Thursday, 26 September 2013

የማታ እንጀራ ይስጥህ!

አገር ቤት ያደገ ወይም የቆየ ሰው ብዙ አባባሎችንና ምርቃኖችን እድሜ ከጠገቡ (እድሜ ካስቆጠሩ) ሰዎች ይሰማል ይማራል:: ከነዚህም ውስጥ የማታ እንጀራ ይስጥህ የሚለው ምርቃት ቀልብን ይስባል:: ገና ነፍስ ሳላውቅ የዚህ አባባል ትርጉም አይገባኝም ነበር:: ትርጉሙን የመጠየቅም እድሉና አቅሙ አልነበረኝም:: ነገር ግን በ20ዎቹ የእድሜየ ክልል ሳለሁ አንድ የተባረከ ሰው ትርጉሙን ሲያብራራ ሰማሁት:: ሳልጠይቅ ያገኘሁት መልስ ነበር:: ከዚያ በኋላ ለአባባሉ ልዩ ክብር መስጠት ጀመርኩ:: 

ማክበርም ብቻ ሳይሆን በጎለመስኩና ባረጀሁ ጊዜ ወፈር ያለ እንጀራ እንዲገጥመኝ እመኝ ነበር:: ሌሎች ሰዎችም በማታ ዘመናቸው ዳጎስ ያለ እንጀራ ሲያገኙ ሳይ አባባሉ ህያው ቃል እንደሆነ  እገነዘባለሁ:: በተለይ ታዋቂ ሽማግሌ ሰዎች ይህ እድል ሲገጥማቸው ማየት ልዩ አንደምታ አለው:: እንኳን ሆነላቸው ያሰኛል:: ጉልበቱ የደከመ ጤናው የተጓደለ ሰው ሲሳካለት ማየት የማይፈልግ ማን ይኖራል? 

የሰሞኑ ድንቅ ዜና የሆነው የክቡር ፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ከምኒልክ ቤተ መንግስት መለስ ያለው አኗኗራቸው ነው:: እንደሰማነው ከሆነ  በወር 400, 000 ብር የሚከፈልበት መኖሪያ ባለ ሁለት ፎቅ ቤት መንግስት ተከራይቶላቸዋል:: ለቤቱ አሳንስር (ሊፍት) ለማስገባት 1.6  ሚሊዮን ብር እንደተበጀተም አውቀናል:: ከጥቅምት ወር ጀምሮ በአዲሱ ቤት እንደሚኖሩ ታውቆአል:: ለክቡርነታቸው አገልግሎት የሚውሉ ሶስት እኔ ነኝ ያሉ መኪናዎች ይመደባሉ:: የቤት ሰራተኞች: ሾፌሮችና የደህንነትና የጥበቃ ከተፎዎችም በመንግስት ደመዎዝ ይቀጠራሉ:: የሳቸውና የቤተሰቦቻቸው የህክምናና ተያያዥ ወጭዎች በቸሩ መንግስታችን ይሸፈናሉ:: የማታ እንጀራ ብሎ ዝም!

ፕሬዚደንት ግርማ ወ ጊዮርጊስና አዲሱ ቤታቸው ምንጭ አውራምባ ታይምስ ድረ ገጽ 

ታድያ ምን ይጠበስ? ቡጨቃ ነዋ! ክቡርነታቸው ሃብታም እንደሆኑ ይነገራል:: ለራሳቸው ጥራት ያለው መኖሪያ ይኖራቸዋል:: ይህ እውነት ከሆነ እስኪ ጥያቄዎችን እናንሳ::
 • ሶስት ሚሊዮን ምስኪን ኢትዮጵያውያን የምን ይሉኝታ ብለው መንገድ ላይ ወጥተው የኔ ብጤ የሚል ስም ሰጥተናቸው በስቃይ ይኖራሉ:: ከቤታቸው ሆነው በረሃብ አለንጋ የሚገረፉ ስንት እንደሆኑ ቤት ይቁጠረው:: እዚያው ከአዲሱ የፕሬዚደንት ቤት ዙሪያ ስንት ጦም አዳሪ አለ? ታድያ ፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ይህ ሁሉ ምስኪን ባለበት አገር በወር 400, 000 ብር ለቤት ኪራይ ብቻ እየተከፈላቸው ሲኖሩ ሼም አይዛቸውም? እንቅልፍስ ተኝተው ያድራሉ? 
 • ቤተሰቦቻቸውስ ቢሆኑ ይህንን ጉድ አሜን ብለው ይቀበላሉ? 
 • መንግስትስ ቢሆን በእድገት ከአለም የመጨረሻ ደረጃ ላይ የምትገኝ አገር ይዞ  እንዴት ይህንን ያደርጋል? ቸርነት ሊባል ነው ወይስ  ደንታ ቢስነትና ማን አለብኝነት? 
 • ወይስ ተመጣጣኝ ቪላ ሰርቶ መስጠት ለምን አልተፈለገም? 
 • ህዝብስ ቢሆን ይህን ጉድ ሰምቶ ዝም ሊል ነው? ቢያንስ መስቀል አደባባይን በሰልፍ አያጥለቀልቅም? አምቶ ዝም ሊል ነው? 
 • ማኅበራዊ ድረ ገጾችና ሊሎች ሚዲያዎችስ ጎናዊ ሃሜትብቻ አቅርበው ዝም ሊሉ ነው? ለምን አለም አቀፋዊና የተደራጀ ተቃውሞ አያሰሙም?
 • አለም አቀፉ የእርዳታና የብድር ተቋማትና አገሮችስ ይህን እንዴት ይመለከቱታል?  

ለማንኛውም ፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የማታ እንጀራ አግኝተዋል:: ጥያቄያችን ለምን አገኙ ሳይሆን እንዴት ይህን ያህል ወጭ አገሪቷ እንደትሸፍን ይፈረድባታል? መንግስትስ ቢሆን ይህንን በማድረግ ለዜጎች የሚያስተምረው ምንድን ነው? ሁለትና ከዚያ በላይ ጡረታ የሚወጡ መሪዎች ካሉ ይህን ያህል ለእያንዳንዱ ሊከፈል ነው? የሚል ነው::

ፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ መጥፎ  ምእራፍ ከፋች ሆነዋል:: በዚህ ሁኔታ እሳቸውና መንግስት እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አንገታቸውን ሊደፉ ይገባል:: ተቃዎሚዎችና የመንግስት ደጋፊዎች በአንድነት ሊቆሙበት የሚገባ ጉዳይ ቢኖር ይህ ዋናው ነው:: ማንም ይህንን ራስ የሚያዞር ወጭ የሚደግፍ ቢኖር ከልቡ ወይም ከህሊናው አይደለም:: 

በአንጻሩ ደግሞ  እንደ ፕሬዚደንት ነጋሶ ጊዳዳ ያሉ ጊዜያዊ ጥቅምን ወደጎን ገሸሽ ያደረጉ ዜጎች ሁሌ አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት ሊሄዱ ይገባል:: እውነት እየሰሩ በደሳሳ ጎጆ መኖር ከቤተ መንግስት እንክብካቤ እጅግ ይልቃል:: ለመጭው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ሊወዳደሩ ያሰቡ ሁሉ አቋማቸውን ሊፈትሹ ይገባል:: አላማቸው የማታ እንጀራ ፍለጋ ወይስ አገርን በቀና ህሊና ለማገልገል? ለኔ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ነጻነት የራሱን ፕሬዚደንት የሚመርጥበት ጊዜ በቶሎ  እንዲመጣ ምኞቴ ነው! 

ብኩንነትና ማን አለብኝነት ይብቃ!!!  

  

   

2 comments:

 1. ...ታዲያ ጉዶቹ እኛው አይደለንም ትላላችኍ? እንዴት ያለ ትክሻ ነው ያለን ባካችኍ?!

  ReplyDelete
 2. ዶ/ር ተክሉ ጥያቄው ተገቢ ነው።
  እዚህ ላይ መንግስት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማስታወቂያ ሕዝቡን ቁጠባ! እያለ ሲናገር መታዘብም ተገቢ ነው። ንግድ ባንክ ''ገንዘብ ብታስቀምጡ ዕጣ ሽልማት አለው'' የሚለው የኢቲቪ የየቀኑን ማስታወቂያ አለመርሳትም ታክሎበት።ሙስናው ቅጥ ሲያጣ እና እንዲህ ለኪራይ በዓመት ለፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወደ አምስት ሚልዮን ብር ሲወጣ ''ቁጠባ'' የሚለው ቃል መዝገበ ቃላት ላይ ተቀየረ እንዴ የማይል ማን ነው? ደግሞስ ይህ ብር የማን ነው የእኔ እና ጉልት እየሸጠች የመደብ ክራይ ለመንግስት የምትከፍለው ምስኪን አይደለም እንዴ? ማለትም ሲያንስ ነው።

  ReplyDelete

የሁለቱ ሲኖዶሶች ፈተና

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕወሓት - መሩ መንግስት ከመጣ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመጋፈጥ ላይ ትገኛለች። ኦርቶዶክስንና አማራን በተለየ መልኩ ለማዳከም ከተቻለም ለማጥፋት የትግሉ ዓላማ አድርጎ...