Friday 17 October 2014

ፓትርያርክ ብፁዕ አባ ማትያስና ተግዳሮቶቻቸው

ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ከተሾሙ እነሆ ሁለት ዓመት ሊሞላቸው አራት ወራት ገደማ ይቀራቸዋል:: ቅድመና ድኅረ ሹመታቸውን ተከትሎ የውይይትና የክርክር መድረኮች በኢትዮጵያም በውጭውም ዓለም ተከፍተው ነበር:: የአምስተኛው ፓትርያርክ የብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ድንገተኛ ሞት አንዳች ለውጥ ለቤተ ክርስቲያኗ ያመጣ ይሆናል ብለው የገመቱና የተመኙ ብዙዎች ነበሩ:: ሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ ሊያወርዱ እንደሚችሉ ተተነተነ:: ዳሩ ግን የእርቁ ሂደት ሳያልቅ ምርጫ ተደረገና ብፁዕ አቡነ ማትያስ በወሳኝ ድምጽ እንዳሸነፉ ተነገረ:: በዚህም የመንግስት ጫናና ማስፈራራት እንደነበረበት ተወሳ:: እርሳቸውም ነጭ ልብስ እንደማይለብሱና የቅንጦት ኑሮ እንደሚጸየፉ: ቤተ ክርስቲያን ያጣችውን ክብርና ተሰሚነት እንደሚመልሱ ተናገሩ:: «ይህን ማን አየው» በሚል ተስፋ አዲሱ ፓትርያርክ የለውጥ ሐዋርያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቅር እያላቸውም ቢሆን የገመቱ ነበሩ::



የጎላ ነገር ሳይሰራ እነሆ ሁለተኛ በዓለ ሲመታቸውን ሊያከብሩ ነው:: ከቀድሞው ፓትርያርክ ጋር አንጻራዊ በሆነ መልኩ ሲወዳደሩ አቡነ ማትያስ ብዙም የመድረክ ሰው አይመስሉም:: በተለያዩ ጉባዔያትና መገኛ ብዙሃንም የአቡነ ጳውሎስን ያህል ጎልተው አልወጡም:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ድምጻቸውና ያሉበት ሁኔታ እየተሰማ የመጣ ይመስላል:: በሆነ ወቅት ላይ በመንግስት ካድሬዎች ለሰዓታት እንደታሰሩና እንግልትም እንደደረሰባቸው ሲነገር ነበር (ይህ እውነት መሆኑን ያጣራ አካል ግን የለም):: የእስራታቸው ዜና ከተሰማ ጀምሮ ግን በንግግራቸው ጠንከር ያሉና የፖለቲካ ቃና ያላቸው አቋሞችን ማስተላለፍ የጀመሩ ይመስላል:: በተለይ ከመስከረም ወር 2007 የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ ጠንከር ያሉ ጉዳዮችን ጠንከር ባሉ አነጋገሮች ማቅረብ ጀምረዋል::  


                                              ብፁዕ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ

የብፁዕነታቸውን የአመራር ክህሎቶችና ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ቅርብ ጊዜ በተደረጉና በመደረግ ላይ ባሉ የቤተ ክርስቲያኗ ጉባዔያት ላይ ፓትርያርኩ ያቀረቧቸው ንግግሮች ዋና የመረጃ ምንጭ ናቸው:: አንደኛው መስከረም ፳፯ ቀን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ፣ መስከረም ፳፱ ቀን ደግሞ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ  የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሃፊዎች የታደሙበት ጉባዔ ነው:: የዚህ ጉባዔ መሪ ቃል ‹‹በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመልካም አስተዳደር አስተሳሰብን ማበልጸግ›› የሚል ሲሆነ ብፁዕነታቸው የመክፈቻ ንግግር በጽሁፍ አቅርበዋል:: ይህ ጽሁፍ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ድረ ገጽ http://eotcssd.org/the-news/398--q-q-.html  ላይ ይገኛል:: ሁለተኛው የመረጃ ምንጭ ደግሞ ጥቅምት ቀን ፳፻፯ .. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብሰባ አዳራሽ በተጀመረው ፴፫ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ ፓትርያርኩ የተናገሩት ነው:: ይህም በማደራጃ መምሪያው ድረ ገጽ http://eotcssd.org/the-news/399-sebeka2007.html ላይ ይገኛል:: ከነዚህ ንግግሮች ቢያንስ ቀጥለው ያሉትን ጉዳዮች መረዳት ይቻላል::      
    

ከቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አስተዳደር አካላት ጋር አለመናበብ

የአምስተኛው ፓትርያርክ አንዱና ትልቁ ችግራቸው በየደረጃው ካሉ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር አካላት ጋር ተናቦ: ተቻችሎና ተስማምቶ አለመስራት ነበር:: የስብሰባ አጀንዳ ከመምረጥ ጀምሮ ውሳኔዎችን እስከማሳለፍና እስከማስፈጸም ባሉ ሂደቶች ቅዱስ ሲኖዶስን ይገዳደሩት ነበር:: በሚያሳድሩት ቀጥታዊና ሥልታዊ ጫና ሲኖዶሱ ጥርስ የሌለው አንበሳ  መስሎ እስከመታየት ደርሶ ነበር:: እንደምንም ተብሎ  የተላለፉ ውሳኔዎች ሳይፈጸሙ የራሳቸው ህይወት ተፈጸመ::

ስድስተኛውም ፓትርያርክ ገና ከጠዋቱ «ብቸኛ ሆኛለሁ» ማለት ጀምረዋል:: እርሳቸው ብቻቸውን እንደሆኑና ሃሳባቸውን የሚሰማ የበላይ አካል እንደሌለ በመረዳታቸው በአጥቢያ ደረጃ ካሉ አለቃዎች ጋር «ዝቅ» ብለው መወያየት እንዳስገደዳቸው በመስከረሙ ጉባዔ አሳውቀዋል:: በንግግራቸውም የደብርና የገዳማት አለቆች ከጎናቸው እንዲቆሙ ተማጽነዋል:: በአጥቢያ ደረጃ ካሉ አመራሮች ጋር መወያየቱ በራሱ ችግር የለውም:: ችግሩ የበላዩ አመራሮች ወይም ቅዱስ ሲኖዶስ በሥራቸው እንዳልተባበራቸው በስሞታ መልክ ለበታች አካላት መቅረቡ ነው:: ይህ ጉዳይ በተለያዩ እርከኖች ያሉ የቤተ ክርስቲያኗ አካላት ላይ አላስፈላጊ ጥርጣሬ ከመፍጥሩም በላይ ሥራን ይበድላል:: ይህንንም በተመለከተ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አሥኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የሰጡት መልስ ተጠቃሽ ነው:: ፓትርያርኩ የጠሩት ስብሰባ ግልጽነት የጎደለውና ወቅታዊ ጉዳዮችንም የተመለከተ እንዳልሆነ ብፁዕነታቸው ተናግረዋል:: እንግዲህ ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅናና ይሁንታ ውጭ የሚደረግ ስብሰባና የሚተላለፍ ውሳኔ እንዴት ውጤት ይኖረዋል?  በአምስተኛው ፓትርያርክ ዘመን ቅዱስ ሲኖዶስ ያጣውን የመወሰንና የማስፈጸም አቅም ከማራዘም ውጭ ሌላ ምን ፋይዳ አለው? ይህ ተናቦ አለመስራት የቤተ ክርስቲያኗን ሰላምና አንድነት ይፈታተናል:: ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገው የአንድ ሰው ወይም አካል ገናናነትን ሳይሆን ተስማምቶና ተቻችሎ ከሁሉም አካላት ጋር መስራትን ነውና ብፁዕነታቸው ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በክብር እንዲሰሩ ክርስትናው ያስገድዳል::  

ወሳኝ የሆኑትን ጉዳዮች ትቶ በጥቃቅን ነገሮች ላይ ማተኮር

ፓትርያርኩ መስከረም ፳፯ ቀን ጉባዔውን ሲከፍቱ ቀጥለው የተዘረዘሩትን አንገብጋቢ የሆኑ የቤተ ክርስቲያኗን ችግሮችን ዘርዝረዋል
v  የምእመናን በቁጥር መቀነስ
v  የቤተ ክርስቲያን ሃብት መቀነስና አብያተ ክርስቲያናት መዘጋት
v  የቤተ ክርስቲያን እሴቶች ለኢትዮጵያ የሚያበረክቱት ጠቀሜታ መቀነስ
v  መዋቅር ዘርግተው ለራሳቸው ጥቅም የሚሯሯጡ ሃላፊዎች መበራከት
v  ከቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እጅግ የላቀ መንፈሳዊ ተግባር መጥፋት
v  በቤተ ክርስቲያን ስም የሚደራጁ ማኅበራትና ግለሰቦች መዋቅርን አለመከተል
v  ማኅበራትና ግለሰቦች ንብረት ማፍራት ላይ መጠመድና አባቶችን መከፋፈል  

በእውነቱ ከሆነ እነዚህ ጉዳዮች እጅግ አሳሳቢዎች ናቸው.: ቶሎ መፍትሄ ካልተሰጣቸው ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር የተጣለባትን አደራ በተገቢው መጠን ልትወጣ አትችልም:: ዳሩ ግን ከጊዜና ከአቅም ውሱንነት የተነሳ እንዲሁም ከመረጃና ማስረጃ እጥረት የተነሳ ሁሉም ችግሮች በአንድ ጊዜ እኩል ትኩረት አያገኙም:: ለአጀንዳዎች ቅደም ተከተል ሰጥቶ መወያየት የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው:: አስተዋይና አዋቂ መሪ የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው:: ጥሩ መሪ ሁሉንም ችግሮች የሚፈታ ማለት ሳይሆን ወሳኝና አንገብጋቢ የሆኑትን ለይቶ በማውጣት መፍትሄ የሚሰጥ ማለት ነው:: ፓትርያርኩ ችግሮችን ቢዘረዝሩም ካለው ጊዜ አንጻር ትኩረት ሊሰጧቸው የሚገቡ ጉዳዮች መለየት ነበረባቸው:: የምእመናን ቁጥር መቀነስና የአብያተ ክርስቲያናት መዘጋት እንዲሁም የሙስና መስፋፋት ከማኅበራት ጥቃቅን ችግሮች ጋር እንዴት እኩል ይታያል?

የሚገርመው ግን ረጅም ጊዜ የወሰዱ ጠንካራ ንግግሮች የተካሄዱት ከማኅበራትም በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ብቻ ነበር:: የተወሰኑ የደብር አለቆች (አብዛኛው ችግር ከነሱ ሥራ ጋር እንደሚያያዝ ስላወቁ) የተወረወረውን ጦር አቅጣጫ ቀየሩለት:: ፓትርያርኩም ጉባዔው በማስተዋልና በመንፈሳዊነት መወያየት እንደሚያስፈልግ ከማሳሰብ ይልቅ ለጀሮ በሚሰቀጥጡ ስድብ ነክ ንግግሮች የተደሰቱ መስለው ታይተዋል:: መሪ የሌለው ስብሰባ ሆኖ የተነሳበትን «አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ማበልጸግ» መሪ ቃል ሳይመራበት ቀረ:: የአቋም መግለጫ የወጣው ቤተ ክርስቲያኒቷን እያንገላታት ስላለው ስለሙስናና አድሎአዊ አሠራር ወይም ስለምእመናን መባዘንና አብያተ ክርስቲያናት መዘጋት ሳይሆን ስለአንድ ማኅበር ሃብታም መሆን ነው:: በመሆኑም የእለቱ ጉባዔ መነሻውና መድረሻው ያልተጣጣሙ ሆነው ቀርቷል:: ይህም ከአመራር ብቃት ማነስ ወይም ከልዩ ዓላማ መኖር ጋር ሊያያዝ ይችላል:: ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉባዔያት የሚጠሩትና የሚመሩት እንዲህ ከሆነ እጅግ አሳዛኝና ፈታኝም ነው:: ብፁዕነታቸው ትልቁን ጉዳይ ከትንሹ ለይተው ካላወያዩና ከሚመለካተቸው አካላት ጋር አብረው ካልሰሩ የራሳቸውን ወይም የሌሎችን አካላት ፍላጎት ከመከተል የሚያግዳቸው አይኖርም::

ስሜትን መሠረት ያደረጉ ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮች

ንዴትን: ብስጭትን: ቅሬታን: ተስፋ መቁረጥን: ድካምን: ደስታን ወይም ስኬትን መነሻ  ያደረገ ንግግር ሁሉ ስሜታዊ ነው:: አይደለም በመንፈሳዊ ህይወት በዓለማዊ አሠራርም ስሜታዊነት ጥቅም የለውም:: ጥሩ መሪ ማለትም ስሜትን ተቆጣጥሮ ሠራተኞችን ወይም አገልጋዮችን በማስተባበር ዓላማን ማሳካት የሚችል ነው:: ቅዱስ ፓትርያርኩ በልምድ ማጣትም ሆነ በብሶት ወይም በሌላ ምክንያት ስሜትን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ንግግሮችን ከላይ በተጠቀሱት ታላላቅ ጉባዔያት ደጋግመው ተናግረዋል:: ለምሳሌ ያህል ቀጥለው የተዘረዘሩት የፓትርያርኩ ንግግሮች አብይ ናቸው
v  የሚሰማኝ ስላጣሁ ከበታች የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ጋር መወያየት አስፈለገኝ ወደፊትም ዓመቱን ሙሉ አደርገዋለሁ
v  ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ቅኝ ገዥ ነው የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ሃብት ቀምቷል
v  ይህ ማኅበር በቁጥጥር ሥር እንዲውል አሳስባለሁ
v   እኔ ይኽን ጉዳይ ከራሴ አወርዳለኹ፤ የቤተ ክርስቲያናችን ገንዘቧ፣ ክብሯ ተወስዷል 
v  ቤተ ክርስቲያን ከቅኝ ተገዥነት ትውጣ፤ ካህናቱ ከመከራ ይውጡ
v  ይህችን ቤተ ክርስቲያን ለመጠበቅ፤ አንዷን ቅድስት፣ ኦርቶዶክሳዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን ልመራ እንጂ ኹለት ቤተ ክርስቲያን የለችም
v  እኔ ብቻዬን የምሠራው ነገር የለም፤ በዚኽ መግለጫ እንድትሠሩበት ነው የምነግራችኹ
v  በህግና በሥርዓት የማይመራ ማኅበር አሸባሪ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው
v  አባ ማትያስ አላበደም፤ መልእክቴን እያስተላለፍኹ ነው ያለኹት፤ መልእክቴን በጸጋ ተቀበሉ ብዬ እማፀናችኋለኹ

እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ነገር ቢኖር ከዚህ በላይ ለተጠቀሱት ከባድ ንግግሮች የቀረበ መረጃም ሆነ ማስረጃ አለመኖሩ ነው:: እንዴትና በምን ሁኔታና ምክንያት ነው ጠቅላይ ቤተ ክህነትና ቅዱስ ሲኖዶስ የፓትርያርኩን ሃሳብ የማይጋሩ? ማኅበሩስ የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ሃብት የቀማው እንዴት ነው? ካህናትንስ እንዴትና በምን ሥልጣን ነው በገዥነት የያዛቸው? ለነዚህና ለሌሎችም ትችቶች መረጃም ሆነ ማስረጃ አልቀረበባቸውም:: ይህ ሆኖ ሳለ እንዴት ተደርጎ ነው የፓትርያርኩ ፍላጎት የሚፈጸመው? «ሃሳቤን በጸጋ ተቀበሉት» ማለታቸውም መረጃና ማስረጃ እንደሌላቸው ጠቋሚ ነው:: አሳማኝ መረጃና ማስረጃ ካለ መለማመጥም ሆነ መለመን አያስፈልግም:: ሁሉም አካል ለእውነት ተገዥ መሆን አለበትና:: የቀረቡት ንግግሮች መሠረታቸው በውል ባይታወቅም ከስሜት ግን የጸዱ አይደሉም:: ስሜት ደግሞ አይደለም ለፓትርያርክ  ለተራ ክርስቲያንም የተመቸ ወይም የሚጠበቅ አይደለም:: ስሜት የጎበኛቸው ንግግሮች የሰውን እንጅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስለማያስቀድሙ በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች መካከል ክፍፍልን ያመጣሉ:: እልህን ከዚያም ቂምን ከዚያም መጠቃቃትን ይጋብዛሉና::  

ማጠቃለያ

ከንግግራቸው እንደምንረዳው ብፁዕ አቡነ ማትያስ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር መልካም ግንኙነት እንደሌላቸውና በዚህም የተነሳ መንፈሳቸው እንደተረበሸ ነው:: በዚህ ሁኔታ ያለ መሪ አይደለም አዲስ ውጤት ሊያመጣ ያለውን ሊንድ ይችላል:: ብፁዕነታቸው በተመረጡበት ወቅት ቤተ ክርስቲያኒቷ ያጣችውን ክብርና አንድነት እንዲሁም ተሰሚነት ለመመለስ ከሁሉም አካላት ጋር እንደሚሰሩ ቃል ገብተው ነበር:: ይህ ግን እስካሁን ሲደረግ ወይም ለመደረግ ሲሞከር አልታየም:: ይባስ ብሎ ጉባዔያት መረጃና ማስረጃ የሌላቸው ተራ ሊባሉ የሚችሉ ክሶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ:: ከጥቂት ታዳሚዎች በስተቀር አብዛኞቹ ግራ ከመጋባትና ከመለያየት ባለፈ እየቀረቡ ባሉ ንግግሮች ተጠቃሚዎች ሊሆኑ አይችሉም:: ይህም የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልግሎት በእጅጉ ይጎዳል::

ይቅር የማይሉና እርቅን የማያውቁ ባለሥልጣናት እንዴት ወንጌልን ሊሰብኩ ይችላሉ? ያጠፋ አካል ካለ ጥፋቱ በተጨባጭ ተነግሮት ይመከራል: አስተዳደራዊ ርምጃ ይወሰዳል እንጅ በመድረክ የስድብ ናዳ ይወረድበታል? የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዴት ይካሄድበታል? ከላይ ያሉት አባቶች በእንደዚህ ያሉ ነገሮች የሚጠመዱ ከሆነ ምእመናን ማንን አርአያ ሊያደርጉ ይችላሉ??? ምናልባትም የምእመናን ቁጥር መቀነስ አንዱና ትልቁ ምክንያት ይህ የበላይ አካላት አላስፈላጊ ግብግብ ይመስለኛል:: ብፁዕነታቸው ለራሳቸውና ለንግግራቸው ይበልጥ በመጠንቀቅ የአባትነት ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል:: የይቅርታ: የእርቅ: የአንድነትና የሰላም አርአያ ሆነው መቀጠል ይጠበቅባቸዋል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን የሚፈልጉት ፍጹም መንፈሳዊ አባት እንጅ በሥልጣኑና በኃይሉ የሚመካና የሚያስፈራራ መሪ አይደለም::        



9 comments:

  1. Kale hiwot yasemalin!!!!

    ReplyDelete
  2. He did the same thing in DC when he split from the main Medhanialem church. He went and set up a Tigrian Medhanialem church. This is was his record and he was elected to this position becaue his is from the "golden" people.

    ReplyDelete
  3. Prey prey prey. This is the last day. zemene LibineDingil yidegrmal YeEgziabher Esat ametsegnawun tibelalegn. Beqa beqa beqa

    ReplyDelete
  4. Geta hoy ayinachew ena libachew betikim ena bekifat temoltoalena asteway lib sitachew.

    ReplyDelete
  5. ቃለ ሂወት ያሰማልን !!! ጥያቄ ለቅዱስ አባታችን ቢደርሶዎትም ባይደርሶዎትም ቀኝ ገዢ ማነው ?ከአባ ጳውሎ ዘመነ ፕትርክና ጀምሮ በዘር ተሰግስገው እንደ ኮሦ ቤተክርስቲያንን ከተጣቧት እና ከሚበዘብዟት ዘረኞች እንዲሁም በማያገባቸው እየገቡ ቤተክርስቲያንን ከሚያውኳት የመንግስት ባለሥልጣናት ናቸው ? ወይስ የወደቁና የተረሱ ገዳማትንና አድባራትን የሚደግፍ ወጣቱንና አዲሱን ትውልድ ዕምነቱን እዲየውቅና ታሪኩን እንዲረዳ የሚያደርግ ማህበር ነው የቤተክርስቲያኗ ቀኝ ገዢ ?

    ReplyDelete
  6. ጎበዝ ዝም ብሎ ፓትርያርኩ ላይ ብቻ መዓት ከማውረድ ለምን እንዲህ አሉ እንኳን ብሎ ለመፈተሽ የደፈረ የለም።ምክንያቱም አብዛኛው ምዕመን ከቤተክርስቲያን በፊት የማህበር አምላኪ ስለሆነ ነው። ቅኝ ግዛት ይሉሀል ይሄ ነው። ለመፍረድ እኮ ቢያንስ የሁለቱንም ወገን ማየት ያስፈልጋል።ማህበሩ የሰራቸው ጥሩ ስራዎች እንዳሉ ሁሉ ስህተቶችም ይኖሩታል።ለምን ተናገሩኝ ብሎ ቡራ ከረዩ ከማለት ቆም ብሎ ራስን መፈተሽ ደግሞ መንፈሳዊነት ነውነሰ

    ReplyDelete
  7. mahiberun kebetekeresetian netelo mayet malet yebetekeresetianen menenet alemawok new.

    ReplyDelete
  8. kfu neger kemenager mastewal melkam new tselotm madreg alebn degmo hulum erasun lemastekakel tekerarbo menegager alebet.eng metekuakor melkam aymeslegnm...mahiberum tru neger eyesera new gn keabatachin gar bekrb menegager alebachu....beterefe zm blen abatoch lay yemaygeba neger banitsif melkam new...mnm bhon abatachn nachhu...e/r krstina hymanotachnn ytebkln....amen

    ReplyDelete
  9. https://fb.watch/fmKvWVYySV/

    ReplyDelete

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...