Sunday, 29 December 2013

ጎጂ ባህሎቻችን (ክፍል 2)

«ጎጂ ባህሎቻችን» በሚል ርእስ ተከታታይ ጽሁፎችን እንደማቀርብ ከሳምንታት በፊት በተለቀቀው ክፍል 1 (ጽሁፉን ለማንበብ ይህን ይጫኑ http://tekluabate.blogspot.no/2013/10/blog-post_20.html) ጽሁፌ ላይ ቃል ገብቼ ነበር:: የመጣጥፎች ዓላማም የማይጠቅሙንን ባህሎች በሚገባ እንድንመረምርና ገንቢና ጠቃሚ ባሃሎቻችንን እንድንገነባ የሚያስችል የውይይት መድረክ መፍጠር ነው::


ክፍል 1 የመጣጥፎችን አስፈላጊነትና ዓላማ በግልጽ ዘርዝሯል:: የፖለቲካ ወይም የኮሚቴ መሪዎችን ያማከለ የለውጥ ፍላጎት ምንኛ ጎጂ ባህል እንደሆነም ክፍል 1 አትቷል:: ይህንንም በተመለከተ በርካታ ገንቢ አስተያየቶችን ከውድ አንባብያን አግኝቻለሁ:: በዚህ አጋጣሚ ጊዜያቸውን ወስደው አስተያየት ለሰጡኝ አንባብያን የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ!

ክፍል 2 ደግሞ ሌሎች በጣም እየጎዱን ያሉትን ባህሎች ይዘረዝራል:: አንባብያን ይህን ጽሁፍ እንደምክንያት በመቁጠር የራሳቸውንና የሌሎችንም አስተሳሰብና ምግባር በአንክሮ እንዲፈትሹ ይጋበዛሉ:: ነገር ግን ይህን ጽሁፍ በተመለከተ አንባብያን የሚከተሉትን ነጥቦች ግምት ውስጥ እንዲያስገቡልኝ  አሳስባለሁ::
  • ቀጥለው የተዘረዘሩት ጎጂ ባህሎች የራሴ እይታዎች ናቸው እንጂ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምርን የተሞረኮዙ አይደሉም
  • እነዚህ ባህሎች ይበልጥ የሚዘወተሩት በአብዛኛው በተማረው ኢትዮጵያዊ ዜጋና የፖለቲካ ድርጅቶች (የመንግስትም የተቃዋሚም) ነው የሚል ግንዛቤ አለኝ
  • ይህም ሲባል ሁሉም ሰው ወይም ድርጅት ቀጥለው የተዘረዘሩትን ሁሉንም ጎጂ ባህሎች አራማጅ ነው ማለት ግን አይደለም:: እያንዳንዱ አንባቢ የየትኛው ጎጂ ባህል ተጠቂ እንደሆነ ራሱ ይገምግም
  • እነዚህ  የተዘረዘሩት ጎጂ ባህሎች የእኔ አዲስ ግኝቶች ናቸው እያልኩም አይደለም:: ምክንያታዊና እውነት ተኮር ኅሊና ያለው ሰው ሁሉ ሊያውቃቸው የሚችላቸው ናቸው:: ለይፋዊ ውይይት ማቅረብ ግን እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ እገምታለሁ
  • ቀጥለው የሚቀርቡት ጎጂ ባህሎች በግለሰብ ህይወትና በፖለቲካዊ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎቻች ዙሪያ የሚዘወተሩ ናቸው 

መለኮታዊ  ኃይል  ለለውጥ

አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ሥር-ነቀል ፖለቲካዊ ለውጥና ዘለቄታነትና ፍትህ የተሞላበት እድገት እንደሚያስፈልግ ያምናል:: ይመኛልም:: ይህ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል ሲታሰብ ግን ናላ ያዞራል:: ገዥው ፓርቲ የነጻነትን ደብዛ ለማጥፋት ሌት ከቀን ይሰራል:: ህዝቡንና ተቃዎሚውን እንዲሁም የራሱን ደጋፊዎችና አባላት ሳይቀር በማያፈናፍን ቁጥጥር ስር አውሏል:: የማያፈናፍኑ ህጎችና ፋታ የማይሰጡ ካድሬዎች የሚሊዮኖችን አንገት አስደፍተዋል:: ይህ ሁኔታም ለቀጣይ በርካታ ዓመታት እንደሚቀጥል እየተነገረን ነው::

በአንጻሩ ደግሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠብ የሚል ሥራ ሰርተው አላሳዩንም:: እንዲያውም እርስበርሳቸው መግባባት ሲያቅታቸው አዲስ ፓርቲ ማቋቋምን እንደ ፍቱን መፍትሄ የቆጠሩት ይመስላል:: አንዱ ሌላውን በአደባባይ ሲሳደብና ሲያዋርድ ይታያል:: የተቀናጀና ፍሬ ሊያፈራ የሚችል ሥራ የሚሰሩበት መቼት ለእነሱም አይታወቅም:: በአጠቃላይ ሲታይ የሚፈለገው ለውጥ ከመንግስትም ከተቃዋሚም በኩል በቀላሉ እንደማይመጣ ማመን ብዙም ሞኝነት አያሰኝም::

በመሆኑም ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በመለኮታዊ ጣልቃ-ገብነት ወይም ቸርነት ብቻ እንደሆነ ሰዎች ማመን ጀምረዋል:: «እሱ ይቅር ካላለን በስተቀር…» የሚሉ ንግግሮችን መስማት እየተለመደ ነው:: ስለዚህም ብዙ ሰው በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የመሳተፍ ፍላጎትና እቅድ የለውም:: ፖለቲካ ፓርቲዎች በቂ አባላት የሏቸውም:: ያሉት አባላትም በሚገባ አይሳተፉም:: መዋጮ አይከፍሉም:: ስብሰባ ቢጠራ ህዝብ በነቂስ አይሄድም:: ሰላማዊ ሰልፍ ተዘጋጅቶ የሚወጡት ሰዎች ጥቂት ናቸው::

ለእኔ ይህ ጎጂ ባህል ነው:: እንዲያውም ገዳይ ባህል! የራሳችንን ንዝህላልነት ስንፍናና ፍርሃት በመለኮታዊ ፈቃድ ማሳበብ ለችግራችን መፍትሄ እንዳናገኝ የምናደርገው ሩጫ ነው:: ክርስቲያን ነኝና አምላክ የሚያቅተው ነገር እንደሌለ አምናለሁ:: በግል ህይወቴም አይቻለሁ:: ነገር ግን ቁጭ ብሎ ከላይ ከአርያም መፍትሄ መጠበቅ ስንፍና ብቻ ሳይሆን ኃጢአትም እንደሆነ የኅይማኖት ትምህርት ያስጠነቅቀናል:: የመጀመሪያው ሰው አዳም እንዲኖር የተፈጠረባትን ቦታ እንዲጠብቃትና እንዲንከባከባት ፍጹም የሆነ ሥልጣን ተሰጥቶታል:: በሚገርም ጥበብ የተሰራው የሰው ልጅ አእምሮ/ኅሊና ዋናው ሥራው በዚህ ዓለም ላይ ያሉ ነገሮችን ክስተቶችን መርምሮ መፍትሄ መፈለግ ነው:: ሰው ሰራሽ ችግሮች (አምባገነንነት ጨምሮ) የሚፈቱት በሰው ልጅ ልዩ ጥረት ነው:: በቂና ንጹህ ጥረት ተደርጎ ችግሮች ሳይፈቱ ቢቀሩ መለኮታዊ እገዛ መጠየቅ ያባትና የናት ነው:: የተቀናጀና ሥልት-መራሽ ትግል ሳያደርጉ ፈጣሪ ለውጥ እንዲሰጠን መጠበቅ ግን ሰው የመሆንን ልዩ ምሥጢር መዘንጋት ነው:: ይህ ሁኔታ ካድሬዎች እንደልባቸው እንዲፈነጩ አስችሏቸዋል:: ኢሕአዴግ ለኢትዮጵያ የሚያስብና የተዘጋጀ አካል እንደሌለ ይሰብክበታል::
   
ይህ ሲባል ግን ጸሎት ወይም ሌሎች ኀይማኖታዊ ሱታፌዎች በራሳቸው ዋጋ የላቸውም ማለት አይደለም:: አምባገነንነት የሚወገደው በጾምና በጸሎት ነው ብሎ  የሚያምን ሰው ካለ በዚሁ ይቀጥል:: እንደ አንድ የትግል ሥልት ሊቆጠር ይችላል:: ነገር ግን ጾምና ጸሎት ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ግድ ይላል:: ቂም ይዞ ጸሎት ሳል ይዞ  ስርቆት አያዋጣምና::

በአጠቃላይ ሲታይ በዚህ ባለንበት ወቅት የሰውንና የመለኮትን ድርሻ ጠንቅቀን አውቀን እየተጓዝን ነው የሚል እምነት የለኝም:: እምቅ የማሰብ የመናገርና የመተግበር ኃይል እያለን አልተጠቀምንበትም:: በገጠር የሚኖረውን አብዛኛውን ምስኪን ኢትዮጵያዊ ልንታደገው አልቻልንም:: አስተሳሰባችን አዚም ሆኖ የግልና የጋራ መብቶቻችንና እሴቶቻችን እንዳንጠብቅ አድርጎናል::

በወቅታዊ ክስተቶች መጠመድ

ፖለቲካዊ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ለውጥ ወይም እድገት እንዲመጣ የሚታገሉ ድርጅቶችና ግለሰበቦች በጣም አናሳ ቢሆኑም አሉ:: በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ አስፈሪ ዝምታ ተስፋ ሳይቆርጡ ይንቀሳቀሳሉ:: ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል! ዳሩ ግን ብዙ እንቅስቃሴዎቻቸው ወቅታዊና ውሱን ናቸው:: ብዙ ጊዜ የመንግስት ውሳኔዎች እና የሥራ አፈጻጸሞች የእንቅስቃሴዎቻቸው ምክንያት ወይም መንስዔ ናቸው:: ወይም ታላላቅ ክስተቶችን ተከትሎ መልስ-መሰል እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ:: ህገ መንግስቱ ሲጸድቅ ኤርትራ ስትገነጠል ምርጫዎች ሲካሄዱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲታወጀ ጋዜጠኞች ሲታሰሩ የአባይ ግድብ ፕሮጀክት ሲለፈፍና ገንዘብ ስብሰባ ሲጀመር ወዘተረፈ መራር የሚመስሉ ትግሎች ተደርገዋል:: ሰልፎችና ውይይቶች ተካሂደዋል:: የአቋም መግለጫዎች ወጥተዋል:: አሁን ደግሞ በሳኡዲ ዓረቢያ በስቃይ ላይ ስለሚገኙ ወገኖቻችን ሌት ከቀን በዘመቻ እየሰራን ነው::

ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ በራሱ አበረታች ነው:: ነገር ግን ከበስተጀርባ የሚያመላክተው ድክመት አለ:: አብዛኞቹ የፖለቲካ ሥራዎች መነሻቸው መንግስትና የመንግስት ድርጊቶች ናቸው:: ይህም ማለት ለተቃዋሚዎች አጀንዳ የሚቀርጽላቸው መንግስት ነው ቢባል አይጋነንም:: ይህ በራሱ አርቆ ማሰብ ላይ ያልተመረኮዘና ጊዜያዊ እሳት ማጥፋት ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ሥልት መኖሩን ያመላክታል:: ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ስናተኩር መንግስት ደግሞ ለዓመታት ሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ዘዴ ያምሰለስላል:: እውነተኛና ጠንካራ ተቃውሞ እንደማይገጥመውም የሚያምን ይመስላል::

ለዚህም ነው ይህን ሁሉ የተቃዋሚዎች ጥረት እንደ ጎጂ ባህል የቆጠርኩት:: ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ ለመብታቸው የሚታገሉ ግለሰቦች መንግስት በሚሰራቸው እለታዊ ተግባሮች ሙሉ በሙሉ ሳይዋጡ ለነገ ማሰብና ስትራቴጂካዊ ትግል እንዲያካሂዱ ይጠበቃል:: የትናንቱንና የዛሬውን የአገራችንን ሁኔታ መርምሮ ለነገ በስፋትና በጥልቀት ማቀድና መንቀሳቀስ ወሳኝነት አለው:: ለምሳሌ ያህል የሳኡዲውን ዘመቻ ትልቅና ቀጣይ አድርጎ መንቀሳቀስ ይቻላል:: በአጠቃላይ ውጭ ላሉ ኢትዮጵያዊያን መብትና ጥቅም የሚቆም ቋሚ አካል ማድረግ ይቻላል:: ይህን የሳኡዲውን ጉዳይ በተመለከተ ከዚህ በፊት የተዘጋጀውን ጽሁፍ ዚህ ይመልከቱ (http://tekluabate.blogspot.no/2013/11/blog-post.html):: መንግስት የሚሰራቸውን ነገሮች እየጠበቅን መቃወምና የአቋም መግለጫ ማውጣት ብቻ የትም አላደረሰንም አያደርሰንም::  

ይህ ሲባል ፓርቲዎች ሁሉ ስትራቴጂክ እቅድ ፈጽሞ የላቸውም ማለት አይደለም:: ብዙዎች በደንብ የተቀናበረና የተጻፈ ራእይና ዓላማ አላቸው:: ወደሥራ የተተረጎመ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ግን ለማዬት አልቻልንም:: በሥራ ያልተገለጠ እምነት ከንቱ እንደሆነ ሁሉ በሥራ ያልተተረጎመ የፖለቲካ አቋም ህዝብን ተስፋ ከማስቆረጥ ያለፈ አንደምታ የለውም:: ትክክለኛ ተቃዋሚ እጅግ ቀድሞ በማሰብ ለመንግስት «የራስ ምታት» ይሆናል እንጅ መንግስት የሚሰራቸውን የማስታገሻ ሥራዎች በማውገዝ አይጠመድም::                 

የትችት ባህላችን

ሌላው ጎጂ ባሃላችን ሂስ መስጠትንና መቀበልን የተመለከተ ነው:: ፓርቲዎች ወይም ኮሚቴዎች ከያዙት አቋም የተለዬ ሌላ አማራጭ ሃሳብ ካለ ማቅረብና መከራከር ተገቢ ነው:: ነገር ግን የተቺዎች ትኩረት የሚውለው በፓርቲዎች ወይም ኮሚቴዎች ሃሳብ ወይም እቅድና ሥራ ላይ ሳይሆን በነሱ ማንነትና ምንነት ላይ ነው:: አንዳንድ ትችቶች ዓላማቸው መሻሻል እንዲመጣ ማድረግ ሳይሆን መወናበድና ተስፋ መቁረጥን ማስፈን ነው የሚመስለው:: በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከለ ያለማቋረጥ የሚደረጉ መወጋገዞች የዚህ ጎጂ ባህል አይነተኛ ማሳያዎች ናቸው::

የሚተቸውም (ትችት የሚቀርብለት/የሚቀርብበት አካል) ትችቶችን በንቀትና በእልህ ያያቸዋል:: ደርግን የሚተቹ አካላት የፊውዳል ሥርዓት ናፋቂዎች ተብለዋል:: ያሁኑን መንግስት የሚተቹ ደግሞ የደርግ ቅሪቶች ወይም ነፍጠኞች ተብለው ይወገዛሉ:: አሁን አሁን ደግሞ አሸባሪዎች ወይም ግንቦት ሰባቶች ተብለው ይሳጣሉ ይከሰሳሉ ይታሰራሉ ይሳደዳሉ.: በአንጻሩ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚተች አካል የወያኔ ደጋፊ ካድሬ ተብሎ ይገፋል:: የለውጥ እንቅፋት ተብሎም ይሳለቅበታል:: ተቺዎች ያለፍላጎታቸው ከማይፈልጉት ፓርቲ ወይም ቡድን ጎን እንዲቆሙ በአንድም በሌላም መንገድ ይነገራቸዋል:: ተከታታይ አውጋዥ ጽሁፎች ይለቀቅባቸዋል:: በዚህ ምክንያት ሃሳብ የሚሰጡ ሰዎች ይሳቀቃሉ:: የማሰብና የመናገር መብታቸውን እንዲገድቡ ይገደዳሉ:: በመሆኑም «ይህ አስተያየቴ/ሃሳቤ እገሌን የሚመለከት ሳይሆን…» እያሉ መናገር እየተለመደ መጥቷል::

በግለሰብ ደረጃም የሚሰጡት አስተያየቶች የዚሁ አይነት ናቸው:: የግለሰቡን ጽሁፍ በቀጥታ ከመተቸትና ከመገምገም ይልቅ የጸሃፊውን ምንነትና ማንነት ማናቋሸሽ የተለመደ ሆኗል:: ይህንን እውነታ ለመታዘብ በየድኅረ ገጹ የሚወጡ ጽሁፎችን በተመለከተ የሚሰጡትን አስተያየቶች ማንበብ በቂ ነው:: የውሸት ስም በሚለጥፉ ሰዎች የሚብጠለጠሉት ሃሳቦች ሳይሆኑ ጸሃፊዎች ናቸው:: በጣም ጸያፍና አሳፋሪ ስድቦች ተደርድረው ይገኛሉ:: የጸሃፊዎች ብሄርና የግል ህይዎት ስድቦችን ለማጣፈጥ ይተነተናሉ:: አሁን እንደዚህ አይነቶቹ አስተያየቶች ነው የሚባሉ ወይስ አሰዳደቦች? ምንስ የሚፈይዱት ጉዳይ አለ? ለእኔ ብልሹ አስተያየት: የሚሰጠውን ሰው የብስለት ደረጃ ከማሳየት ውጭ ምንም አይነት ግብ አይመቱም:: በስድብ-ነክ አስተያየቶች የተነሳ ከመጻፍ የሚያቋርጥ ጸሃፊ የለም:: መጻፍ ጥሩ አስተያየት መሰብሰብ ላይ ያተኮረ አይደለምና:: በመሆኑም ስድቦችና ሌሎች ስሜት የሚንጸባረቁባቸው አስተያየቶች በጣም ጎጂ ናቸው::

በግልባጩ ደግሞ ጽሁፎችን ወይም የተከናወኑ ሥራዎችን በደንብ ሳይመረምሩ የተጋነነ ምስጋና የሚያዥጎደጉዱ አሉ:: ርእሱን ወይም የጸሃፊውን ስም በማየት ብቻ «ግሩም ነው» የሚሉ አሉ:: ለእኔ እነዚህ አይነት አስተያየቶችም ጎጂ ናቸው:: አንባቢው የተሻለ የንባብ ልምድ እንዳያካብት ከማድረጋቸው በተጨማሪ ጸሃፊዎች እጅግ ለተሻለ ሥራ እንዲነሳሱ የማነቃቃት እድላቸው በጣም ውሱን ነውና:: ያልተሰራውን እንደሆነ አድርጎ መቁጠር ወይም በጣም አጋኖ ማሳዬት እንደጎጂ ባህል መቆጠር አለበት:: ገንቢ ትችት ለአገርና ለግለሰብ ህይዎት መሻሻል ጠቀሜታው የጎላ ነውና ተቺዎች ሆይ ስሜታችሁን ተቆጣጥራችሁ ትክክለኛና ኃላፊነት የተሞላበት አስተያየት ስጡ!
\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\\

 ይቀጥላል!
                                         

No comments:

Post a Comment

የሁለቱ ሲኖዶሶች ፈተና

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕወሓት - መሩ መንግስት ከመጣ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመጋፈጥ ላይ ትገኛለች። ኦርቶዶክስንና አማራን በተለየ መልኩ ለማዳከም ከተቻለም ለማጥፋት የትግሉ ዓላማ አድርጎ...