በጋምቤላ: በአሶሳ: ወዘተ) ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ በአንድ ቀን ውስጥ ማካሄድና የሰልፉን የአቋም መግለጫ ለመንግስት በጽሁፍ መስጠት: አጥጋቢ መልስ መንግስት በተወሰ ጊዜ ውስጥ እንዲሰጥ ማሳሰብ
- መንግስት በተሰጠው ጊዚ ውስጥ አጥጋቢ መልስ ካልሰጠ በግብረ ኃይሉ አማካኝነት በጥንቃቄ በሚመረጡ ጥቂት ከገዥው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ባላቸው ተቋማት ላይ ብሄራዊ ማእቀብ መጣል: ማእቀቡ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ቀድሞ መወሰንና መንግስት በዚያ ጊዜ ውስጥ መልስ እንዲሰጥ ማስገደድ
- መንግስት በተሰጠው ጊዚ ውስጥ አጥጋቢ መልስ ካልሰጠ ህዝቡ በአስተባባሪ ግብረ ኃይሉ በዝርዝር የሚቀርቡትን ሁሉንም ንብረትነታቸው የገዥው ፓርቲ የሆኑ ድርጅቶች (ባንኮችን ጨምሮ) ላይ ማእቀብ መጣል
- አሁንም መንግስት ለህዝብ ጥያቄ መልስ የማይሰጥ ከሆነ በመላ ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ያመረረ ሰልፍ ማድረግ: መንግስት ጥያቄዎችን እንዲመልስ ዳግም ማሳሰብ
- አጥጋቢ ምላሽ ከመንግስት እስኪገኝ ድረስ እንደአስፈላጊነቱ ስልትን እየቀያየሩ (ለምሳሌ ካድሬዎችንና ባለሥልጣናትን ከማህበራዊ ህይወት ማግለል: መንግስት በሚጠራቸው ስብሰባዎች አለመገኘት ወይም ተገኝቶ ጆሮንና አፍን መዝጋት: ተቀማጭ ገንዘብን ከባንክ ማውጣት: በጭቆና ምክንያት ለታሰሩት ለተደበደቡት ለተሰደዱት ለጠፉት በህብረት ሻማ ማብራት: ሥራቸውን ለህዝብ ማቅረብና ለውይይት ማብቃት: የተቀናጀ ሥራ ማቆም አድማ ማድረግ: ትግሉን በሁሉም የአገሪቱ ክፍል መቀጠል…
- የስለላ ሥራ በመንግስት ባለሥልጣናትና በካድሬዎች ላይ ማካሄድና መጥፎ ሥራቸውን በተለያዩ መንገዶች ለህዝብ ይፋ ማድረግ
- በእውነት ላይ የተመሰረተ የፕሮፓጋንዳ ሥራ መስራት: የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ህዝብን በመረጃ ማንቃት
- ለመንግስት የሚላኩ ውሳኔዎችን የአቋም መግለጫዎችን እንዲሁም ሥራ ላይ ያሉ የትግል ስልቶችን ለዲፕሎማቶችና በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በየዕለቱ ማሳወቅ
ማጠቃለያ
ይህ ሁሉ ሲደረግ መንግስት ዝም ብሎ አይቀመጥም:: ከአስተባባሪ ግብረ ኃይሉ እየቀደመ የማስታገሻና የማርከሻ እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚችል ግልጽ ነው:: በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል
ልዩነት እንዲኖር ያደርጋል:: የትግሉን አስተባባሪዎች ሊያስር
ሊያንገላታ ይችላል:: ህዝቡንም ሊያስፈራራና ሊደበድብ
ሊያስርም ይችላል:: ይህ ሁሉ ሊመጣ እንዳለው ቀደም
ብሎ መገመትና መስዋእት ለመክፈል መዘጋጀት ያስፈልጋል:: ለውጥ ባጭር ጊዜም ሊመጣ ስለማይችል የተለያዩ ስልቶችን
በቀጣይነት መጠቀም ወሳኝ ነው:: ህዝብን የማንቃትና የማረጋጋት
ሥራ ግን የሁል ጊዜ ተግባር ሊሆን ይገባል:: ምናልባት መንግስት በሚያስወስደው የኃይል እርምጃ በመነሳሳት ህዝቡ ኃይል እንዳይጠቀም በግልጽ መናገር ያስፈልጋል:: እንዲያውም ሰላማዊ ሰልፎች
በሚካሄዱበት ጊዜ ከህዝቡ ውስጥ ሥርዓት አስከባሪዎችን መምረጥና ማሰማራት ይጠቅማል:: ምናልባት መንግስት የሰልፍ ፈቃድ ባይሰጥ በህገ መንግስቱ መሰረት የሚፈለገውን ሰዓት ያህል ቀድሞ መንገርና ሰልፉን በእምቢተኝነት
ማካሄድ ግድ ይላል:: ህገ መንግስቱ ላይ የተጠቀሰው
ሰልፍ የማድረግ መብት የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ ከሚከለክል የባለሥልጣን ትእዛዝ የላቀ ነውና:: በዚህ ሁኔታ ለሚከሰት ማንኛውም
ችግር ተጠያቂው ሰልፉን የሚከለክለው አካል ወይም መንግስት ብቻ ነው:: ህግን መሰረት ያደረገ በይዘቱ የተለያዬና ቀጣይነት ያለው ህዝባዊ እምቢተኝነት የሚፈለገውን ፍትህ ሰላም ነጻነትና እኩልነት ያመጣ ዘንድ የታመነ
ነው::
No comments:
Post a Comment