Sunday, 20 October 2013

ጎጂ ባህሎቻችን

ባህል ብዙ ትርጉም ይኖረዋል:: ለእኔ ግን የአንድ ኅብረተሰብ የአስተሳሰብ: የጠባይና: የባህርይ መገለጫ ወይም ምልክት ነው:: በተፈጥሮ (በዘር ውርስ) የማይገኝና በሰው ብርቱ ጥረት የሚፈጠር ስለሆነ እያንዳንዱ አገር የራሱ የሆነ ልዩ ባህል አለው:: ለልጅ ልጅም በትምህርትና በተሞክሮ ያስተላልፋል:: በጊዜ ብዛትና በተለያዩ ብሄራዊ: ክልላዊና: ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች የተነሳ ባህል ሊከለስ ሊዳብር ሊለወጥም ይችላል:: ያም ቢሆን ግን አገራት በባህላቸው ልዩ የሆኑ ናቸው (የዓለም ህዝቦች የሚጋሩትም ባህል እንዳለ ሳንረሳ):: በአጠቃላይ ባህል የኅብረተሰብን ምንነትንና ማንነትን ገላጭ ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም::


ዳሩ ግን ሁሉም ባህሎች ጠቃሚ ወይም ገንቢ ላይሆኑ ይችላሉ:: እንዲያውም በባህል ስም ገዳይ የሆኑ አስተሳሰቦችና ምግባራት ሊስተዋሉ ይችላሉ አሉም:: ለግለሰብ እድገት ጤናና ሰላም እንዲሁም ለአገር መሻሻል ልዩ አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ባህሎች እንዳሉ ሁሉ ባለንበት እንድንሄድ እንዲያውም ባላንስ እንዳጣ መኪና ወደኋላ እንድንሸራተት የሚያደርጉ ባህሎችም አሉ:: እነዚህን ወደፊት እንድንሄድ የማያግዙ ወይም ወደኋላ የሚጎትቱንን ጎጂ ባህሎች ብያቸዋለሁ:: ቆም ብለን ማሰብና መገንዘብ መመርመር ከፈለግንና ከቻልን ጎጂ ባህሎችን መለየት እንችላለን:: እንዲህ ማድረግ ከቻልን ደግሞ  ጠቃሚ ባህል ግንባታ ላይ እናተኩራለን:: ለግል ህይወታችንና ለአገራችንም ጠቀም ያለ ለውጥ ባጭር ጊዜ ማምጣት እንችላለን:: በመሆኑም በዚህና በቀጣይ ጽሁፎች ለኛ ለኢትዮጵያውያን ጎጂ ናቸው ብዬ የማስባቸውን የምንነታችንንና የማንነታችንን መገለጫ የሆኑ ባህሎቻችንን ለመለየት እሞክራለሁ::

ጎጂ ባህል ስል ግን ሁሌ አሰልቺ በሆነ መልኩ በሚዲያ የሚለፈፉትን አይነት ማለቴ አይደለም:: ለእኔ ጎጂ ባህል ግግ ማውጣትን: እንጥል መቁረጥን: የሴት ልጅ ግርዛትን: ያለእድሜ ጋብቻን: ያለአቅም ድግስን: እጅ ሳይታጠቡ መመገብን: ወዘተረፈ አይመለከትም:: ምንም እንኳን እነዚህ ተግባራት ጎጂነታቸው የማያነጋግር ቢሆንም ለእኔ ግን በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ ሆነው አይታዩኝም:: ትኩረቴ የሚሆነው አስተሳሰባችንን ጠባያችንንና ምግባራችንን ማእከል ባደረጉ ደካማ ባህሎቻችን ላይ ነው:: እነዚህ ባህሎች ላለፉት በርካታ ዓሥርት ዓመታት ባለንበት እንድንረግጥ እንዲሁም በአንዳንድ የህይወት ዘርፎች ወደኋላ በፍጥነት እንድንጓዝ ያደረጉን ናቸው ብዬ አምናለሁ:: ለብሄራዊ ድቀታችን ግንባር ቀደም ተጠሪውና ተጠያቂው መንግስት ቢሆንም እንደህጻን ልጅ ተንከባክበን የያዝናቸው አንዳንድ ባህሎቻችንም ቀላል ያልሆነ አስተዋጽዖ አድርገዋል:: በግል ህይወት በቤተሰብ በጎረቤት በጓደኛ በመስሪያ ቤትና በብሄራዊ ደረጃ እንቅስቃሴያችን ጥራትና ዋጋ እንዳይኖረው የሚያደርጉ ብዙ ጎታቾች አሉን::      

በተከታታይ የምዘረዝራቸው ባህሎች በተወሰነ መልኩ ደካማ ጎኖች ተብለውም ለፈረጁ ይችላሉ:: ለእኔ ግን ደካማ ጎን  የግለሰብን ችግር አመላካች ስለሚሆን ቃሉን በዚህ ጽሁፍ እምብዛም አልጠቀመውም:: ጽሁፌን በደንብ እንድትረዱልኝ ግን በቅድሚያ ማሳሰቢያዎቼን ልጥቀስ:: አንድ: በጅምላ የኢትዮጵያ ባህል ገዳይ ወይም ጎጂ ነው እያልኩ አይደለም:: ለቁጥር የሚያዳግቱ የትም አገር የማይገኙ ወርቅ ባህሎች ሞልተውናል:: ለመሻሻል እንዲረዳን በጎጂዎች ላይ ብቻ ማተኮሬ እንጅ:: ሁለት: ቀጥዬ የምጠቅሳቸው ጎጂ ባህሎች ሁሉም ሰው ጋር አሉ የሚባል ባይሆንም ብዙዎቻችን ግን የምንጋራቸው ይመስላሉ:: ለማንኛውም እያንዳንዱ አንባቢ የየትኛው ጎጂ ባህል ሰለባ እንደሆነ ራሱ ይመርምር:: ሥስት: ይህ ጽሁፍ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በተሰበሰበ መረጃና ማስረጃ ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን ከማህበራዊ ሚዲያዎች የተመለከትኩትንና በማህበራዊ ህይወት የታዘብኩትን መሰረት ያደረገ ነው:: አራት: ጎጂባህሎች በፖለቲካው ዘርፍ በሃይማኖት ተቋማት በስራ ቦታ በጓደኝነት ህይወት በቤተሰብ እንዲሁም በትዳር ህይወት ውስጥ እንደልብ ይገኛሉ:: አምስት: ባህል ሊተች የማይችል ቅርስ ነው ወይም እኛ ኢትዮጵያውያን ጎጅ ባህል የለንም ብሎ የሚያምን ሰው ካለ ቆም ብሎ አስተሳሰቡን ይፈትሽ:: ይህ አስተሳሰብ ራሱ የጎጂ ባህሎች ቁንጮ እንደሆነ ይረዳ:: ስድስት: የሚዘረዘሩት ጎጂ ባህሎች አዲስ ናቸው እያልኩም አይደለም:: በአንድም በሌላም መልኩ በተለያዩ ተችዎች ተነስተው ይሆናል:: ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በቀጣይነት መወያየት በእጅጉ ይጠቅማል በሚል እሳቤ ለማቅረብ ወሰንኩ:: ችግሮች እስኪጠፉ ድረስ አብዝቶ መወያየት ጥሩ ነው:: ሰባት: በዚህ ጽሁፍ የሚቀርበው ጎጂ ባህል  ብሄራዊና ፖለቲካዊ አንደምታ ያለው ነው::

  

መሪ-መራሽ የለውጥ ትኩሳት

በብሄራዊ ደረጃ ፖለቲካዊ እምርታ ሳናስመዘግብ የቀረነው በበርካታ እንቅፋቶችና ምክንያቶች ነው:: በእኔ እይታ ግን መሪን ያማከለ እንቅስቃሴ ወይም ትግል በተደጋጋሚ ማድረጋችን ለውድቀታችን ዋና መንስኤ ነው:: መሪዎች ለውጥ እንዲመጣ የማይናቅ ድርሻ ማድረግ እንደሚችሉ የማይካድ ቢሆንም እኛ ግን ከሚገባው መጠን በላይ መሪዎችን እንደአጥቢያ ኮኮብ ያለምንም መጠራጠር ስንከተል በተደጋጋሚ ጉድ ሆነናል:: የመሪዎች መሰደድ ወይም መታሰር ወይም መሞት ድንገት እንደነጋበት ጅብ ክፉኛ አስደንግጦናል:: መሄጃም አሳጥቶናል ልንወድቅም ተፍግምግመናል እየተፍገመገምንም ነው::

ለማስረጃ ያህል ብዙ ማለትይቻላል:: ጃንሆይ እግዚአብሔር የቀባቸው ታላቅ መሪ ናቸው ብሎ ብዙው ሰው ያምን ስለነበር በወቅቱ የተከሰቱ አስተዳደራዊ ችግሮችን ለመፍታት አልተቻለም:: ኢትዮጵያ ማደግ የምትችለው በሳቸው ሥራ ብቻ እንደሆነ ታመነ:: በአጠቃላይ ንጉሡ አንዳች ነገር ሰርተው ለውጥ እንዲያመጡ ለዘመናት ተጠበቀ:: መጨረሻ ላይ በመሪ- ተኮር ለውጥ ባህል መያዝ ያልፈለጉ የወጣቱና የጦሩ ክፍል ተነሳና ሌላ ምዕራፍ ተጀመረ:: በኋላም ጓድ መንግስቱ ለውጥና እድገት እንዲያመጡ ለዘመናት ተመኘን:: መሪው ሲኮበልሉ ጅምሮች ሁሉ እንዲጠፉ ተደረገ:: የኢሕአፓ ትንታግ መሪዎችን በማየት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ተስፋ ተጣለ:: ወጣቱም ንቁ ተሳታፊ ሆነ:: መሪዎቹ ሲሰደዱና ሲታሰሩ እንዲሁም ሲሞቱ የተሰነቀው ተስፋ የማይጨበጥ እንደሆነ ግልጥ ሆነ:: ከዚያም መለስ ዜናዊ አገሪቷን በመዳፋቸው ስር አደረጉ:: በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ (ደጋፊውም ተቃዋሚውም) ለውጥ የሚመጣ ከሆነ በሳቸው ብቻ እንደሆነ አሰበ:: ድንገት ሰውዬው ሲሞቱ ድርጅታቸውም አብሮ ሞተ:: ተከታዮቻቸውና ተቃዋሚዎችም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ባለማወቅ ግራ ተጋቡ:: መሞታቸውንም ለመቀበል የተቸገሩ ደጋፊዎች ነበሩ:: ግን ሁሉም ሰው በብዙ ጎጂ ባህሎች የተጠቃ ስለሆነ ያለተቀናቃኝ መልሰው የፖለቲካውን መዘውር ጨበጡት:: ቅንጅት መንፈስ ነው እስኪባል ድረስ በፍጥነት በህዝብ ልብና ህሊና ውስጥ ገባ:: መሪዎች እንዳልሆነ ሲሆኑ እንደብረት ግሎ የነበረ ትግል እንደ በረዶ ቀዘቀዘ::

የአገር መሪዎችን እንደ ምሳሌ አነሳሁ እንጅ መሪ የማምለክ አባዜ በሁሉም የኑሮ  ደረጃና ዘርፍ ይታያል:: በመስሪያ ቤት አለቆች ብቻ ለውጥ እንዲያመጡ በንቃት እንጠብቃለን:: ሌላው ቀርቶ በሥራ ቦታ የተፈቀደልን መብት ሲጣስ ዝም ብለን እናልፋለን:: ሌላ ሰው እንዲከራከርልን እንጠብቃለን:: ስብሰባ ላይ ከአለቆች የተሻለና የተለየ ሃሳብ እያለን አንናገርም ተከራክረን ጥሩ ውሳኔ እንዲተላለፍ የበኩላችንን አስተዋጽዖ አናደርግም:: 

በጓደኝነትም ችግሩ እንዲሁ ነው:: ብዙ ጊዜ አንዱ በሃሳብ ወይም በሌላ ነገር ከፍ ብሎ ይታያል:: እሱ ያለው ካልሆነ ጓደኝነት ሊሰረዝ የሚችል ኮንትራት ነው:: ሌላኛው ጓደኛ ይህን ስለሚያውቅ የጓደኛው ተለጣፊ ሆኖ ይኖራል:: ሲሳሳትና መጥፎ ሥራ ሲሰራ ለማስተካከል አይጥርም:: የመናገርና በነጻነት የመኖር መብቱን ቀስ በቀስ ለጓደኛው ያስረክባል:: የሚዝናኑባቸው ቦታዎችና ቀኖች እንዲሁም የመወያያ ርዕሶች የሚመረጡት በአንደኛው ወገን ነው:: ሌላኛው ወገን ግን ሳያውቅ የበታችነት ስሜት እየተሰማው ቁጥብነት እያጠቃው ይኖራል:: እንዲህ አይነቱን ሰው ለብሄራዊ ለውጥና ለእድገት ለማሳተፍ አዳጋች ነው እሱን ንቁ ተሳታፊ ከማድረግ እድገት እራሱን ማምጣት ይቀላል:: 

የመሪና የተመሪነት ባህል በትዳርም ውስጥ ልዩ ቦታ አለው:: ባል ወይም ሚስት እንደፈርዖን የሚፈሩበት ቤት ሞልቷል:: ብዙ ጊዜ ባል አምባገነን ነው ይባላል ሊሆን ይችላል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሚስቶች ወሳኝና አደገኛ የሆነ አካሄድ ጀምረዋል:: ለመብታቸው መቆማቸው የሚበረታታ ነው:: ዳሩ ግን የነሱ የበላይነት ደግሞ  አይጣል ነው:: የወንድን ጭቆና በሴት ጭቆና  ለመተካት የሚደረግ ፍልሚያ እንጅ በእኩልነትና በመተሳሰብ የሚደረግ የለውጥ ጉዞ  አይመስልም:: ጨቋኝ ባል  ወይም ሚስት ሆይ የራሳችሁን መብት ለመጠበቅ የሌላውን ሰው መብት ማፈን ያለባችሁ አይመስለኝም:: 

በሃይማኖቱም በኩል ችግሩ ፈርጥሟል:: ቄሱ: ፓስተሩ: ሼኩ: ብለዋልና ፈቅደዋልና እያለ ሰብአዊ መብት ሲረገጥ መንፈሳዊ ህይዎት ሲቀጭጭ  ዝም ብሎ  የሚያየው እኮ በጣም እየበዛ ነው:: ዝምታው ስለበዛ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች እኮ  ምድርን ገነት ሳይሆን ሲዖል እያደረጓት ነው:: ሴቶችን የሚደፍሩና ትዳር የሚበትኑ አሉ:: በሙስናና በዘር ግንድ የተጠመዱ ሞልተዋል:: የሰውን አእምሮ ሃይማኖታዊ በሚመስል ግን ባልሆነ ትምህርት አስንፈዋል:: የለውጥ ማዕበልን አፍነዋል:: ይህ ሁሉ የሆነው እነሱን ፍጹም መሪ አድርጎ  ያለማስተዋል የሚንጋጋ መንጋ ስላለ ነው:: ይህ ጎጅ ባህል ነጻ ናቸው በሚባሉ የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ሥር መሰረቱን ዘርግቷል:: ሃይማኖቶች የሚያዝዙትን ከማወቅና ከማገናዘብ እንዲሁም ከመፈጸም ይልቅ መሪዎች የሚለፍፉትን በየቤቱ በተናጥል የሚሰሩትን መጥፎ  ድርጊት መደግፍና መሸፋፈን እንደጽድቅ ሥራ እየተቆጠረ ነው:: ይህ ሲባል እውነተኛ የሃይማኖት መሪዎች የሉም ማለት አይደለም ቁጥራቸው ግን እጅግ ውሱን ነው::   

ይህን ሁሉ ያነሳሁት መርህን ሳይሆን መሪን ያማከለ ትግል ዋጋ እንደሌለውና ጎጂ ባህል እንደሆነ ለማሳየት ነው:: ጃንሆይን: መንግስቱን: መለስን: ኢሕአፓን: ቅንጅትን ቄሱን ፓስተሩን ሼኩን መሪና የለውጥ ሐዋርያ አርገን ተከተልናቸው:: ግባቸውን ዓላማቸውን እስትራቴጅያቸውንና ታክቲካቸውን በደንብ ሳናውቅና ሳናምንባቸው መሪዎችን አመንባቸው:: በጭፍንም ተከተልናቸው:: የነሱ እንቅፋት እኛንም ክፉኛ አደናቀፈንና ወደቅን:: በመሆኑም በዓለም ላይ ካሉ አገሮች በሁሉም የእድገትና የለውጥ መለኪያዎች አንሰን ተገኘን:: ወገኖቻችን በባዕድ አገር እንደአውሬ በመሳሪያ ይታደናሉ: በአደባባይ ይገደላሉ: በአረብ እስር ቤቶች የሰውነት ክፍላቸው ለገበያ ይቀርባሉ:: እንደዚህም ሆኖ ችግራችንን የሚፈታ አንዳች መሪ እንዲመጣ ቁጭ ብለን እንመኛለን:: ራሳችን ለውጥ ማምጣት እንደምንችል አናምንም:: ሌላው ቀርቶ የራሳችንን የግል ሰብአዊ መብቶች መሪዎች እንዲያስከብሩልን በትዕግስት እንጠብቃለን: ታዲያ ከዚህ የከፋ ምን ጎጅ ባህል አለ?
                                


6 comments:

 1. wonderful peice, this is also the problem of Africa as acontinent but few African nations have come out from worshiping self-aappointed leaders. Though I hate Obamas effort to democratise Africa, once he criticized Africa correctly : he said Africa doesn't need strong men but strong institutions. This piece of yours can e seen in relation to Obam¨\s statement. African leaders have the need to be worshiped so none of them prepare good leaders. They see themselves as Alpha and Omega, if I am not ruling the country, let the nation die with me. This is their attitude. People have been influenced by this attitude too. Because when a certain attuitude lingers in a society, at last it will be considered as normal and truth.

  ReplyDelete
 2. Dear Teklu,
  It is really a wonderful effort in sharing such marvellous idea for your fellow
  Ethiopians, i totally agree with you,
  we must stop worshipping and over estimating
  leaders and institutions. Keep up the job!!!!!!!!
  worku

  ReplyDelete
 3. Dear Teklu,
  I always give priority to read your articles. The reasons are so many. But, the most important point to me is all articles written by Teklu are very touchy and we found the points in our daily life. You can easily understand what Teklu wants to say. At last, I would like to comment to continue to write in this very important issues of other parts of the Goji culture of Ethiopians.
  Thank you!!

  ReplyDelete
 4. እናመሰግናለን ተክሉ!
  ልክ ነው ብዙ ጎጅ ባህሎች እንዳሉን የታወቀ ነው፡፡ የዘረዘርካቸውም ጎጂ ባህሎች አሉበት፡፡ እንደሚመስለኝ ምናልባት ስለ ጎጂ ባህሎቻችን እንደጻፍከው ሁሉ መፍትሄውም ምን መሆን እንደሚችል ቢያንስ እንደጎጅነቱ የተዘረዘረውን ያህል ብትጨምርበት ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በተረፈ በርታ፡፡ //ፋንታው

  ReplyDelete
 5. ጥላዬ ንጉሤ10 November 2013 at 18:35

  ድ አቶ ተክሉ

  ጐጅ ባህሎቻችን በአስተሳሰባችን፣ በሥራችን እና በማህበራዊ ግንኙነቶቻችን ላይ ያላቸዉን አሉታዊ ተጽእኖ በተመለከተ ላቀረቡት አስተያየት አመሰግነወታለሁ። በተለይም ደግሞ በመሪወች ላይ ያለን ፍጹም እምነትና ያለምንም ማመዛዘን በጭፍን የመከተል ወይም የማግለል ዝንባሌወቻችን እና ተግባሮቻችን በምንፈልገዉ መጠን ወደፊት ለመገስስ እንዳንችል ካደረጉን ምክንያቶች ዋናዉ ነዉ ማለት ያቻላል።

  በቁሳዊ ሀብት ረገድ የድህነት ቁንጮ መሆናችን የታወቀ ቢሆንም ጐጅ ልማዶችን እና አሠራሮችን የተንተራሰዉ የአስተሳሰብ ድህነታችን ትኩረት ተሰጥቶት በቀና መንፋስ ዉይይት ሊደረግበት እና መፍትሄ ሊፈለግለት የሚገባ አብይ ሀገራዊ ጉዳይ ነዉ። ጐጅ ባህሎቻችን በህብረተሰባችን ዉስጥ በሰፊዉ የተንሰራፉ በመሆናቸዉ ከልክፍቱ ንጹህ የሆኑ ወገኖች የሚገኙት በመብራት ተፈልገዉ ነዉ ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዚህ አጋጣሚ እኔ በመብራት ተፈልገዉ ሊገኙ ከሚችሉት ዉስጥ አንዱ አለመሆኔን እንደማዉቅ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ።

  በአስተሳሰባችን ኋላ ቀርነት ምክንያት የገባንበትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ቀዉስ በዚህ አጭር ጽሁፍ በጥልቀት መዘርዘር አይቻልም። ይሁን እንጅ አስተሳሰባችን ሳይጠራ በተሻለ የዕድገት ጐዳና እንራመዳለን ማለት ዘበት መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

  የአስተሳሰባችን ደንቀራነት የሚጀምረዉ የግል አስተሳሰብ ሳይሆን የቡድን አስተሳሰብ እና ተጽዕኖ የሚመራን ከመሆኑ ነዉ። ያለበቂ ምክንያት እና መረጃ ግለሰቦችን፣ ቡድኖችን ወይም ድርጅቶችን መዉደድ እና መጥላት እጅግ የተጠናወተን የአስተሳብ በሽታ ሲሆን እኔም እንደ ወገኖቸ ሁሉ የበሽታዉ ተጠቂ ነኝ።

  በተለይም ደግሞ የመናናቅ፣ ያለመደማመጥ፣ ያለመቻቻል እና በሌላዉ ኪሳራ ትክክል ሆነን ለመገኘትት የምናደርገዉ ጥረት ከመነሻዉ የመከነ በመሆኑ መሻሻል በሩቅ አልፎን እየሄደ እዚህ ደርሰናል። የግል ፍላጎታችን እና ጥቅማችን ከሕብረሰቡ ፍላጎት ስለምናስቀድም የግል ልዕልናን ለማጉላት የምናጠፋዉ ጊዜ እና የምንደክመዉ ድካም ከፍተኛ ነዉ። በመሆኑም አፍራሽ አስተሳሰቦች እና ሥራወች መንሰራፋታቸዉ አስገራሚ ሊሆን አይገባም። በማንኛም ዘርፍ የዘራነዉን እንደምናጭድ ማስታወስ ይኖርብናል።

  አካፋን አካፋ ማለት የሚፈልግ አንተም ያዉ ነህ ሲባል የሚካፋዉ ከሆነ ግለሰብም ሆነ ሕብረተሰብ አንድ እርምጃ ወደ ፊት መራመድ መቻላቸዉ ከህልምነት አያልፍም። ህልምም በአብዛኛዉ ቅዠት ነዉ ስለሚባል ነፃነት፣ ፍትህ እና እኩልነትም ለከንፈራችን የቀረበ ነገር ግን ከተግባራችን የራቀ ቅዠት እንደሆነብን ይኖራል።

  በአሁኑ ወቅት የጐጅ ባህሎቻችን ተጽዕኖ ጎልቶ ከሚታይባቸዉ መድረኮች አንዱ በድህረገጾች ላይ በሚወጡ መጣጥፎች ላይ የሚሰጡ አስተያየቶች ተጠቃሽ ናቸዉ። የአንድን ሰዉ መጣጥፍ ለመተቸት የመጣጥፉን ይዘት በመረዳት ገንቢ አስተያየት ከመስጠት ይልቅ ዘለፋ እና ጥራዝ ነጠቅ ቋንቋ በመጠቀም መወረፍ እና ማዋረድ የተለመደ ነዉ። ይህ ሁኔታ አሳዛኝ የሚሆነዉ ዘለፋ የሚሰነዘረዉ በመጻፍ እና በመናገር ነፃነት ሥም በመሆኑ ነዉ። እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ ዘለፋን ተመርኩዞ ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከኔ በለይ ላሳር የሚል ግለሰብ ራዕይ ያለዉ መሆኑ ወይም አለመሆኑ ነዉ። እርሰዎም በጽሁፈወ መጀመርያ ላይ ማስገንዘቢያ የሰጡበት ምክንያትና በማጠናቀቂያዉም “ለገንቢ አስተያት” በማለት የኢሜል አድራሻዎትን የሰጡበት ምክንያት ከላይ የጠቀስኩትን መሰል አፍራሽ አስተያየት በሩቁ ለማለት ይመስለኛል። ተገቢም ነዉ። በግልም ሆነ በጋራ የምንገኝበት ሁኔታ ፋይዳ በለለዉ እሰጥ አገባ መደናቀፍን አይፈቅድም።

  በጐጅ ባህሎቻችን ላይ ያተኮረ ዉይይት ይቀጥል። እኔም የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግ እሞክራለሁ። እርሰዎም ተከታዩን ጽሁፍ እንደሚያቀርቡ ተስፋ አደርጋለሁ። በመልካም ባህላችን ላይ የመገንባት፤ ጐጅ የሆኑትን የማስወገድ ልምድ እናዳበር።

  ጥላዬ ንጉሤ

  ReplyDelete
 6. I like the helpful info you supplly on ypur articles. I will bookmark your webloog and test once more right here frequently. I am slightyly certain I'll learn a lot of new stuff right right here! Good luck for the next!

  ReplyDelete

የሁለቱ ሲኖዶሶች ፈተና

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕወሓት - መሩ መንግስት ከመጣ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመጋፈጥ ላይ ትገኛለች። ኦርቶዶክስንና አማራን በተለየ መልኩ ለማዳከም ከተቻለም ለማጥፋት የትግሉ ዓላማ አድርጎ...