Wednesday, 1 August 2018

የቅዱስ ሲኖዶስ አንድነት ታወጀ!


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 2ኛው ዙር የሰላምና የአንድነት ጉባኤ 24 አባላት ያሉት ጠቅላላ ጉባኤ 12 አባላት ያሉት ሥራ አሥፈፃሚ አባላትና 6 አባላት ያሉት ጽ/ቤት አዋቅሮ የቅዱስ ሲኖዶስን አንድነት ለማምጣት ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ጥሯል፡፡ ዓላማውን ለማሳካት በሰሜን አሜሪካ፤ በአውሮፓና በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትና ምእመናን ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ የእግዚአብር ፈቃድ ሆኖ ሁለቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሶች አንድነት እንደመሰረቱ ለ2ኛው ዙር የሰላምና የአንድነት ጉባኤ አባላት ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ/ም ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው ምተን ኢን ሂልተን ሆቴል ተበሰረ፡፡

ሂደቱን ለማስታወስ ያህል ዋና ዋና ክስተቶች እንዲህ ተዘርዝረዋል፡፡
  •  ሐሙስ ሐምሌ 12 ቀን  6ቱ የሁለቱ ሲኖዶሶች ልዑካን አበውና የ2ኛው ዙር የሰላምና የአንድነት ጉባኤ አባላት ዋሺንግተን ዲሲ ገቡ 
  •  ዓርብ ሐምሌ 13 ቀን የሰላምና የአንድነት ጉባኤ አባላት ያዘጋጇቸውን ሰነዶች መመርመር  ማሻሻል ቀጠሉ 
  •  ቅዳሜ ሐምሌ 14 ቀን ብፁዕን አባቶችና የሰላምና የአንድነት ጉባኤ አባላት በሰነዶች ላይ ውይይት ቀጠሉ 
  • እሑድ ሐምሌ 15 ቀን ጠዋት የጉባኤው አባላት በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በመሄድ ቅዳሴ አስቀደሱ 
  • እሑድ ሐምሌ 15 ቀን ከሰዓት በኋላ የጉባኤው መክፈቻ ጸሎት በደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተካሄደ 
  • ሰኞ ሐምሌ 16 ቀን ጠዋት ብፁዕን አባቶች ለሰላምና ለአንድነት ጉባኤ አባላት የምስራች አበሰሩ አባቶች በራሳቸው ተነሳሽነት እንደተስማሙ የአቋም መግለጫም እንዳዘጋጁ እሱንም ከሰዓት በኋላ እንደሚያቀርቡ አሳወቁ   
  • ሰኞ ሐምሌ 16 ቀን ከሰዓት በኋላ ብፁዕን አባቶች ያዘጋጁትን የአቋም መግለጫ ለሰላምና  ለአንድነት ጉባኤ አባላት አነበቡ ታላቅ ደስታም ሆነ 
  • ሐሙስ ሐምሌ 19 ቀን ጠዋት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባሉበት በወተር ጌት ሆቴል ዜናው ሚዲያና እንግዶች ባሉበት በይፋ ታወጀ 
  • ሐሙስ ሐምሌ 19 ቀን ከሰዓት በኋላ በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በዋሺንግተን ዲሲና በዙሪያዋ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት በተገኙበት ታላቅ የምስጋና ጉባኤ ተደረገ
  •  ቅዳሜ ሐምሌ 21 ቀን ጠዋት ዶክተር ዐቢይ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስና ከሊቃነ ዻዻሳት ጋር ውይይት አደረጉ በመጨረሻም ፓትርያርኩና ሊቃነ ዻዻሳቱ እንዲሁም የሰላምና የአንድነት ጉባኤ አባላት ከዶክተር ዐቢይ ጋር አብረው ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ተወሰነ 
  • ረቡዕ ሐምሌ 25 ቀን ቅዱስ ፓትርያርኩና ሊቃነ ዻዻሳቱ እንዲሁም የሰላምና የአንድነት ጉባኤ አባላት አዲስ አበባ ገቡ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው    
ትዮጵያ ያለውን ሲኖዶስ ወክለው የተደራደሩ
  • ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ
  • ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
  • ብፁዕ አቡነ አብርሐም
አሜሪካ ያለውን ሲኖዶስ ወክለው የተደራደሩ
  • ብፁዕ አቡነ ኤልያስ
  • ብፁዕ አቡነ ሚካኤል
  • ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ
ከ2ኛው ዙር የሰላምና የአንድነት ጉባኤ የተገኙ
  • መልአከ ሕይወት ሐረገ ወይን ብርሃኑ ሰብሳቢ ከካናዳ
  • ሊቀ  ኃይላት ፍሬሰው ገድሌ ምክትል ሰብሳቢ ከአሜሪካ
  • ቀሲስ ዶክተር መዝገቡ ካሳ ጸሐፊ ከኢትዮዽያ
  • መልአከ ሕይወት ቀሲስ ጌጡ የኋላሸት ከስዊድን
  • መልአከ መዊ ልሳነ ወርቅ ውቤ ከጀርመን
  • መልአከ መንክራት አንዷለም ይርዳው ከአሜሪካ 
  • መልአከ አሚን ፋሲል አስረስ ከአሜሪካ
  • መልአከ ምህረት ኃይለ ገብርኤል ይትባረክ ከካናዳ
  • ዲያቆን ማንያዘዋል አበበ ከኔዘርላንድ
  • ጄኔራል ሰለሞን በየነ ከኢትዮጵያ
  • ዶክተር ንጉሡ ለገሰ ከስዊትዘርላንድ
  • ዶክተር አብርሐም ከኢትዮጵያ
  • ዶክተር ተክሉ አባተ ከኖርዌይ
  • ኢንጅነር አሰፋ አበባው ከአሜሪካ 
  • አቶ አበበ እንግዳሰው ከካናዳ
  • አቶ አቤል አድማሱ ከካናዳ
  • አቶ አምሃ ወልዴ ከኢትዮጵያ
  • አቶ ዳግም ታደሰ ከአሜሪካ
  • አቶ ብርቃዬሁ መቀጫ ከእንግሊዝ
  • አቶ ብርሃን ተድላ ከኢትዮጵያ 
የቅዱስ ሲኖዶስ አንድነት የታወጀበት የብፁዕን ሊቃነ ዻጳሳቱ የአቋም መግለ
 ይህ ነው!
 +++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ “አሜን”  
”የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ፤ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው “ 2ኛ ቆሮ 11 ፡ 28
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካዮች የተሰጠ የጋራ አቋም መግለጫ

ጥንታዊት፤ ብሔራዊት፤ ሐዋርያዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ የሆኑ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ማለትም እምነትን፤ አንድነትን፤ ፍቅርን፤ ሰላምን፤ሥነ ጥበብን፤ኢትዮጵያዊነትን፤ታሪክን፤ባሕልንና ቋንቋን ለትውልድ ሁሉ ያበረከተችና በማበርከት ላይ የምትገኝ እና እንዲሁም ለሀገራችን ኢትዮጵያ ባለውለታ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን መሆኗ ይታወቃል።

ቤተ ክርስቲያናችን ለኢትዮጵያ ካበረከተቻቸው አስተዋጽዖ መካከል ፦
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ከመጀመሩ አስቀድሞ ትምህርት ሚኒስቴር ሆና ስታገለግል መቆየቷ ፤  አገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትኮራበትና የራሷ መታወቂያ የሚሆናት ፊደል ቀርጻ ማስረከቧ ፣ የፍልስፍና ፤ የቁጥር፤ የህክምና ጥበቦች መሠረት መሆኗ ፤የዓለም ቱሪስቶችን ትኩረት የሚስቡ በቁጥር የማይወሰኑ ቅርሶችን ይዛ መገኘቷ  እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ ። 

በጠቅላላው ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ለመረዳት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ታሪክ ማወቅ አስፈለጊ መሆኑ የሚያነጋግር አይደለም ፡፡ ይህንም የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ወይም ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ያዩ የሀገር ጎብኝዎችና የታሪክ ጸሐፊዎችም በስፋት በታሪክ ዘግበውት ይገኛል። ዛሬ በዋናነት የሚታወቁ በአውሮፓውያን እና በየትኛውም ዓለም ቤተ ሙዝየም እና ቤተ መጻሕፍት ጎልተው የሚገኙት የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ቅርሶች መሆናቸውን ሁላችንም የምናውቀው ሐቅ ነው።

በዓለም ላይ  ስሟ ደምቆ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአባቶች መለያየት ምክንያት በገጠማት ፈተና ለሁለት ተከፍላ በመቆየቷ ሊቃውንቷ አዝነዋል ፤ ምዕመናን ግራ ተጋብተዋል ፤ የቀደመ ክብሯን አጥታለች ፣ ልጆቿ ተበታትነዋል፤ እንዲሁም ባለውለታ በመሆኗ በልዩ ልዩ እምነት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንም አዝነዋል።

ላለፉት 44 ዓመታት በተፈጠረው  የሐሳብ ልዩነት፤ የፖለቲካ ቀውስና የአባቶች አንድ አለመሆን መብቷን፤ልዑዓላዊነቷን፤ ክብሯን፤ ነጻነቷንና አንድነቷን በተፈጠረው አሳዛኝ ሁኔታ እንድታጣ ብትሆንም  እየወደቀችና እየተነሣች በፈቃደ እግዚአብሔር ከዚህ ከዘመናችን ደርሳለች። በመሆኑም የሰላም እና የፍቅር አስተማሪ የሆነች ቤተ ክርስቲያናችን ከደረሰባት ፈተና መውጣት እንድትችል በተለያየ ጊዜ የሰላም ጥረት ሲደረግ ቢቆይም ሳይሳካ ቆይቷል ፤ ስለሆነም የተፈጠረው የረጅም ጊዜ ችግር ዘመን ተሻጋሪ እንዳይሆን እና ለትውልድ እንዳይተላለፍ ስለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ እና የተሰጠ አደራ መሆኑን የሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶስ እምነት በመሆኑ ችግሩ እንዲፈታ ልዑካን ሰይሟል።

በነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም  የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ በእርሷም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ” ትንቢተ ኤርምያስ 6 ፡ 16 በማለት እንደተናገረው ቤተ ክርስቲያናችን ወደ ቀደመ አንድነቷ እንድትመለስ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ በወሰነው መሠረት ከሁለቱም ሲኖዶሶች የተወከሉ አባቶች ጉዳዩን በጥልቀት ተነጋግረውበታል። ከዚህም በመነሳት ከአለፈው በመማር የሚመጣውንም ዘመን አሻግሮ በማየት ለተተኪው ትውልድም ዳግም መለያየትና ችግር የማይፈጠርበትን መሠርታዊ ሥራ  ሠርቶ ማለፍ  ግዴታ መሆኑን በማመን የሚከተሉትን የጋራ አቋም መግለጫ  አውጥቷል

1. ስለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ

በሀገራችን ኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም. በተፈጠረው የመንግሥት ለውጥ የተነሣ አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለሁለት ተከፍላ በሁለት ፓትርያርኮች የሚመሩ አንድ ሲኖዶስ ለሁለት ሲኖዶሶች መፈጠራቸው ግልጽ ነው። በዚህም የተነሣ አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በስደት ዓለም መቆየታቸው ይታወቃል። ስለሆነም የሁለቱን ቅዱሳን ፓትርያርኮች ቀጣይ ሁኔታ በተመለከተ በሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶሶች የተወከሉት የሰላም ልዑካን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም በአደረጉት የጋራ ስብሰባ በሰፊው ከተወያዩ በኋላ እንደሚከተለው በአንድ ድምጽ ወስነዋል። 

ሀ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ  በፓትያርክነት ክብርና ደረጃ ወደ ቅድስት አገር ኢትዮጵያ  እንዲመለሱ /እንዲገቡ፤

ለ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገር ቤት ኢትዮጵያ ሲመለሱ በክብር የሚያርፉበትን የመኖሪያ ቦታ በተመለከተ ደረጃውን የጠበቀ በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ ውስጥ ቦታ ተዘጋጅቶና የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶ  በክብር እንዲቀመጡ፤

ሐ/ የሥራ አፈጻጽምን በተመለከተ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጸሎት እና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤

        1.1/ ስለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤
ሀ/ በሕገ ቤተ ክርቲያን መሠረት የአስተዳድር ሥራውን በመሥራት ቅድስት ቤተ ክርስቲንን እንዲመሩ፤

ለ/   ጸሎት እና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤

1.2/ የሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርክ አባቶቻችን ስም በቅደም ተከተል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  በአለችበት ዓለም ሁሉ ዘወትር በጸሎት እንዲነሣ፤

1.3/ ሁለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በሕይወተ ሥጋ እስከ አሉ ድረስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በእኩልነት የአባትነት ክብራቸውን ጠብቃ እንድትይዝ፤

1.4/ይህ ስምምነት ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ የአገር ቤትና የውጭ አገር ሲኖዶስ የሚለው ስም ቀርቶ አንዲት ቤተ ክርስቲያንና አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንዲሆን፤

2. ስለ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት 

 ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት የተነሳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ ወድቃለች። ይህም ይታወቅ ዘንድ ሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት እንደ ተፈጸመ  በልዑካኑ ታምኖብታል። ስለሆነም ለአለፉት ዘመናት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መብትና ክብር በመጠበቅና በማስጠበቅ በውጭም ሆነ በውስጥ በአገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ኃላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉና ከጊዜው ጋር አብሮ በመሄዱ ስለተፈጸመው ጥፋትና ለዘመናት በቤተ ክርስቲያኒቱ መለያየት የተነሣ በጥልቅ ኃዘን ልባችው የተሰበረውን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልጆች ያለፉትንም ሆነ ዛሬ ላይ ያሉትን  በጋራ ይቅርታ እንዲጠይቅ የልዑካኑ ጉባዔ በአንድ ድምጽ ተስማምቶ ወስኖአል።

 ስለሆነም ከሁለቱም ሲኖዶስ ውህደት በኋላ ያለፈው የቀኖና ጥሰት ስህተት ለወደፊቱ እንዳይደገም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ሉዓላዊነት ተጠብቆና ጸንቶ እንዲኖር ለማድረግ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት ያደረገ  ደንብ በቅዱስ  ሲኖዶስ  ምልዐተ ጉባዔ እንዲዘጋጅ  የልዑካኑ ጉባዔ በአንድ ድምጽ ተስማምቶ ወስኖአል።

3. ስለነባር ሊቃነ ጳጳሳት

 ከልዩነት በፊት የተሾሙ ነባር ሊቃነ ጳጳሳትን በተመለከተ በሁለቱ ሲኖዶስ የተላለፈው ቃለ ውግዘት በጋራ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተፈቶ ስማቸውና ክብራቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ቤት በሀገረ ስብከት እንዲመደቡና እንዲያገለግሉ ጉባኤው  በአንድ ድምጽ ተስማምቶአል።

4.  ከልዩነት በኋላ  ስለተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት 

 ከልዩነት በኋላ በሁለቱም ወገኖች የተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳትን፤ ጳጳሳትንና ኤጲስቆጶሳትን በተመለከተ ፦ ስማቸውን እንደያዙ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀበላቸውና በውጭ ዓለምም ሆነ በሀገር ቤት በሀገረ ስብከት ተመድበው እንዲያገለግሉ ጉባዔው በአንድ  ድምጽ ተስማምቶአል። ስም አጠራራቸውንም አስመልክቶ እንደ ሹመት ቅደም ተከተላቸው ቀዳማይ፤ካልዓይ፤ሣልሳይ... ወዘተ እየተባሉ እንዲጠሩ ጉባዔው  በአንድ ድምጽ  ወስኖአል።

5. ስለቃለ ውግዘት

 በተፈጠረው ችግር ምክንያት በሁለቱም ሲኖዶስ ቃለ ውግዘት እንደ ተላለፈ ይታወቃል። ስለሆነም ከዚህ ስምምነት በኋላ ቃለ ውግዘቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንዲነሣ  የሰላም ልዑካኑ በአንድ ድምጽ ወስኖአል።

6. በውጭ ዓለም በስደት የምትገኘውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓላማ ያገናዘበ መዋቅራዊ አስተዳድርን ስለማዘጋጀት

 እንደሚታወቀው በዘመናችን በየትኛውም ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ በአሉበት ሁሉ ተስፋፍታ ትገኛለች። ይሁን እንጂ በውጭ ዓለም የምትገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእናት ቤተ ክርስቲያን ጋር አንድነቷን፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንና ክብሯን ጠብቃ መኖር እንዳለባት ጉባዔው አምኖበታል።

ስለሆነም የየሀገሩን ሕገ መንግሥት መሠረት ያደረገ የቃለ አዋዲውና የሕገ ቤተ ክርስቲያን ገዥነት የሚረጋገጥበት  መመሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያዘጋጅ ልዑካኑ በአንድ ድምጽ ወስኗል። እንዲሁም በውጭ ዓለም የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና በመዋቅራዊ አስተዳድር መሠረት ከአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ በመቀበል በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንድትመራም ወስኖአል።

በተጨማሪም በሁለቱ ሲኖዶስ መካከል የተደረገውን የዕርቀ ሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግና የሁለቱንም ሲኖዶስ ውሕደት ፍጹም ለማድረግ እንዲሁም በስደት የሚገኙ ብፁዓን አባቶች ወደ እናት አገራቸው ተመልሰው፥ የቀደመውን ሰላምና አንድነት አጽንተው፥ ሁሉም በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚተዳደሩበትን ቅድመ ሁኔታ የሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ልዑካን እንዲያዘጋጁና እንዲከታተሉ የሁለቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ልዑክ በአንድ ድምጽ ወስኗል።

በመጨረሻም አገራችን ኢትዮጵያ በዘመናችን በደረሰባት ፈተና የከፋ አደጋ ይደርስባታል በሚል በብዙዎች ሲነገር የቆየ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ለብዙዎች ሥጋት የነበረውን የአገራችን ሁኔታ በገዳማት አድባራት እና በኢትዮጵያውያ ህዝብ ጸሎት ባልተጠበቀ መልኩ ወደ ሰላም እንዲቀየር እያደረጉ ያሉ ክቡር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ምኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ልዩነቷን ፈትታ አንድ እንድትሆን ላደረጉት ጥረትና ለሰጡን ድጋፍ በቅድስት ቤተ ክርስቲያንችን ስም ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባለን ።ከዚህም ጋር የሥራ ዘመናቸው ሁሉ የሰላም የፍቅር የአንድነት የእድገትና የብልጽኛ እንዲሆንላቸው የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡

ቤተ ክርስትያን በአንድነቷና በነጻነቷ ተክብራ ስላምና ፍቅርን ለልጆቿ አጎናጽፋና ተጎናጽፋ ስሟንንና ታሪኳን ጠብቃ እንድትኖር በራስ ተነሣሽነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉትን በሀገራችን በኢትዮጵያና በልዩ ልዩ ዓለማት የሚገኙትን ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በአቀራራቢነትና በአደራዳሪነት ያገለገሉትን የኮምቴ አባላት የሁለቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ልዑካን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም ምስጋና ያቀርርባል።

እግዚአብሔር አገራችን ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ ም

++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++ 

ይህን እንድናይ ላደረገ አምላክ ምስጋና እናቀርባለን!   


ከሰላምና አንድነት ጉባኤ አባላት መካከል 




የጉባኤው አባላት በቅዱስ መርቆሪወስ ቤት 


ሁለቱን ሲኖዶሶች ወክለው የተወያዩ ብፁዕን አባቶች 


ከሰላምና አንድነት ጉባኤ አባላት መካከል


ከሰላምና አንድነት ጉባኤ አባላት መካከል


የምስራቹ ዜና እንደተሰማ የጉባኤው አባላት የተነሱት ፎቶ 

ወተር ጌት ሆቴል መግቢያ የጉባኤው አባላት የተነሱት 

ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባሉበት በወተር ጌት ሆቴል የጉባኤው አባላት የተነሱት 


ብፁዕን አባቶች በቅዱስ ሚካእኤል ቤተ ክርስቲያን በተደረገው የምስጋና ዝግጅት ላይ 










No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...