Saturday 16 April 2016

ማኅበረ ቅዱሳንና አራቱ ፈታኞች ክፍል 2

ክፍል 1 ጽሑፌ ስለማኅበረ ቅዱሳን (ማቅ) መጻፍ ለምን እንዳስፈለገ ማኅበሩን እንዴት እንዳወቅኩትና ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ የማኅበሩን አመሰራረትና ዓላማ በጥቂቱ አቅርቤያለሁ በዚህ ክፍል ደግሞ ማቅን አብዝተው የሚፈትኑ አካላት እነማን እንደሆኑ በደረጃ ከነምክንያቶቻቸው አቀርባለሁ ይህ ጽሑፍ በክፍል 1 እንደተጠቀሰው ማቅንም ሆነ ሌላ አካልን ለመቃወምም ሆነ ለመደገፍ የተዘጋጀ አይደለም ያሉ እውነታዎችን ከግል እይታዬ በመነሳት በትንተና መልክ ለአንባቢ ማስገንዘብ እንጅበዚህ ጽሑፍ ምክንያት ሊነሱ የሚችሉ ውይይቶችና ሙግቶች በመጨረሻ የተሻለ ግንዛቤ እንዲመጣ ያደርጋሉ ብዬ አምናለሁ። ለጽሑፎቼ እንደ ግብዓት ያገለገሉኝ የግል ተሞክሮዬ የማቅ ገጸ ድርና እትሞች እንዲሁም ስለማቅ በተለያዩ ሚዲያዎች የተነሱ ዘገባዎች ናቸው    

አራቱ ፈታኞች  

ማቅ ከምስረታው ጀምሮ ከተለያዩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ አካላት የተለያየ ግምት ወይም ተቀብሎ አለው   ማቅ በተለያዩ  አካላት ምን አይነት ግምት እንደሚሰጠው ለመጠቆምና ፈታኞችን ለምን አራት እንዳደረስኳቸው ለማሳየት ያህል እነዚህን አካላት ደጋፊዎች ተቃዋሚዎች ገለልተኞች ተቃደጋፊዎችና ፈታኞች ወይም አሳዳጆች ብዬ ከፋፍያቸዋለሁ እነዚህ አካላት ለማቅ ያላቸውን ግንዛቤና ግምት በተመለከተ እንደሚከተለው ባጭር ባጭሩ ለመግለጽ ሞክሬያለሁ  

ደጋፊዎች

ደጋፊዎች ማቅ በቤተ ክርስቲያን ስር ታቅፎ ወጣቶችና ምሁራን ሃይማኖታቸውን ከነትውፊቱ ጠንቅቀው አውቀው ለትውልድ እንዲያስተላልፉ የሚጥር ማኅበር እንደሆነ በማመን ሙሉ ድጋፋቸውን ይሰጣሉ። ከቤተ ክህነት ቀጥሎ ለቤተ ክርስቲያን አለሁ ባይ አካል እንደሆነ ያምናሉ። ባጠቃላይ ደጋፊዎች ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ከፍዘትና ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል በሚደረግ ጥረት ማቅ ልዩ ቦታ እንዳለው ስለሚያምኑ በሞራል፣ በዕውቀት፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በተቻለው ሁሉ ይራዳሉ። የማቅን ደካማ ጎን ሲያገኙ በመምከርና በመገሰጽ ለማስተካከል ይጥራሉ።

በዚህ ስር ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ሰንበት ትምህርት ቤቶች (በተለይ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ካየለበት ጊዜ ጀምሮ)፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት እንዲሁም የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ዘመናዊ ትምህርት የተማረውና የሰው ሕይወት እንጅ የሃይማኖት ትምህርት መታደስ የለበትም ብሎ የሚያምነው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ እንዲሁም ሰፊው ህዝብ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ይጠቀሳሉ። ማቅ በውጭው ዓለምም ቀላል የማይባል ደጋፊ አለው  
   

ተቃዋሚዎች

በአንጻሩ ደግሞ ተቃዋሚዎች (የፖለቲካ ተቃዋሚዎች አላልኩም!) የማቅን ዓላማ በይፋ ባይቃወሙም በማቅ የአሠራር ሂደት ላይ በመመርኮዝ አብዝተው ይቃወማሉ ማቅ የሚሠራውን ማናቸውንም ሥራ ማብጠልጠልና ውድቅ ማድረግ ይቀናቸዋልበመሆኑም የማቅ አባላትን ለማየትም ከነሱም ጋር መሆንን አብዝተው አይወድዱምማቅን ለምን አምርረው እንደሚጠሉና እንደሚቃወሙ ሲጠየቁ በአብዛኛው የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች ማቲያሲያዊ ይመስላሉ  ማለትም ብፁዕ ፓትርያርክ አባ ማቲያስ ሁሌ የሚያቀርቧቸው «ማቅ ከቤተ ክርስቲያን በላይ ገዘፈ፣ በሁሉ ረገድ ቤተ ክርስቲያን አነሰች ማቅ አየለ፣ ማቅ  ሀብታም ሆነ፣ ማቅ ገንዘቡን ለቤተ ክርስቲያን አያስገባም» ወዘተ የሚሉ ናቸው

ባጠቃላይ ተቃዎሚዎች ማቅን ከነፍሳቸው ቢጠሉትም ማኅበሩን ለማጥፋት ግን በእቅድና በስልት አይንቀሳቀሱም። ንዴታቸውና ቅናታቸው በተቃውሟቸው ይበርድላቸዋል። በዚህ ስር ኢትዮጵያም ሆነ ውጭ አገር የሚኖሩ ግለሰቦች፣ አንዳንድ የቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ አንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎችና የመንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደሮች ሊጠቀሱ ይችላሉ ተቃዋሚዎች ብዛታቸው ከደጋፊዎች ቢያንስም  ልዩ ልዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ሌሎች ሰዎችን ለጊዜውም ቢሆን በማደራጀት አቧራ ማስነሳት ይችላሉ! ችለውም ነበር  

      

 ገለልተኞች

በደጋፊዎችና በተቃዋሚዎች መካከል ገለልተኞች ይገኛሉገለልተኞች በማቅና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ተስተጋብሮት በደንብ አይረዱም። ቢረዱትም እንኳን ሁኔታዎችን ገምግመው ሀሳብ ወይም ፍርድ ለመስጠት ይቸገራሉ። ስለማቅ ውይይት ሲነሳ እንደማይም ለመሆን ይጥራሉ። ገለልተኛ ሆኖ መታየት ብልህነት ስለሚመስላቸውና ሰላም እንደሚሰጣቸው ራሳቸውን ስላሳመኑ በጉዳዮች ላይ «ጀሮ  ዳባ ልበስ ብለው ይኖራሉ። አስተያየት እንዲሰጡ በግልጽ ሲጋበዙ «ይቅርታ እኔ ስለጉዳዩ ብዙ አላውቅም! በቡድንም በማኅበርም በሚደረጉ ውይይቶች አላምንም! ለኔ ቤተ ክርስቲያኔ ብቻ ትበቃኛለች!» አይነት መልስ ይሰጣሉ። ገለልተኞች «ማቅን በሩቁ ቢሉም ማኅበሩን ለማጥፋት ወይም ለማዳከም ግን ፍላጎት የላቸውም። በዚህ ስር ቀላል የማይባሉ የሃይማኖት ማኅበራትና የሲቪክ ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች ይጠቃለላሉ።

ተቃደጋፊዎች

ሁሉም ባይባልም በውጭው ዓለም በተለይም በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያዊያንንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በአባልነት ያቀፉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ግብረ ኃይሎችና የድጋፍ ኮሚቴዎች ለማቅ ያላቸው ግምት ለየት ይላል እነዚህን አካላት ተቃደጋፊዎች ብያቸዋለሁ! ተቃዋሚም ደጋፊም ናቸውና። ማቅ የኢትዮጵያን ታሪክ ያለምንም ፍርሃትና ስጋት ለወጣቱ በማስተማሩ፣ ማቅ በብሄረሰብ ሳይሆን በብሄራዊ ደረጃ በመዋቀሩ፣ ማቅ በልዩ ልዩ አገልግሎቶቹ ኢትዮጵያዊነትን እንጅ ዘውግን ባለማንጸባረቁ፣ ማቅ በቤተ ክርስቲያንና በአገር ዙሪያ ያለውን ሙስናና አስተዳደራዊ ዝርክርክነትን በመቃወሙ፣ በነዚህና  በሌሎችም ጉዳዮች ማቅ ለመንግስት የራስ ምታት በመሆኑ ወዘተ እነዚህ አካላት በይፋ ለመደገፍ የሞራል ብቃት ቢያጥራቸውም በልባቸው ያመሰግናሉ የማቅንም ፈጽሞ መጥፋት ወይም መዳከም አይመኙምም።

ይሁን እንጅ ማቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የመንግስት አገልጋይ እንደሆነ የሚነገረውን ቅዱስ ሲኖዶስ ደግፎ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር አብሮ እንደሆነ የሚነገረውን ውጭ አገር ያለውን ቅዱስ ሲኖዶስ ባለመቀበሉ፣ መንግስት በሚያደርጋቸው መጠነ ሰፊ ግፎች ማቅ በይፋ ባለመቃወሙ፣ ማቅ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ባለመሥራቱ፣ በውጭ አገር የሚገኙ ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ወደኢትዮጵያው ሲኖዶስ እንዲገቡ ማቅ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ በመነገሩ ወዘተ ማቅን አጥብቀው ይቃወማሉ  በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ያለውን የማቅን እንቅስቃሴም በጥንቃቄ ይከታተላሉ እንዲያውም ማቅ የመንግስት ደጋፊና ዲያስፖራውን ለመከፋፈል የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው ብለው የሚያምኑም አሉ። ይህን የፖለቲካ ትኩሳት በመጠቀም የራሳቸውን የግል ጥላቻ በማኅበሩ ላይ የሚወጣጡም ይገኛሉ  ይህ ሁሉ ቢሆንም ማቅን በተቀናጀ ስልትና እቅድ ለማዳከም ብሎም ለማጥፋት ከሚደረገው ጥረት ጋር ተቃደጋፊዎች አይተባበሩም        

ፈታኞች

ፈታኞች ወይም አሳዳጆች ግን እጅግ የተለዩ አካላት ናቸው። የመጨረሻ ዓላማቸው ማቅን ማጥፋት ያም ካልተቻለ ወገቡን እንደተመታ እባብ ማኅበሩ ሲሽመደመድ ማየት ነው። ይህን ዓላማ ለማሳካት ማንኛውንም አዋጭ መንገድና ስልት ይጠቀማሉ። እንዲሁም በመሠረታዊ ዓላማ ከማይመስሏቸው ሌሎች ተቋማት ጋርም ትብብርና ትስስር ይፈጽማሉ። በተለያዩ ዘዴዎች ማቅን እንደ ጭራቅ ወይም ሰይጣን ስለው ለማሳየት ይሞክራሉ። ጉልበት፣ ውግዘትና ክስ ዋነኞች የተቃውሟቸው መገለጫዎች ናቸው።

እነዚህን አካላት ፈታኝ ብያቸዋለሁ። እንደሚታወቀው ፈተና በመንፈሳዊውም በዓለማዊውም ሕይወት ብዙ አይወደድም። ፈታኙ በተፈታኙ ላይ የበላይነት አለው። ፈተናውን ማቅለል ማክበድም ይችላል። እንደዚህም ሁሉ ማቅን በተለያዩ መንገዶች የሚያስጨንቁ የተለያዩ አካላት ናቸው።

እነዚህ አካላት እነማን ናቸው? ማቅን የሚያስጨንቁባቸው መሠረታዊው ምክንያቶችስ ምንድን ናቸው? ምክንያቶችስ በትክክል የማቅን ችግር ያሳያሉ? በዚህ ማቅን በመፈተኑ ሂደት የሚጎዳው ማቅ ብቻ ይሆን? ለመሆኑ ማቅ ለኢትዮጵያና ለቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ጠቃሚ ነው? ፈተናዎችን ለማለፍስ ከማቅ እንዲሁም ከተለያዩ አካላት ምን ይጠበቃል? ይህ ጽሑፍና ቀጣይ ክፍሎች ለእነዚህ ከባድ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይሞክራሉ።

ፈታኞች እነማን ናቸው?

ማቅን በቋሚነትና በስልት የሚፈትኑ አካላት አያሌ ናቸው ። ዋናዎቹ ግን የተሐድሶ አቀንቃኞችና ደጋፊዎቻቸው፣ የፕሮቴስታንት እምነት ድርጅቶችና ደጋፊዎቻቸው፣ የእስልምና ሃይማኖት ድርጅቶች፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና ጣሊያን፣ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክና ጽ / ቤታቸው፣ ሙዘረኞች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጭ አገር ባለው ቅዱስ ሲኖዶስ ስር ያሉ ካህናትና አገልጋዮች ናቸው።

ማቅ ሲቋቋም ጀምሮ ትልቁ ሥራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ እምነት፣ ቀኖናና ትውፊት ለትውልዱ በማስተማር መጠበቅና ማስጠበቅ ስለሆነ «የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እድሳት ያስፈልገዋል ከሚሉ የተሐድሶ አቀንቃኞችና ደጋፊዎቻቸው ጋር ጭድና እሳት መሆኑ አይገርምም። ተሐድሶዎች ከምእራቡ ዓለም በሚያገኙት ገንዘብ በመታገዝ ለመስፋፋት ጥረት ያደርጋሉ። ማቅ ደግሞ ትውልዱን በማንቃትና መረጃና ማስረጃ ሰብስቦ ለሚመለከተው ክፍል በማቅረብ ፍልሚያውን ቀጥሏል። ተሐድሶዎች ራሳቸው በሚዲያ እንደተናገሩት ከቤተ ክህነት ይልቅ ማቅ የራስ ምታት እንደሆነባቸውና እንቅስቃሴያቸውን በብዙ መንገድ እንደገደበባቸው ያምናሉ። የፕሮቴስታንት እምነት ድርጅቶችና ደጋፊዎቻቸው እንዲሁም የእስልምና ሃይማኖት ድርጅቶች ግልጽ በሆኑ ምክንያቶች ማቅን አምርረው ይጠላሉ።

ጣሊያንና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ማቅን ይጠላሉ። ማቅ በአድዋና በሌሎችም ጦርነቶች ጣሊያንና ቫቲካን ያደረጉትን ግፍ በጥናት አስደግፎ ለህዝብ አቅርቧል። እንዲያውም ጣሊያንና ቫቲካን ኢትዮጵያን ይቅርታ እንዲጠይቁ ካሳም እንዲከፍሉ የሚጠቁሙ መደምደሚያዎችን ሰጥቷል ማቅ ። አንድም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በደቡብና በሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ውስጥ በምታደርገው የመስፋፋት እንቅስቃሴ ማቅን እንደ ተቀናቃኝ ታያለች። ማቅ ከየሀገረ ስብከቶች ጋር በመተባበር በአካባቢው የሚኖሩ አያሌ ኢትዮጵያዊያንን ወደኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት እያመጣ ነውና።  
         
ምንም እንኳን የተሐድሶ አቀንቃኞችና ደጋፊዎቻቸው፣ የፕሮቴስታንት እምነት ድርጅቶችና ደጋፊዎቻቸው፣ የእስልምና ሃይማኖት ድርጅቶች እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና ጣሊያን ለማቅ የዕለት ዕለት ፈተናዎች ቢሆኑም ኅልውናውን የሚያሰጉ ግን አይደሉም። ማቅ በዋናነት እነዚህ አካላት በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሱትን እንግልት ለመከላከል ተቋቁሟልና። እነዚህን አካላት ለመቋቋም ድርጅታዊ ልምድ ዝግጅትና አቅም አለው ቢባል የከበደ ንግግር አይሆንም። ማቅ ይህን ያህል ዘመን ሊቆይ የቻለው እነዚህ አካላት የሚያደርሱበትን ልዩ ልዩ ጫናዎች ተቋቁሞ ነውና

ዳሩ ግን የኢትዮጵያ መንግስት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክና ጽ//ቤታቸው፣ ሙዘረኞች እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጭ አገር ባለው ቅዱስ ሲኖዶስ ስር ያሉ ካህናትና አገልጋዮች ለማቅ ልዩ ፈተናዎች ናቸው። ከሌሎቹ ይልቅ እነዚህ አራት አካላት ማቅን አስጨንቀው ይዘዋል። እነዚህን አካላት በይፋ ለመፋለም የተቋቋመበት ዓላማ ስላልሆነ አስቸጋሪ ነው። ዝም እንዳይልም በኅልውናው መጥተውበታል። ማቅ እስካሁን ድረስ ስልታዊነትን ያገናዘበ አካሄድን በመምረጥ ለመቋቋም ሞክሯል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጥንካሬ ያላቸውን መግለጫዎች በማውጣት ራሱን ከመከላከል ወደ ማጥቃትም መውሰድ እንደሚችል አመላክቷል። ይህ መንገድ የት ያደርሳል ? ለመሆኑ እነዚህ ፈታኝ አካላት እንዴትና ለምንድን ነው ማቅን ለማፈን የፈለጉት?  


ይቀጥላል!  

No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...