Friday, 15 November 2013

የተባበሩ ክንዶች ከሳውዲ ባሻገር

ሰሞኑን ቅስም ሰባሪ በሆነ ክስተት ውስጥ ራሳችንን አግኝተናል:: ውድ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ ዘግናኝ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተካሄደባቸው ነው:: የችግሮቹን አይነትና መጠን የኢትዮጵያውያን የመገናኛ ብዙኃን በሚገባ  እየዘገቡት ነው:: በአጠቃላይ ሲታይ ግን የሳውዲዎችን ርምጃ እንደሰው ለመረዳት የሚከብድ ነው:: በዚህ ዘመንና መንግስት ባለበት አገር እንዴት የሰው ልጅ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ካገር እንዲወጣ ይታሰባል? ህግን ለመጠበቅ ወይም ለማስከበር ሲባል በምንም ዋጋ የማይገኘውን ውድ የሰው ልጅ ህይወትን ማጥፋትና ማጎሳቆል እንዴት ሚዛን ይደፋል?

ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አይቻልም:: ምንም እንኳን ከሳውዲ አረቢያ መልካም የሆነ የሰው ልጅ መብት አያያዝ ባይጠበቅም በአደባባይ የሰው አገር ዜጋን መግደል መድፈር እንዲሁም መደብደብ ግን በምንም መልኩ ሊታገሱት አይቻልም:: ሳውዲዎች የኛን ወገኖች ያዋረዱ መስሏቸው ራሳቸውንና አገራቸውን አዋረዱ:: ከሰው ተርታ ለመቆጠር ብዙ እንደሚቀራቸውም ራሳቸው አረጋገጡ:: ሌላው እኛ ኢትዮጵያውያን ልናረጋግጥላቸው የሚገባ ነገር ቢኖር ግን በአንድም በሌላም መንገድ ቢሆን የሞቱና የተጎዱ ወገኖቻችንን ደም  ከእጃቸው እንደምንሻ ነው::

ባለቤቱ  የናቀውን ጨው

የሚያሳዝነው ግን የኢትዮጵያን ህዝብ ወክሎና ሆኖ  በወቅቱና በቦታው አንድም  አካል አለመገኘቱ ነው:: በቅርቡ የሚገኘው ኤምባሲያችን ለወገኖች ሰቆቃ ጆሮውን በበቂ ሁኔታ አልሰጠም:: ምናልባትም ተቋሙ ለተቋምነት የሚያበቃ አቅምና  ተሰሚነት ላይኖረው ይችላል:: መከራ ላይ ያሉ ወገኖቻች የሚደውሉት የይድረሱልን የስልክና የአካል ጥሪ መልስ ካልተሰጠው ታዲያ ይሄ ኤምባሲ ተብሎ  ሊጠራ ነው? ጥያቄው መሆን ያለበት እነማን የዜግነት እርዳታ ይፈልጋሉ እንጅ እነማን በቦሌ እነማን ደግሞ ባባሌ ወጡ አይደለም:: የኢትዮጵያ ኤምባሲ (በሳውዲ አረቢያ) ሆይ በሚዛን ተመዘንክ ክፉኛም ቀለህ ተገኘህ::

መንግስት ደግሞ ስለሞቱትና ስለተጎዱት ሰዎች ብዛት ከራሱ ጋር ክርክር ይዟል:: ለመሆኑ የመንግስትን አፋጣኝና በቂ ትብብር ለማግኘት ምን ያህል ሰው መሞትና መድማት አለበት? የተጎዳው አንድ ሰው ብቻ ቢሆንስ ድንግጥ ተብሎ የሳውዲን መንግስት መጠየቅ አይገባም? የተጎዱት ሙሉ ካሳ ሳይሰጡና የሳውዲ ህዝብና መንግስት በይፋ ይቅርታ ሳይጠይቁ ምንም አይነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳይኖር መንግስታችን ለምን አላደረገም? አምባሳደራቸውን ከአዲስ አበባ ማባረር: ወደሳውዲ የሚላኩትን የንግድ እቃዎች ማቋረጥ: ኢትዮጵያ ያሉትን የሳውዲ ቢዝነሶች ለጊዜው ሥራ እንዲያቆሙ ማድረግ: ለተባበሩ መንግስታት እየተደረገ ያለውን ውንብድና ማጋለጥ: ወዘተረፈ ራሱን መንግስት ብሎ ከሚጠራ ማንኛውም አካል ይጠበቅ ነበር:: ይህን ለማድረግ አቅምና ፍላጎት ቢያንስ ዝም ይባላል እንጅ ጉዳቱን አሳንሶ ማየትና ማቅረብ ምን ይሉታል? ኢትዮጵያ ውስጥስ የታሰበውንስ ሰላማዊ ሰልፍ መከልከል ምን ይሉታል? የአቅም ማነስ ወይስ የልቡና ክፋት ወይስ ባንዳነት? ለማንኛውም የዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም መሥሪያ ቤት ውጭ ጉዳይ ሆይ በኢትዮጵያውያን ተመዝነህ ቀለህ ተገኘህ::

ሳይደግስ አይጣላ

ደስ የሚለው ግን በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን በማውገዝ መራር ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው:: በአውሮፓ በሰሜን አሜሪካ በእስያና በአፍሪካ ሰላማዊ ሰልፎችን በነጭ የሥራ ቀናት ሳይቀር እያደረጉ ነው:: ለማድረግም ተዘጋጅተዋል:: ማኅበራዊ ድረ ገጾች ልዩ ትኩረት ሰጥተውታል:: የኢሜል ልውውጦች ርዕሳቸው ይህ ጉዳይ ነው:: ኢትዮጵያውያን ስንገናኝ ውይይታችን ይህ ጉዳይ ሆኗል:: አገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን እያሰሙ ነው:: አዲስ አበባ ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች የተቃውሞ  ሰልፍ ያካሂዳሉ (በተናጥል ቢሆንም)::

በአጠቃላይ ሲታይ የሳውዲ አምባሳደሮች እንዲሁም መንግስት ኢትዮጵያውያን አሁንም ቢሆን አንድ እንደሆንን ያይን ምስክሮች እየሆኑ ነው:: ችግሩ በአጥጋቢ ሁኔታ እስኪፈታ ድረስም ተቃውሞው እንደሚቀጥል እያወቁ ነው:: ከአሁን በኋላ አንገታቸውን ቀና አድርገው ለመሄድ ይቸገራሉ:: ደምን ያፈሰሰ ሰላምና ሞገስ የለውም!

ከሳውዲ ባሻገር

ነገር ግን አሁን እያደረግነው ያለው ወገን የመታደግ እንቅስቃሴ ዘላቂ መሆን አለበት:: ለጊዜው ተንጫጭተን ዝም የምንል ከሆነ ስሜታዊ ብቻ እንደሆንን ማሳያ ነው:: ለወደፊትም ተመሳሳይ ጥቃት በማንም ወገን ወይም አካል እንደማይፈጸምብን ማረጋገጫ የለንም:: ትብብራችን የሚቀጥል ከሆነ ግን ለህዝባችን ታዕምር መስራት እንችላለን::

እንደኢሳት ዘገባ ከሆነ የተከሰተውን ቀውስ በተመለከተ ዓለም አቀፋዊ አካል ወይም ግብረ ኃይል ተቋቁሟል:: ይህ ሊበረታታ የሚገባው ጉዳይ ነው:: ምንም እንኳን ይህ አካል ምን ምን ነገሮችን እንደሚሰራ ግልጽ ባይሆንም:: እንደኔ አመለካከት ከሆነ ይህ አካል ላቅ ያሉ አላማዎችን ማንገብ አለበት:: ዋና ዋናዎቹ
  • የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን  ማንነትና ብዛት አጣርቶ አግባብነት  ያለው የህግ ርምጃ በገዳዮች ላይ እንዲወሰድ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ለቤተሰብም አስፈላጊው ካሳ እንዲከፈል ማስደረግ 
  • የተደበደቡ ወገኖቻችን አስፈላጊውን ህክምና እንዲያገኙ መጣርና ካሳ እንዲፈለጋቸው መጠየቅ
  • የተደፈሩ እህቶቻችን አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው መጣርና ካሳ እንዲከፈላቸው መጠየቅ
  • ወደኢትዮጵያ መመለስ ለሚፈልጉ ትብብር እንዲደረግ ጫና መፍጠር
  • ንብረታቸው የተዘረፈባቸውና የወደመባቸውም ቢሆኑ ካሳ እንዲሰጣቸው መጠየቅ  
  • የሳውዲ መንግስትና ህዝብ ለኢትዮጵያውያን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ ግፊት ማድረግ   
  • ይህ የማይሆን ከሆነ በሳውዲ ቢዝነሶች ላይ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ማዕቀብ እንዲያደርጉ ማበረታታት
  • በተደራጀ መረጃና ማስረጃ  የተፈጸመውን ግፍ ለዓለም ህብረተሰብ ማጋለጥ

እነዚህ ሥራዎች ጊዜያዊና ሳውዲ አረቢያ ያደረገችውን ወንጀል የተመለከቱ ናቸው:: የእኛ የኢትዮጵያውያን ችግሮች ከዚህ በላይ ናቸው:: ኢትዮጵያውያንን ዕለት ከዕለት የሚያሰቃዩ ብዙ አገራት ብዙ መንግስታት ብዙ ችግሮች አሉ:: ይህ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ኃይል ራሱን በተጠናከረ መልኩ ካደራጀ እነዚህን ችግሮች የመፍታት ወይም በጣም የመቀነስ እምቅ ጉልበት ይኖረዋል:: ማለትም የዚህ ኃይል ለዘለቄታ መኖር ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው:: ከሳውዲ ጉዳይ እልባት በኋላ ሥራውንም ቀጥሎ በተዘረዘሩ ጉዳዮች ዙሪያ ሊያደርግ ይገባል ብዬ አምናለሁ:: እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያውያንን ከዘር ከፖለቲካና ከሃይማኖት ነጻ በሆነ መልኩ ያስተባበረ ኃይል የለምና!
·         ኢትዮጵያውያን በግልም ይሁን በኅብረት በየትም አገር መብታቸው ሲጣስ ይከራከራል አስፈላጊውን አካል በመያዝ ለተጎዱት ጠበቃ ይቆማል
·         በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚያጋጥማቸውን ከአቅም በላይ የሆኑ ማኅበራዊ ምጣኔ ሃብታዊ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ሲገጥማቸው አስፈላጊውን ድጋፍና  ምክር ያደርጋል
·         ኢትዮጵያዊ ስሜት ኅብረትና መተሳሰብ እንዲጨምር የውይይት መድረኮችን ያመቻቻል ፕሮጀክቶችን ይቀርጻል
·         ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች ያለምንም ፍርሃት በነጻነት የመኖር መብታቸውን እንዲኖሩ ያበረታታል ያለአግባብ የሚታሰሩትን ይታደጋል    
·         ልማትና ለውጥ ተኮር ፕሮጀክቶችን ውጭ ባሉ አገሮች በመክፈት ኢትዮጵያንን ያግዛል ያስተባብራል
·         የፖለቲካ ድርጅቶች የልዩነት መኖርን አምነው በጋራ እንዲሰሩ ያበረታታል
·         እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለተፈጥአዊ ሰብአዊና ህገ መንግስታዊ መብቱ ዘብ እንዲቆም ማስተማር ማበረታታት

የተቋሙ አቋም

እኒህንና ሌሎችንም ዓላማዎች ለማሳካት የዓለም አቀፉ ግብረ ኃይል ማንነትና ምንነት ወሳኝ ነው:: በአጠቃላይ የዚህ አካል አባላት ራእይ ያላቸውና ከህዝቡ በአስተሳሰብና በምግባር ቀደም ብለው የሄዱ መሆን አለባቸው:: ስሜት የማያጠቃቸውና የአጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድና እስትራተጂ በመንደፍ ለችግሮች ቅደም ተከተል መስጥት የሚችሉ መሆን አለባቸው:: ተጨማሪ መስፈርቶችንም መዘርዘር ይቻላል::
·         የብሄር ፖለቲካ ያላንገላታቸው
·         የቡድንም ሆነ የግለሰብ መብትን አቻችሎ  መሄድ እንደሚቻል የሚያምኑ
·         ከትናንቷ ኢትዮጵያ ይልቅ የዛሬዋንና የነገዋን አብዝተው የሚያዩ
·         ከህግና ከህዝብ በታች መሆናቸውን የሚያምኑና የሚተገብሩ
·         ሌላውም ኢትዮጵያዊ እንደነሱ ጥሩ መስራት እንደሚችል የሚያውቁ
·         ከተለያዩ  አካላት ጋር የተሳካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መፍጠር የሚችሉ
·         በመንግስትና በዘር ወይም በሃይማኖትና በፖለቲካ መስፈርቶች ህዝብን የማይከፋፍሉ
·         ታላቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የሚያምኑና እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ቀድሞ ማወቅና አማራጭ መፍትሄ ማስቀመጥ የሚችሉ
·         አብሮ  መስራት አስቸጋሪ ከሆነው ከመንግስት ጋር ሳይቀር  ለመተባበር ጥረት የሚያደርጉ ወዘተረፈ

እንዴት ይዋቀር

በዚህ ጽሁፍ መግቢያ እንደጠቀስኩት በሳውዲ እየተሰቃዩ  ያሉ ወገኖቻችንን  ለመታደግ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ግብረ ኃይል እንደተቋቋመ ታውቋል:: ይህ አካል እነማንን ያቀፈ ስብስብ እንደሆነ አላውቅም:: ከላይ የጠቀስኳቸውንና ሌሎችንም የመሪ ክህሎቶች የሚያሟሉ ከሆነ ይህ ጽሁፍ የሚሰብከውን ዓላማ ለማሳካት ሊያስተባብሩ ይችላሉ:: ይህ ከሆነ እንቅስቃሴው ፍጥነትና  ቅልጥፍና ይኖረዋል:: ቡድኑ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በአባልነት ወይም በደጋፊነት ሊያሳትፍ ይችላል:: ለዚህም በየዋና ከተማዎች የሚገኙ የኢትዮጵያውያን ማኅበራት (Ethiopian communities) ልዩ  አስተዎጽዖ ሊያደርጉ ይችላሉ:: ምናልባት ችግር ሊሆን የሚችለው አንዳንድ ማኅበራት የፖለቲካ ጥላ ይዘው የሚዞሩ ይሆናል:: ይህ ከሆነ በቀና መንፈስ ላይተባበሩ ስለሚችሉ ሌላ ገለልተኛ ወገን መፈለግ ይሻላል:: ምናልባት የሃይማኖት መሪዎች በተሳታፊነት ወይም በአማካሪነት ሊያገለግሉ ይችሉ ይሆናል:: ከዚህ ውጭ ግን ያገር ፍቅር የወገን ችግር የሚያንገበግባቸው ግለሰቦች ስላሉ እነሱንም ማሳተፍ የሚቻልበት መንገድ ቢመቻች የተመረጠ ነው:: አካሄዱ ምንም ይሁን ምን በየዋናከተማው የግንኙነት ጣቢያዎች ቢኖሩ ለሥራው ቅልጥፍና ወሳኝ አስተዋጽዖ ማድረግ ይችላሉ:: ይህ ሁሉ ሲደረግ ግን ገዥው ፓርቲ እጁን አጣጥፎ  እንደማይቀመጥ ከወዲሁ መገንዘብና መቋቋሚያ ስልቶችን ማዘጋጀት ወሳኝ ነው::

ግልጽ ማድረግ ያለብኝ ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲቋቋም እየለፈፍኩ እንዳልሆነ ነው:: የእኔ ሃሳብ የሚያጠነጥነው ከፖለቲካ ከዘር ከሃይማኖት ከጾታ እንዲሁም ከግለሰብ ስግብግብነትና ሁሉን አውቃለሁ ባይነት ፍጹም ነጻ የሆነ አካል እንዲቋቋም ነው:: አላማውም አንድና አንድ ነው: ውጭ አገር የሚኖሩና አገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያንን መብትና ጥቅም ለማስከበር ሌት ከቀን መጣር:: እንዲህ አይነት አካል ከተቋቋመ የህዝቡን የልብ ትርታ ማግኘት ይችላል:: ለአገራችንም ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት ይቻላል::        

ማጠቃለያ  

ይህንን ጽሁፍ የሚያነብ ሰው የተሰነዘረውን የመፍትሄ ጠቋሚ ሃሳብ  «ምናባዊ» በማለት ሊያጣጥለው ይችላል:: ለኔ ግን ማንም ለኢትዮጵያውያን ለውጥ አመጣለሁ ሰቆቃን አስቆማለሁ ብሎ  የሚያስብ  አካል  እነዚህንና ሌሎችንም የመሪ እሴቶች  ካላሟላ እንደማይሳካለት ስለማውቅ አልቀበለውም:: ህዝብን ማገልገል  ከፈለገ ህዝቡ «ይህማ እንዴት ይቻላል» ብሎ  ተስፋ የቆረጠበትን ጉዳይ አንስቶ  ለውይይት ከዚያም ለመፍትሄ ማብቃት አለበት:: በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያን  «አይቻልም» ብለው የደመደሙት ነገር ቢኖር ነጻነት እኩልነት ፍትህና እድገት ናቸው:: እነዚህን ለማሳካት አቅሙና ቆራጥነቱ የሌለው ተቃዎሚ ፓርቲ ወይም ሲቪክ ማኅበረሰብ ወይም ግለሰብ ካለ አርፎ ይቀመጥ:: እኔ ተመሪ እንጅ መሪ አይደለሁም ብሎ ይመን:: ቆርጠው የተነሱትን አያዳክም:: በሳምንት ሁለት ቀናት ለዚያውም ለተወሰኑ ሰዓታት በሚደረግ ጉንጭ አልፋ ክርክርና አምባጓሮ በሚመስል ስብሰባ የኢትዮጵያ ችግር አይፈታም:: ለገዥው ፓርቲ «ተቃዎሚ የፖለቲካ ፓርቲ ያበረታታል» የሚል ድል ከመስጠት ውጭ ሌላ ጥቅም የለውም:: እንዲያውም ብቃት የሌላቸው የፖለቲካ ሰዎችና ፓርቲዎች የህዝቡንም ለመብቱ የመታገል ሞራልና ብቃት ክፉኛ እየተፈታተኑት ነው:: ስለዚህ ላቅ ያሉ ችሎታዎችና ተሞክሮዎች እንዲሁም ቆራጥነት የሚያንሰው ማንም ካለ ሊያስተባብርና ሊመራ ወደመድረክ አይውጣ:: እኛ ኢትዮጵያውያን ማንም የሚለማመድብን ምቹ መሬቶች አይደለንም:: አንድ እውነተኛ መሪ ነኝ የሚል አካል ካለ የኢትዮጵያ ችግር በሳውዲ አረቢያ ሰሞኑን በመታየት ላይ ካለው ዘግናኝ ግፍ የገዘፈ እንደሆነ ማየት አለበት:: ለዚያም የሚመጥን ብቃት ልምድና መስዎእትነት እንደሚያስፈልግ ጠንቅቆ  ይረዳ!  

No comments:

Post a Comment

የሁለቱ ሲኖዶሶች ፈተና

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕወሓት - መሩ መንግስት ከመጣ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመጋፈጥ ላይ ትገኛለች። ኦርቶዶክስንና አማራን በተለየ መልኩ ለማዳከም ከተቻለም ለማጥፋት የትግሉ ዓላማ አድርጎ...