Friday 5 February 2016

ስደት ክርስትናና ኢትዮጵያዊነት ክፍል 2

ለተገፉት መቆም  

ክርስትና በግል የሚኖሩት ሕይወት አይደለም:: «እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት ለባልንጀራው እንጅ»  (ፊል 2: 4) እንዳለ ለሰው ልጅ ሁሉ ይልቁንስ ለኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ደኅንነት ማሰብና የምንችለውን ማድረግ መንፈሳዊ ግዴታችን ነው:: በመካከለኛው ምሥራቅ በአፍሪካና በአውሮፓም ሳይቀር ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በመከራ ላይ ናቸው:: የሰው ልጅ የገጠመው ከባድ የተባለ መከራ ሁሉ የደረሰባቸው አሉ:: በየእስር ቤቶች የሚጉላሉና ጠያቂ ያጡ ብዙዎች ናቸው:: በደላሎችና በአሸባሪዎች እጅ የወደቁት ብዙ ናቸው:: የሰውነት ክፍሎቻቸው ለሽያጭ የቀረቡባቸው አሉ:: በሃይማኖታቸው ምክንያት መስዋዕትነትን የተቀበሉም አሉ:: ባጠቃላይ በሞትና በህይወት መካከል የሚገኙ ወገኖቻችን ብዙዎች ናቸው:: በአገራችን በኢትዮጵያም ቢሆን ያለአግባብ በእስር የሚማቅቁ የሚገደሉ የሚሳደዱ አሉ:: በረሃብ የሚሰቃየው ወገናችንም በሚሊዮን የሚቆጠር ሆኗል:: ሙስናና ዘረኝነት ህዝባችንን ተፈታትኗል:: ለእነዚህ ሁሉ ወገኖች ኢትዮጵያዊያን ሊደርሱላቸው ይገባል:: በጸሎት ከማሳሰብ ጀምሮ ገንዘብና አስፈላጊ ቁሳቁስ በመላክ እንታደጋቸው::


በስደት የነበሩት አስቴርና መርዶኪዎስ እስራኤላውያን በግፍ እንዲገደሉ የሚያዘውን የንጉሡን አዋጅ በሌላ አዋጅ እንዲሻር ያደረጉት እግዚአብሔር የሰጣቸውን ጥበብ ተጠቅመው የግድያ አዋጅ እንዲዘጋጅ ያደረገውን የጄኔራሉን የሐማን መጥፎ ሥራ በማጋለጥ ነው:: እኛም በኢትዮጵያዊያን ላይ ግፍ የሚያደርሱባቸውን አካላት በሙሉ ለመንግስታትና ለመገናኛ ብዙኅን ሁሉ ሳንታክት እናጋልጥ:: ልባችንና ኅሊናችን ሁል ጊዜ ከተገፉት ጋር ይሁን:: ሊቀ ነቢያት ሙሴ «የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ:: ከግብጽም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ከእግዚአብሔር ህዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ» (ዕብ 11:24 - 26) :: እኛም በምንችለው ሁሉ ወገኖቻችንን እንርዳ:: ይህም ቢያቅተን እንኳን በጸሎታችን ሁል ጊዜ ከተገፉት ጋር እንሁን:: የልባችንን መሻት የሚመለከት እግዚአብሔር መከራውን ያስታግስላቸዋልና:: 

ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ መስራት  

በስደት ያለን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት በየዕለቱ ከሚከናወነው አገልግሎት በተጨማሪ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ሥራዎችን መሥራት አለብን:: ለአብነትም አባቶቻችን ያደረጉትን ተጋድሎ ማየቱ ጥሩ ነው:: አባታችን ኖኅ በእግዚአብሔር ጥበብ እጅግ ግዙፍ የሆነ መርከብ በመሥራት ፍጥረታትን ከጥፋት ውኃ አድኗል:: የሕይወት ዑደት እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል:: በአህዛብ ጦርነት የተነሳ ክፉኛ የፈረሰውን የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንዲሁም የተጎዳውን የህዝቡን ሥነ ልቡና እንደገና የጠገኑትና ያነቃቁት ዕዝራና ንህምያ ናቸው:: የመካከለኛው ምሥራቅና የአፍሪካን ህዝብ ካጋጠመው ጽኑ ረሃብ የታደገው የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ነው:: ለ400 ዘመን ሰውን በማያፍሩ እግዚአብሔርን በማይፈሩ ፈርዖኖች ሲገዛ የኖረውን የእስራኤል ህዝብ ነጻ ያወጣው ሙሴ ነው:: ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ እንድትመጣ ያደረገ ምኒልክ ቀዳማዊ ነው:: ጌታ የተሰቀለበት ግማደ መስቀልና አልባሳቱ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ያደረገ ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት ነው:: ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሆኑትን ኢየሩሳሌም ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ገንብተው እስከ አሁን ድረስ ለትውልድ ያቆዩ አባቶቻችን ናቸው:: እነዚህ ሥራዎች ለትውልድ የተረፉና የሚተርፉ ናቸው::  

እኛም በበኩላችን ለታላላቅ ሥራዎች መነሳሳት አለብን:: አብያተ ክርስቲያናትን በባዕድ አገር መትከል አለብን:: ይህም ለልጆቻችን ሕይወት ወሳኝ ከመሆኑም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያናችን በውጭው ዓለም በቋሚነት የምትስፋፋበትን ሁኔታ ያመቻቻል:: አገራችንንም በበጎ መልኩ ያስተዋውቃል:: እንዲሁም ከምእመናን አስተዋጽዖ በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን ራሷን የምትችልበትን የገንዘብ አቅም የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶችንና ተቋማትን ማቋቋም አለብን:: በተጨማሪም በውጭ አገራት ላሉ ህዝቦች ሃይማኖታችንን በቋሚነት ለማስተማር የምንችልበትን መንገድ በኅብረት መቀየስ አለብን:: በስደት የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ችግሩንና ፈተናውን ለማጥናትና ተጨባጭ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማቅረብ ይቻል ዘንድ የጥናትና ምርምር ተቋም ይኑረን:: የቤተ ክርስቲያናችንንና የአገራችንን ታሪክና ባህል የሚዘክር ቋሚ ቤተ መዘክር ይኑረን:: ይህ ሁሉ ታላላቅ ሥራ ሊሠራ የሚችለው በፍጹም እምነትና ኅብረት ነው:: መጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ የማይቻል ነገር እንደሌለ እንመን:: «የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል እኛ ባሪያዎቹ ተነስተን እንሠራለን» (ነህ 2: 20) እንበል:: በተለያዩ የሙያ መስኮች ዕውቀትና ጥበብ ያላቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት እንሰብስባቸው በየሙያቸውና ፍላጎታቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዲያገለግሉ እንጋብዛቸው:: እናበረታታቸው:: የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔ በማይረቡ ጥቃቅን ጉዳዮች ጊዜውንና ኃይሉን ከማባከን ይልቅ ትውልድ ተሻጋሪ ሥራዎችን ማነሳሳትና ማስተባበር ይጠበቅበታል::   

ኢትዮጵያዊ መልካችንን አለመቀየር  

አገርን መውደድ እግዚአብሔርን መውደድ ነው:: ክርስቲያኖች አይደለም ለትውልድ አገራቸው በስደት ላሉባቸው አገራትና ለዓለም ሁሉ ሰላምንና አንድነትን የሚፈልጉ ናቸው:: በስደት ያለን ክርስቲያኖች ይልቁንም አገራችን ኢትዮጵያን በልባችን ይዘን እንዞራለን:: ደስታም ሆነ ችግር ሲገጥመን ኢትዮጵያ መኖር ይገባን እንደነበር እናስባለን:: ቤታችን አለባበሳችን አነጋገራችንና አመጋገባችን ኢትዮጵያዊነትን ይሰብካል:: ይህ ሁሉ ለአገራችን ያለንን ፍቅር ይገልፃልና የሚበረታታ ነው::

እንዲሁም ለጉብኝት ወይም ለእረፍት ኢትዮጵያ ስንሄድም ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ሥራ መሥራት አለብን እንጅ እንደ ዝንጉዎች በስደት ለፍተን ግረን ያገኘነውን ገንዘብ ለታይታና ለማማለያ አንጠቀምበት:: እንደ አንዳንዶችም ከእረፍታችን መልስ ስለቆሙ ሕንፃዎችና ስለተዘረጉ አስፋልት መንገዶች ብቻ አናውራ:: ያለአግባብ ስለታሰሩና ስለሚሳደዱ በሚሊዮን ስለሚቆጠሩ ረሃብተኞች ስለተንሰራፋው ዘረኝነትና ሙስና እንዲሁም ፈተና ላይ ስለወደቀው አንድነታችን ባጠቃላይ ስለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሕይወትና አኗኗርም በግልጽ እንመስክር:: ባጠቃላይ ኢትዮጵያን በተመለከተ የምናደርገው ግምገማና ንግግር በገሃድ የሚደረገውንና የሆነውን ያካተተ ይሁን:: ይህን ካደረግን ነው ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን የሚያሰኘን እንጅ ስማችን ብቻ አይደለም::             


ሌላው መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ቢኖር አገራችን ተመልሰን ለመኖር ማሰብ ነው:: ምንም እንኳን በምዕራቡ ዓለም ለመኖር ለጊዜው የተመቸ መስሎ ቢታይም የትውልድ አገር ውስጥ ሊገኝ የሚችለውን ርካታና ደስታ ሊተካ ግን አይችልም:: የውጭው ዓለም ሃይማኖትን እየረሳ ሴኩላሪዝምን መርሁ እያደረገ በመሄድ ላይ ነው:: የግለሰብ መብት የሃይማኖት ተቋማት ካሏቸው ህግጋትና ሥርዓታት ይልቅ ቅድሚያ እየተሰጠው ነው:: ይባስ ብሎም ዲያብሎስ ከፍጥረታት መካከል አንዱ ስለሆነ በእግዚአብሔር ላይ ማመጽ መብቱ ነው ብለው የሚከራከሩ እየተነሱ ተከታይም እያገኙ ነው:: ከሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ስለፈጣሪ መኖር የሚያትቱ ሃሳቦች እንዲወጡ እየተደረገ ነው:: በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ዲያብሎስን የሚያስተዋውቁና የሚዘክሩ ትምህርት ቤቶችና ኃውልቶች እንዲገነቡ እየተጠየቀ ነው:: የተጀመሩም አሉ:: ግብረ ሰዶማዊነት መብት ሆኗል:: አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ በመድኃኒትነት ስም እየተበረታታ ነው:: ትዳርን ያለ በቂ ምክንያት ማፍረስ እጅግ የቀለለ ጉዳይ ሆኗል:: ፍችን የሚያበረታቱ ጥቅማ ጥቅሞችም በመንግስታት ተዘጋጅተዋል:: ከነዚህና ከሌሎችም ጉዳዮች የተነሳ ውጭ አገር እስከ ህይወተ እልፈት ድረስ መቆየት ለክርስቲያኖች የከበደ ይሆናል:: በተለይም ለልጆችና ለወጣቶች! በመሆኑም በትውልድ አገራችን በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮች ሁሉ ተወግደው መኖር እንችል ዘንድ የሁል ጊዜ ጸሎታችን መሆን አለበት:: አገራችን ለዜጎቿ ሁሉ ምቹ መኖሪያ እንድትሆን የበኩላችንን አስተዋጽዖም ማድረግ አለብን:: ይህ ከሆነ ነብዩ ኤርምያስ «በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጣልን  (ኤር 13: 23) እንዳለው ኢትዮጵያዊ መልካችንን አለወጥንም ማለት ነው::


ማሳሰቢያ ይህ ጽሑፍ በኦስሎ  የቅዱስ ገብርኤልና አቡነ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምትዘጋጀው ኅዳገ ተዋሕዶ  መጽሔት ላይ የወጣ ነው! 

በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ ስለወቅታዊ ጉዳዮች ትንታኔ ይቀርባል!


No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...