Friday 30 May 2014

አገራዊ ስሜት ለምን ይጎድለናል

ከበርካታ ሳምንታት በፊት ከጓደኞቼ ጋር ኢትዮጵያ ስላለችበት ወቅታዊ ሁኔታ እየተወያየን ነበር:: ሁሉም ተሳታፊ የተስማማበት ጉዳይ ቢኖር ኢትዮጵያ ከምንም ጊዜ በላይ እጅግ ከባድ ማኅበራዊ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ መግባቷን ነበር:: ለዚህም በግንባር ቀደምነት ተጠያቂው መንግስት እንደሆነ ቢሰመርበትም ህዝቡም ላለንበት ሁኔታ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ታላቅ አስተዋጽዖ እያደረገ እንደሚገኝ ተወስቷል::
እንዲያውም ኢትዮጵያውያን ለአገርና ለለውጥ ያላቸው ስሜት እንደ በረዶ የቀዘቀዘ እንደሆነ ተነገረ:: ለዬት ያለና ታላቅ አገራዊና ወገናዊ ጉዳይ ሲነገር ህዝቡ ጸጥ ረጭ ብሎ ሰምቶ ሃሳቡን ሳይሰጥ ሹልክ እያለ እንደሚወጣ ሁሉም የታዘበውን እያነሳ ተናገረ:: ብዙዎች ለወገናቸው ጥልቅ ስሜት ስለሌላቸውና በተለያዩ  ጉዳዮች ላይ በንቃት ስለማይሳተፉም መንግስት በጭቆናው እንዲቀጥል ሞራልና ጉልበት እየሰጡት እንደሆነም ተጨመረበት::   

ከቀናት በኋላ በሌላ መድረክ ፋንታው የሚባል ወንድሜ ለኦስሎ ነዋሪዎች ከላከው ጾዳቤ ውስጥ "ለነገሩ ብዙ ኢትዮጵያዊ ሰው ለብዙ ነገር ስሜት የለውም" የሚል ትችት አገኘሁ:: ይህ በቀላሉ የማይታለፍ ጉዳይ እንደሆነና ውይይት እንደሚያስፈልገው በማመን ጸሃፊውን ቀጥለው በተዘረዘሩት ጥያቄዎች ዙሪያ ልምዱንና  እውቀቱን እንዲያካፍለን ተማጸንኩት:: 
  •  ሰው ስሜት የለውም ስንል ምን ማለታችን ነው?
  • የስሜት አለመኖር ምክንያቱና መንስዔው ምንድን ነው?
  • የስሜት አለመኖር የሚያስከትለው ጉዳት ወይም ጣጣ ምንድን ነው? 
  • ስሜት-አልባነትን እንዴት ማጥፋት ወይም መቀነስ ይቻላል? 
  • ስሜት-አልባነትን ለማጥፋት ወይም ለመቀነስ በሚደረግ ትግል ዋና ተዋንያን እነማን ናቸው?

የስሜት ያለህ! 

አቶ  ፋንታውም "የኢትዮጵያዊ ስራና ጥልቅ ስሜት አቅም" በሚል ርዕስ ይበል የሚያሰኝ ትንታኔ አቀረበ:: ስሜትን በሁለት ከፍሎ አብራራ:: ሃሳባዊ ስሜት "ከልባችን ለመውደድና በአእምሮአችን ለመረዳት በዙሪያችን በሚከሰቱ ነገሮች ላይ የምናሳየው ጥልቅ ፍላጎትና የምናደርገው ግንኙነት ነው"
 (http://www.ethiopiawakeup.net/maindr/passion):: ስሜት በልብ ወይም በአእምሮ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በሥራ እንደሚገለጥም ምሳሌ እያነሳ አብራርቷል:: የስሜት አለመኖር የሚያስከትለውን መዘዝም ከእድገትና ለውጥ ካለመኖር አኳያ አጠር አድርጎ  አንስቷል:: 

እኔም ፋንታው ባነሳቸው ባብዛኞች ሃሳቦች እስማማለሁ:: በዚህ ጽሁፍ አገባብ ስሜት ማለት በአካባቢያችንና በአገራችን ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮችን በነቃ አእምሮ ተከታትሎና መርምሮ የራስን ግንዛቤ መውሰድ ከዚያም የሚገባውን አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሆነም እስማማለሁ:: በስብሰባዎችና የውይይትመድረኮች መሳተፍ: የፖለቲካ ወይም የሲቪል ተቋማትን መምራት ወይም አባል መሆን: የራሱና የሌላ ሰው መብት ሲጣስ መቃወም: እድገትና ለውጥ በሚያመጡ ፕሮጄክቶች መሳተፍ ወዘተ አገራዊ ፖለቲካዊ ስሜት የሚገለጥባቸው መንገዶች ናቸው:: 

ምናልባት ጥያቄ ቢኖረኝ ስሜት በሌለው ኢትዮጵያዊ ብዛት ላይ ነው:: እንደ ፋንታው አመለካከት ከሆነ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በቂ ስሜት የለውም:: ይህ ቁጥር እንዴት ታወቀ? አገር ቤት ያለው ወይስ ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ነው ስሜት የሌለው? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥናትና ምርምር ያስፈልጋል::  

ዳሩ ግን ከምናየውና ከምንሰማው መገመት አይከብድም:: ከአምስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሚኖርባት አዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቶ የሚወጣው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያዘጋጇቸው ስብሰባዎች የሚገኘው ህዝብ ከበቂና ከተጠበቀው በታች ነው:: ምክንያቱ ደግሞ መንግስትን ከመደገፍ ወይም የጭቆና አለመኖር ሊሆን እንደማይችል ለማንም ግልጽ ነው:: በውጭ አገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን በዘመናዊ ማህበራዊ የመገናኛ ብዙኃን ስለአገራቸው የሚጽፉና የሚያነቡ ጥቂቱ ናቸው:: ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በሚመለከት የውይይትና ክርክር መድረኮች ተዘጋጅተው የሚሳተፉት ጥቂቶች ናቸው:: በሰላማዊ ሰልፍ የሚሳተፉትም እንዲሁ:: በአንጻሩ ደግሞ የሙዚቃ ምሽት ወይም የስፖርት ዝግጅቶች እንዲሁም ሰርግና ልደት በሚደረግበት ጊዜ ያረፍዳል እንጅ የተጠራው ሁሉ ሽክ ብሎ ይገኛል:: ያልተጋበዘውም ባለመጋበዙ ይሰማዋል:: 

ለመሆኑ አገራዊ ፖለቲካዊ ስሜት የሚጎድለን ለምንድን ነው? ይህ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሌ የሚያነሱት ጥያቄ ነው:: በዝግጅቶቻቸው በቂ ሰው አይገኝምና:: ይህ ጥያቄ ባንድም በሌላም መንገድ ቢነሳም አጥጋቢ መልስ አላገኘም:: አንዳንዶች የዚህ ሁሉ ችግር ህዝቡ ያለው ፍርሃት እንደሆነ ተናግረዋል:: ሌሎች ደግሞ ይህ ዝምታ የኢትዮጵያ ህዝብ የትዕግስቱ መለኪያ እንደሆነ ጽፈዋል:: ነገር ግን እነዚህ ምክንያቶች ችግሩን በፍጹም አይገልጹትም:: የሁሉም ሰው ምክንያቶች ሊሆኑም አይችሉም:: የተጠናከረ ውይይት ቢካሄድ ይህን ችግር መቅረፍ እንደሚቻል በማመን በዚህ ጽሁፍና በተከታታይ ጽሁፎች አገራዊ ጉዳዮችን በአንክሮ እንዳንከታተልና በሚገባ እንዳንሳተፍ የሚያደርጉ መንስኤዎችንና ምክንያቶችን በዝርዝር ለማየት እሞክራለሁ::      

መንስኤዎችና ምክንያቶች   

ለአገራዊ ስሜት አለመኖር መንስኤዎችን ከምክንያቶች ለመለየት የተደራጀ ጥናትና ምርምር ያስፈልጋል:: በዚህ ጽሁፍ ግን ሁለቱን አንድ ላይ አድርጌ አቀርባለሁ:: ይህን ማድረጌም የጽሁፌን ዓላማ ከመምታት አያግደኝም:: ይልቁንም አላስፈላጊ ክብደትን ያስወግድልኛል ብዬ አምናለሁ:: 

በቂ ስሜት ያለመኖር መንስኤዎቹና ምክንያቶቹ ከሰው ሰው ከጊዜ ጊዜ ሊለያዩ ይችላሉ:: ቢሆንም ግን ዋና ሊባሉ የሚችሉትን መገመቱ አይከብድም:: ከማኅበራዊ ህይወቴ ጋር በተያያዘ ከተመለከትኳቸውና ከታዘብኳቸው የስሜት አልባነት መንስኤዎች ወይም ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ዋናዎቹ ናቸው:: 

ዝንባሌና ፍላጎት

ሰዎች በተፈጥሮአቸውና በህይወት ተሞክሮአቸው የተነሳ ለተወሰኑ ጉዳዮች ብቻ ልዩ ፍላጎትና  ዝንባሌ አላቸው::  በመሆኑም ለአገራዊ ጉዳዮች ምንም ደንታ የሌላቸው ሰዎች ይኖራሉ:: ሌላው ቀርቶ በግል ህይወታቸውም ሲበደሉና መብታቸው ሲጣስም አይገዳቸውም እጅጉን የሚያሳስባቸውና መስዋዕት የሚከፍሉለት ብቸኛው ጉዳይ ሥራቸውና የቤታቸው ነገር ነው:: የተሰማሩበትንም ሥራ የሚመለከቱት ለአገር በሚያደርገው አስተዋጽዖ ጭምር ሳይሆን የደመዎዛቸው መገኛና ማግኛ መሳሪያ በመሆኑ ብቻ ነው:: 

በዚህ ምድብ ውስጥ በርካታ በትምህርት ብዙም ያልገፉ ሰዎች: ቴክኒሽያኖች: መሃንዲሶች: ፕሮፌሰሮች: ዶክተሮች እና ሌላ ትልቅ ማዕረግና ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎችም ይገኛሉ:: እነዚህን ሰዎች አይደለም በማስታወቂያ በአማላጅም ቢሆን ወደ አገራዊ ውይይት መድረክ ማምጣት ከባድ ነው:: ያለው አማራጭ እነዚህ ሰዎች በተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ላቅ ያሉና ተጨማሪ አገልግሎቶችን እንዲያበረክቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ብቻ ነው:: በፖለቲካዊ ውይይት ወይም መድረክ እንዲሳተፉ ማስገደድ ከአለት ላይ ውኃ ለማፍለቅ እንደመሞከር ነው:: በአገራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መሳተፍ የሁሉም ሰው ምርጫ ሊሆን አይችልም::  

የአቅም ጉዳይ 

ቀላል የማይባሉ ሰዎች ደግሞ በአገራዊ ጉዳዮች ለመሳተፍ እምቅ ኃይል ቢኖራቸውም ለራሳቸውና ለሌሎች ሰዎች ያላቸው የተሳሳተ ግምት አስተዋጽዖ እንዳያደርጉ ያደርጋቸዋል:: ራሳቸውን ዝቅ አርገው ስለሚመለከቱ ወጣ ብለው ለመታየት አይፈልጉም:: ውይይቶች በሚካሄዱባቸው ጊዜ ጥሩ ሃሳቦች ቢኖራቸውም   ለመጠየቅ ያመነታሉ:: አልፎ አልፎም ሃሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ:: ከብዙ ሰዎች የሚያበረታታ ምላሽ ካላገኙ በሰው እንደተጠሉና እንደተናቁ በመገመት ራሳቸውን ያስጨንቃሉ:: ከሰዎች የሚያገኙት ግምት አበረታች ስለማይሆን ተሳትፎአቸውን ለመግታት ለራሳቸው ቃል ይገባሉ:: አገራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ አስተዋጽዖ ለማድረግ ይህ ነው የሚባል አቅም እንደሌላቸው ራሳቸውን ያሳምናሉ:: በመሆኑም ቀስ በቀስ  በታዳሚነት ከሚገኙባቸው መድረኮች ይርቃሉ:: 

ሌሎቹ ደግሞ ከላይ ከተጠቀሱት ሰዎች ተቃራኒ ናቸው:: በእውነትም ጥሩ ሃሳብና ተሞክሮ ቢኖራቸውም የሌላውን ለመቀበል ይቸገራሉ:: ሁሌ የራሳቸው ሃሳብ ብቻ እንዲያሸንፍ ይከራከራሉ:: ይህ ሳይሆን ቢቀር ስብሰባው ወይም ውይይቱ እርባና እንደሌለውና ችሎታ በሌላቸው ሰዎች እንደሚመራ ያወራሉ:: ያስወራሉ:: እንደምንም ብለው ለሚቀጥለው ጊዜ የመሪነቱን ቦታ ለመያዝ ይሯሯጣሉ:: ካልተሳካላቸውም ሙከራቸውን እንደ ሽንፈት ቆጥረው ከሱታፌ ይታቀባሉ:: ከተሳካላቸው መድረኩ ወይም ፓርቲው የግል ንብረታቸው እስኪመስላቸው ይቆጣጠሩታል:: ሥልጣን እንዲለቁ ወይም እንዲያካፍሉ ወይም የሌላውንም ሰው አስተዋጽዖ ቦታ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ያኮርፋሉ:: ያደረጉት አስተዋጽዖ የተረሳባቸው ይመስላቸዋል:: የመገለል ስሜት ያጠቃቸውና እንቅስቃሴአቸውን ቀስ በቀስ ያቋርጡና በትዝታ መኖር ይጀምራሉ:: ከቻሉም ሲሳተፉባቸው የነበሩትን መድረኮች ወይም ድርጅቶች ይኮንናሉ:: ለማዳከምም ይጥራሉ:: አንዳንዶችም የራሳቸውን ተስፈንጣሪ ድርጅቶች ይፈጥራሉ:: የባሰባቸው ደግሞ የመንግስት ደጋፊና አባል በመሆን ብቸኝነታቸውን ለመቋቋምና ተፈላጊነታቸውን ለመጨመር ይጥራሉ::

                  ////////// ይቀጥላል ////////


1 comment:

  1. I was recommended this web site by my cousin. I am not sure
    whether this post is written by him as no one else know such detailed about my difficulty.
    You are wonderful! Thanks!

    ReplyDelete

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...