Friday 14 March 2014

ብአዴንንም ጠበቅ!

              
ኢሕአዴግን እንደመሰረቱ ከሚነገረው አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ኢትዮጵያን በአንደኛ ደረጃ የጎዳ ወይም ያዳከመ የትኛው ነው ብለው ያስባሉ? ለምን? ለዚህ ጥያቄ ወጥ የሆነ መልስ ሊኖር አይችል ይሆናል:: እያንዳንዳችን ያለን አስተሳሰብና ፍልስፍና ሊለያይ ይችላልና:: ነገር ግን በመረጃ ተኮር የአስተሳሰብ ብሂል የሚጓዝ ማንኛውም ሰው ሊሰጠው የሚችለው መልስ ሊመሳሰል ይችላል:: ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ያለውን የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ መክተት ለምንሰጠው መልስ ጥሩ መነሻ ይሆናል::


ለእኔ ኢትዮጵያን በአንደኛ ደረጃ ክፉኛ ያንገላታትና እያንገላታት ያለ ፓርቲ ህወኃት ነው:: ከመመስረቻው ጊዚ ጀምሮ በያዘው ጸረ-ኢትዮጵያዊ አቋም የተነሳ ለቍጥር የሚያዳግቱ ታሪካዊ ጥፋቶች ተፈጽመዋል:: ህዝቡን የማይወክሉ ፓርቲዎችን በመፍጠር በህዝብና በመንግስት መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት አጥፍቷል:: በተድበሰበሰ ሪፈረንደም ኤርትራን አስገንጥሏል:: የሙያ ማኅበራትን ክፉኛ አዳክሟል:: የመናገርና የመጻፍ መብቶችን ደምስሷል:: የተቃወሙትን አሳዷል አስሯል ገድሏል አንገት አስደፍቷል:: በደህንነት ቢሮው አማካኝነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የካድሬ ማምረቻ እንዲሆኑ አድርጓል:: የምርጫ ድምጾችን ሰርቋል አሰርቋል:: ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲነሳ ይታትራል ወዘተረፈ:: 

                                           ምስል ከኢሕአዴግ ድረ ገጽ የተወሰደ

ብአዴን ደግሞ የአማራውን ብሄረሰብ ወክያለሁ ለእሱም መብትና ጥቅም ቆሜአለሁ እያለ የሚለፍፍ ፓርቲ ነው:: ዳሩ ግን ይህ ድርጅት ቆሜለታለሁ ለሚለው ህዝብ ምን እየሰራለት ነው? በውኑ ለእድገቱ ምን ያህል ይጥራል? ሰብአዊ መብቱንስ ምን ያህል ያከብርለታል ያስከብርለታል? መልሱ አሁንም ከሰው ሰው ሊለያይ ይችላል:: ፓርቲውን የሚደግፍ ሰው ቀና መልስ ይኖረዋል:: ለእኔ ግን ብአዴን ለአማራው የቆመ ሳይሆን በአማራው ላይ የቆመ ድርጅት ነው:: አማራ ተብሎ የሚጠራ ሰው ሁሉ አንገቱን ደፍቶ ክብሩን ተገፎ እንዲኖር ሌት ከቀን የሚሰራ ታታሪ ድርጅት ነው:: በምስኪኑ ገበሬ ገንዘብ ምድር ላይ ለመሪዎቹ ገነትን የፈጠረ ለህዝቡ ግን ምድርን ሲዖል ያደረገ ድርጅት ነው:: መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከህወኃት ቀጥሎ የተጎዳውና የተዋረደው በብአዴን ነው::     
             


                                           ምስል ከኢሕአዴግ ድረ ገጽ የተወሰደ

የዚህን ድምዳሜ እውነታነት ለማረጋገጥ የብአዴን መሪዎች በተለያዪ ጊዜያት ያቀረቧቸውን ንግግሮች መስማትና የተዋዋሏቸውን ውሎች መቃኘቱ ከበቂ በላይ ነው:: የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒትር መለስ ዜናዊ የአቅም ማነስ ችግር አለበት ብሎ የተሳለቀበት የአቅም ግንባታ ሚኒስትር የነበረው አቶ ተፈራ ዋልዋ አንድ ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት አማራው በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ የጫነው እዳ እንደሆነ ተናግሯል:: በሙስና ስም ከሥልጣኑ ተወግዶ እስር ቤት ለበርካታ ዓመታት የማቀቀው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ አማራው ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ተጠርጎ መውጣት እንዳለበት ተናግሯል:: የቀድሞው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ በረከት ስምዖን ገበሬው ተኛ ሲሉት እንደሚተኛ ሂድ ሲሉት እንደሚሄድ ደረቱን ነፍቶ ተናግሯል:: በቅርቡ ደግሞ የአማራው ክልል ምክትል ሊቀመንበርና የብአዴን ጸሐፊ አቶ አለምነው መኮንን አማራው በባዶ እግሩ እየሄደ መርዝ የሚተፋ ክፉ ፍጡር እንደሆነ እልህ እየተናነቀው ተናግሯል::   

ርግጥ እነዚህ ንግግሮች የተናጋሪ ግለሰቦቹን እንጅ የፓርቲውን አቋም አይገልጹም የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል:: ለእኔ ግን እነዚህ ንግግሮች የፓርቲውን አቋም ያንጸባርቃሉ:: አንደኛ እነዚህ ባለሥልጣናት እነዚህን ንግግሮች ያቀረቧቸው በመንግስትና በፓርቲ ሥራ ላይ ሳሉ እንጅ በግል ከጓደኞቻቸው ወይም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው አይደለም:: መንግስትና ፓርቲው ያስተባበሯቸው ህዝብ የተገኘባቸው መድረኮች ላይ የተነገሩ ናቸው:: ሁለተኛ ድርጅቱም ሆነ መንግስት እነዚህን ክፉ ንግግሮች በተመለከተ ማስተባበያ ወይም ማስተካከያ አለመስጠቱ ወይም ይቅርታ አለመጠየቁ በሃሳብ ደረጃ እንደሚደግፋቸው ያመላክታል:: ሦስተኛ አቶ አለምነው መኮንን የተናገረው የፓርቲውን አቋም እንደሆነ ራሱ በግልጽ ተናግሯል::         

በዚህም ብአዴን ከሌሎች አቻ ድርጅቶቹ በጣም ይለያል:: ኦህዴድ ደኢህዴንና ህወኃት መሪዎቻቸውን በሙስናና በሌላ እኩይ ምግባር ይከሳሉ እንጅ ለስምም ቢሆን ቆሜልሃለሁ የሚሉትን ህዝብ በአደባባይ አያዋርዱም:: ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ አላዋረደም:: እንዲያውም የተገፋና የተጨቆነ ህዝብ እንደሆነ  ይናገርለታል:: ኦነግ የሚል ታርጋ በመለጠፍ ተቀናቃኞቹን ግን ያዋክባል:: ህወኃትም የትግራይ ህዝብ ምርጥ ዘር እንደሆነ አብዝቶ ይመሰክርለታል:: ደኢህዴንም ቢሆን የትኛው ብሄረሰብ ሥልጣን እንደሚይዝ ይዶልታል እንጅ የደቡብ ህዝቦችን በአደባባይ አያዋርድም:: የእነዚህ ሦስት ድርጅት ባለሥልጣናት ለንዋይና  ለሥልጣን ይገዳደራሉ እንጅ ቆመንለታል ለሚሉት ህዝብ በአደባባይ ውርደትን አያስጎነጩትም:: ብአዴን ግን ከአምባገነናዊ አገዛዝና ሙስና በተጨማሪ የአማራውን ህዝብ በይፋ በአደባባይ ያዋርዳል:: አማራው ሌላውን ኢትዮጵያዊ እንደሚጠየፍና እንደሚንቅ ብአዴን ደጋግሞ ተናግሯል:: ይህም ሌሎች ብሄረሰቦች በእርሱ ላይ እንዲነሳሱ ከመቀስቀስ አይተናነስም::

ይህ ጉዳይ በቀላሉ መታለፍ የለበትም:: ፓርቲው ለሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ተጠያቂና ኃላፊ መሆን አለበት:: ፓርቲው እስካሁን ድረስ ያደረጋቸውን ህዝብን የሚያንቋሽሹ ንግግሮችና ፕሮፓጋንዳዎች በማሰብ ይፋዊ ይቅርታ መጠየቅ አለበት:: በተጨማሪም የአማራውን ተወላጅ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የሚያቀራርቡ ፕሮግራሞች ተነድፈው በቋሚነት መካሄድ አለባቸው::

ይህ የማይደረግ ከሆነ ግን ህዝቡ ራሱ ርምጃ  የሚወስድበት ጊዜ ይኖራል:: የተቃዎሚው ጎራም ይህንን እንደትልቅ አጀንዳ መያዝ አለበት.: ማንኛውም ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ትግል ህወኃትን ብቻ ሳይሆን ብአዴንንም ትኩረት ውስጥ ማስገባት አለበት:: ሁሉንም ግፍና ጭቆና የሚፈጽመው ህወኃት ነው ብሎ ማሰብ ችግራችንን በዘላቂነት ላለመፍታት እንደቆረጥን አመላካች ነው:: ከህወኃት በተጨማሪ ብአዴንንም ጠበቅ አርጎ መያዝ አስፈላጊና ወቅታዊ ነው::


 ህዝብ ይከበር!

No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...