Friday 29 January 2016

ስደት ክርስትናና ኢትዮጵያዊነት

ስደት ለምን?

ስደት ከትውልድ አገር በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ወጥቶ በሌላ አገር ለረጅምም ሆነ ለአጭር ጊዜ መኖርን ያመለክታል:: በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ስደተኞች አዳምና ሔዋን ናቸው:: ምንም እንኳን እግዚአብሔር ከምድር አፈር ቢፈጥራቸውም አገራቸው በምሥራቅ በኩል ባለች በኤዶም ገነት ይሆን ዘንድ ፈቃዱ ሆነ:: አዳም በተፈጠረ 40 ቀኑ ሔዋን በተፈጠረች 80 ቀኗ ኤዶም ገነት ገቡ:: በዚያም ሰባት ዓመት ከአንድ ወር 17 ቀን በደስታ ከኖሩ በኋላ ጠላት ዲያብሎስ በእባብ ተመስሎ አሳታቸው:: የታዛዥነት ምልክት የሆነችውን ያልተፈቀደላቸውን ዕፀ በለስን ስለበሉ እግዚአብሔር ከገነት አስወጣቸው:: በተፈጠሩባት ምድር በድካም እንዲኖሩ ተፈረደባቸው:: ስደት ወደ ምድር:: አዳምና ሔዋን እግዚአብሔርን በማሳዘናቸውና ገነትን በማጣታቸው ሐዘን ላይ እያሉ ክፉ ልብ የነበረው (1ዮሐ 3: 11 - 12) ልጃቸው ቃየን በቅናት ተነሳስቶ ወንድሙን አቤልን ገደለው:: በእግዚአብሔር አምሳያ የተፈጠረውን ሰውን በመግደል የመጀመሪያው ሰው ሆነ:: ከቤተሰቡና ከእግዚአብሔር ቁጣ የሚያመልጥ መስሎት ኖድ ወደተባለ አገር ተሰደደ:: እድሜ ልኩን ተቅበዝባዥ ሆነ:: ባጠቃላይ ሲታይ የዚህ ቤተሰብ አባላት ማለትም አዳም ሔዋንና ቃየን መራር ለሆነ ስደትና መከራ የተዳረጉት በራሳቸው ኃጢአት የተነሳ  ነው::


ሌሎችም የእግዚአብሔር ሰዎች በራሳቸው ፈቃድ ወይም ከሌሎች በሚደርስባቸው ተጽዕኖ የተነሳ የተሰደዱ አሉ:: ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት» (ዘፍ 1:23) በተባለው አምላካዊ ቃል መሠረት ሰዎች እየበዙ ሲመጡ የተሻለ ቦታ ለማግኘት በራሳቸው ምርጫ ወደ ምድር ሁሉ ተሰደዱ:: እንዲሁም የጦር ምርኮኛ ሆነው የተሰደዱ በሌላ አገር መጻተኛ ሆነው የኖሩም አሉ:: ለምሳሌ ዳንኤል አናንያ አዛርያ ምሳኤል ዕዝራ ነህምያ አስቴር መርዶኪዎስ:: የብዙዎች አባት የሆነው አብርሐም ጣዖት ከሚፈበረክባትና ከሚመለክባት ከአገሩ ከካራን ወደ ከነዓን እንዲሰደድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ:: እሱም አምላኩ የተናገረውን በሙሉ እምነት በመቀበል ወደ ከነዓን ተሰደደ:: የይስሃቅ ልጅ ያዕቆብ ከወንድሙ ከዔሳው ብኩርናን ገዛ:: አባቱን በማታለል በረከትን ተቀበለ:: በዚህም የተነሳ ዔሳው እንደሚገድለው ባወቀ ጊዜ አገሩን ትቶ አጎቱ ላባ ወደሚኖርበት ወደ ካራን አገር ተሰደደ:: በዚያም ሃያ ዓመት ለላባ ተገዛ:: ተመልሶም ወደከነዓን ሄደ:: በዚያም ብዙ ከኖረ በኋላ በረሃብ የተነሳ በስተእርጅናው ወደ ግብጽ ወረደ::

12 የያዕቆብ ልጆች ውስጥ አንዱ የሆነው ዮሴፍ ወንድሞቹ በሚያየው ራእይና ከአባቱ በሚያገኘው ምርቃት በመቅናት ለነጋዴዎች ሸጡት:: በግብጽ መጻተኛ ሆኖ ኖረ:: እግዚአብሔር አብሮት ስለነበር ከፈርዖን ሞገስንና ትልቅ ሥልጣንን አገኘ:: በኋላም እስራኤላውያን ወገኖቹ በአገራቸው በተነሳው ጽኑ ረሃብ ምክንያት ወደ ግብጽ ወረዱ:: ዮሴፍም የሰውን ልጅ ከረሃብ ታደገ:: እስራኤላውያን በግብጽ እየበዙ ሄዱ:: ዮሴፍን የማያውቅ ፈርዖን ተነሳ:: በባርነት 400 ዘመን ተገዙ:: እግዚአብሔር መከራቸውን ተመልክቶ በሙሴ አማካኝነት ወደ አገራቸው ከነዓን እንዲመለሱ አደረገ::      

በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ህጻናት እንዲገደሉ በሚያዝዘው የንጉሥ ሄሮድስ የጥፋት አዋጅ የተነሳ ወደ ኢትዮጵያና ግብጽ ተሰደዋል:: ይህ ስደታቸውም ፈተና ሲገጥመን ለጊዜው ካለንበት ቦታ መሰደድ እንዳለብን ያስተምረናል:: ከጌታችን ስቅለት በኋላም የወቅቱ የሮሜ ባለሥልጣናት ሐዋርያትንና ሌሎችንም ክርስቲያኖች እንዲሁ አሳደዋል:: ዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱትም ሃይማኖታቸውን በነጻነት መኖር ስላልቻሉ ነው:: ባጠቃላይ ሲታይ እስከ 4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ክርስቲያኖች በሃይማኖታቸው የተነሳ በስደት ለመኖር ተገደዋል::   

ኢትዮጵያዊያን አባቶችም ቅድስት አገር እየሩሳሌምን ለመሳለም አገራቸውን ትተው ተሰደዋል:: በዚያም የራሳችንን አብያተ ክርስቲያናት ተክለዋል:: ለትውልድ አስተላልፈዋል:: ከደርግ ዘመን ጀምሮ ግን ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ቅድስት አገራቸውን ኢትዮጵያን ትተው በምድር ሁሉ እየተበተኑ ይገኛሉ:: የሃይማኖት አባቶች የመንግስት ባለሥልጣናት አዛውንቶች ወጣቶችና ጎልማሶች እንዲሁም ህጻናት ሳይቀሩ ዋላ የውኃን ምንጭ አብዝቶ እንደሚናፍቅ ስደትን የሚመኙ ሆነዋል:: የስደቱ ምክንያትም ልዩ ልዩ ነው:: እንደ አዳም ሔዋንና ቃየን በጥፋታቸው የሚሰደዱ አሉ:: ጦርነትን ሸሽተው የተሰደዱም አሉ:: እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ድንግል ማርያም አረጋዊው ዮሴፍና አብርሐም በሃይማኖት ምክንያት የሚሰደዱም አሉ:: እንደ ያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ወገኖቻቸው ባደረጉባቸው ግፍ ምክንያት የተሰደዱ ሞልተዋል:: የሮሜ ባለሥልጣናት ቀደምት ክርስቲያኖችን እንዳሳደዱ የኢትዮጵያ መንግስታትም ኢትዮጵያዊያንን በግፍ አሰድደዋል:: በርግጥ ቀጥታዊ የሆነ ተጽዕኖ ሳይደረግባቸው ወይም መከራ ሳያገኛቸው በራሳቸው ተነሳሽነት የሚሰደዱም አሉ:: 

ያም ሆነ ይህ የስደት ሁሉ ዋና መንስኤ በአገር ቤት በተመቸ ሁኔታ መኖር አለመቻል ነው:: ብዙዎች በስደታቸው ወቅት የሚደርስባቸው መከራ ከሰው ኅሊና በላይ ነው:: በበረሃና በውኆች የቀሩ ውድ ወገኖቻችን ብዙዎች ናቸው:: አካላቸው ጎድሎ ጤናቸው ታውኮ ያሉም አሉ:: የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ለማግኘት መንግስታትን ደጅ የሚጠኑም አሉ::

ከመከራ የተረፉት ወይም በተሻለ ሁኔታ ከአገር የወጡት በያሉባቸው አገራት ሃይማኖታቸውን አልረሱም:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመላው ዓለም በማቋቋም ራሳቸውንና ልጆቻቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ:: ዳሩ ግን የውጭው ዓለም ሃይማኖትን እየረሳ ሰብአዊነትን እያጠበቀ በመምጣቱ የተነሳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ቀጥታዊና ተዘዋዋሪ ጫናዎችና ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል:: ኢትዮጵያዊያን በያሉባቸው አገራት እንዴት ማንነታቸውን መጠበቅና መኖር እንዳለባቸው የሚጠቁም ትምህርት ከማንኛውም ጊዜ በላይ አሁን ያስፈልጋል::

የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ስደት ክርስትናንና ኢትዮጵያዊነትን እንዴት በአንድ ላይ አጣምሮ መኖርና መያዝ እንደሚቻል ባጭሩ ማሳየት ነው:: ይህ ጽሑፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ዓበይት የስደት ታሪኮች መሠረት በማድረግ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመን በስደት ዘመኑ እንዴት በእግዚአብሔርና በሰው ፊት መመላለስ እንዳለበት ያመላክታል:: ምእመናን ቀጥለው የተዘረዘሩትንና ሌሎችንም መልካም ምግባራት አጥብቀው መያዝና ለትውልድም ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል::  

እግዚአብሔርን ማስቀደም

በስደት ሕይወት ብዙ ስኬት ሊባሉ የሚችሉ ጉዳዮች አሉ:: ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የሚያሰጋው ሰው ሌላ አገር በጤናና በሰላም መድረስ መቻሉ በራሱ ስኬት ነው:: ብዙዎች በሲዖል በሚመሰሉ እስር ቤቶች መከራቸውን እያዩ  ነውና:: ሌሎችም በየበረሃውና በውኆች የሞቱ አሉና:: በተሰደዱበት አገር የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ማግኘት ቤት መሥራት ወገንን በሚቻለው ሁሉ መርዳት ትዳር መያዝ እንዲሁም ልጆችን ማፍራትም ስኬት ሊባሉ ይችላሉ:: ይልቁንም በባዕድ አገር ቤተ ክርስቲያን ማቋቋም ትልቅ ስኬት ነው::

እኒህና ሌሎችም መልካም ነገሮችን ያደረግናቸው በኛ ጥበብና ጥረት ብቻ እንደሆነ ካመንን ከእግዚአብሔር ጋር እንጣላለን:: ሁሉንም መልካም ነገር ያከናወነልን እግዚአብሔር መሆኑን ማመን ያስፈልጋል:: ዮሴፍ በግብጽ በስደት እያለ «እግዚአብሔር በመከራዬ አገር አፈራኝ» (ዘፍ 41:52) በማለት መከራ በበዛበት የባዕድ አገር ሥልጣንና ጥሩ ቤተሰብ ስላገኘ ምሥጋናውን አቅርቧል:: በስደት ዓለም «አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ:: እርሱንም አምልክ:: ከእርሱም ተጣበቅ:: ዓይኖችሁ ያዩትን እነዚህን ታላላቆች የሚያስፈሩትንም ነገሮች ያደረገልህ እርሱ ክብርህ ነው» (ዘዳ 10: 20 - 21) እንዳለ በባዕድ አገር እግዚአብሔር ሞገስ ዕውቀት ጤናና ክንድ ሆኖን ሕይወታችን እጅግ ተቀይሯል:: ለጊዜውም ቢሆን ያልተሳካልን ካለንም እግዚአብሔርን መማጸንና መታገስ ያስፈልጋል::

ባጠቃላይ በስደት ሆነን መልካሙ ሁሉ እንዲሆንልን አምላካችንን እየለመንን መጣርና በሚገኘውም ስኬት እርሱን ማመስገን ያስፈልጋል:: እስራኤልን ከግብጽ ባርነት በእግዚአብሔር ፈቃድና እርዳታ ነጻ አውጥቶ የመራ ሙሴ በበረሃ ሳሉ እግዚአብሔርን አሳዘነ:: እስራኤላውያን የሚጠጡት ውኃ ባጡ ጊዜ ሙሴና አሮን በመገናኛ ድንኳኑ ሰግደው እግዚአብሔርን ተማጸኑ:: እግዚአብሔርም ሙሴ በበትሩ አለቱን ሲመታው ውኃ እንደሚያገኙ ተናገረው:: ሙሴም እንዲሁ አደረገ:: ውኃም ከአለቱ ፈለቀ:: ዳሩ ግን ሙሴና አሮን ይህን ያደረገው እግዚአብሔር እንደሆነ ለህዝቡ አልተናገሩም:: ምሥጋናም አላቀረቡም:: እግዚአብሔርም «በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይህንን ጉባኤ ይዛችሁ አትገቡም» አላቸው (ዘኍ 20: 12):: በዚህም ምክንያት ሙሴ ዘመኑን ሙሉ የናፈቃትን የተስፋይቱን አገር ከነዓንን ፈስጋ ከተባለው ተራራ ላይ ወጥቶ በዐይኑ ብቻ አይቶ በዚያው አረፈ:: እኛም ሁሉን ለሚያደርግ ለእግዚአብሔር ምሥጋና የማናቀርብ ከሆነ ካሰብነው አንደርስም:: እንደ ሙሴ ምንም ብንለፋም ኢትዮጵያን ዳግም ሳናይ ከመንገድ እንቀራለን::                                                                                                                                                                                                                            በተማርነው መጽናት

በስደት ዓለም ስንኖር እምነትንና ምግባርን የሚፈታተኑ ብዙ ነገሮች በሥራ ቦታ በጓደኛ በጎረቤት እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ይገጥሙናል:: ጥንቃቄ ካልተደረገ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ቀስ በቀስ እንድንተው ያደርጋሉ:: ለጾም ለጸሎት ለምጽዋት ለትዳር ለአገልግሎትና ለምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ለቅዱሳን ያለንን ፍቅር ቀስ በቀስ ይሸረሽሩብናል:: ባጠቃላይ ለማንነታችን ጥንቃቄ እንዳናደርግ በአንድም በሌላም መንገድ ተጽዕኖ ያደርጉብናል:: ይልቁንስ ሆን ብለው በእቅድና በመርህ ደረጃ ሃይማኖታችን እንዲዳከም የሚንቀሳቀሱ አካላትም አሉ:: ከቁሳዊ ማለትም ሴኩላሪዝም ፍልስፍና ጀምሮ ፈጣሪ የለም ብለው እስከሚያምኑ ሰዎች ጫናው ቀላል አይደለም:: በዚሁም ላይ ሁሉም ነገር ከግለሰብ መብት አኳያ ብቻ በሚተነተንበት ዓለም ክርስትና አይደለም ድጋፍ ሊያገኝ እንደ እንቅፋት ይቆጠራል:: በመሆኑም ግብረ ሰዶምን ጽንስ ማስወረድን አደንዛዥ ዕፅ መጠቀምንና ሌሎችንም መጥፎ ድርጊቶች ቤተ ክርስቲያናችን ስትቃወም እንደ አክራሪና የሰው መብት ረጋጭ ትቆጠራለች::

ከዚያም መለስ ሌሎች የእምነት ድርጅቶች ኦርቶዶክስ ተዋህዶን በመልካም አይመለከቷትም:: በተለያዩ መንገዶች የማዘናጋት እንዲሁም አባላትን የመንጠቅ ደባ እየሠሩ ይገኛሉ:: ይባስ ብሎ ኦርቶዶክስ አማኝ መስለው የምእመናንን ኅሊናና ልቡና የሚከፍል ለጥርጣሬ ከዚያም ለክህደት የሚያመቻች ትምህርት በየቤቱ እየዞሩ የሚያቀርቡም አሉ:: በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መታደስ አለባት ብለው የተነሱ ግለሰቦች ዶግማዋንና ቀኖናዋን በማምታታት ከውስጥ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ:: በተለይም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንንና በያሬዳዊ ዜማ ላይ የዘመቱ አሉ:: 


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ወጣቶችና አባቶች ሀሰተኞችን ከእውነተኞች መለየት በመቻላቸው ተቃውሞ ማሰማት ጀምረዋል:: ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት:: በስሜት ሳይሆን በማስተዋል አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የሚሠሩትን ሥራ በተመለከተ መረጃና ማስረጃ ሰብስበን ለሚመለከተው የቤተ ክርስቲያን አካል ማቅረብ ይገባናል:: አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድም ክትትል እናድርግ:: ኃጢአተኛ መገሰጽ አለበት:: ወርቅን የሚወዱም መነቀል አለባቸው:: መናፍቃንም በትምህርትና በንስሃ መመለስ ካልፈለጉ መወገዝ አለባቸው:: ይህ የሚሆነው ምእመናን በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ የሚደረጉ ማናቸውንም ጉዳዮች በአንክሮ ሲከታተሉና ያገባኛል 
በሚል መንፈስ ዘብ ሲቆሙ ብቻ ነው:: 

ባጠቃላይ «በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ:: ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች እያሳቱና እየሳቱ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ:: አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር:: ከማን እንደተማርከው ታውቃለህና» (2ጢሞ 3: 12 - 15) እንዳለው ሃይማኖታችንን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከዚያም ከቅዱሳን ጠንቅቀን በተረዳነው መሠረት በጥንቃቄ እንያዝ:: ማንም በምንም ነገር እንዳያታልለን ሁል ጊዜ በማስተዋል እንጓዝ:: ይህም ሲባል የማይመስሉንን ሁሉ ማግለልና መጥላት አለብን ማለት አይደለም:: አብረናቸው በሰላም እየኖርንን የራሳችን የሆነውን ሁሉ እንጠብቅ ማለት እንጅ::       

ልጆቻችንን ማስተማር

በስደት ዓለም የሚወለዱ ልጆች ዙሪያውን በእንክርዳድ እንደተከበበ ስንዴ ይቆጠራሉ:: ትኩረታቸውን የሚስቡ አያሌ ጉዳዮች በየዕለቱ ይገጥሟቸዋል:: ከጓደኛ ከጎረቤት ከትምህርት ቤትና ከማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኅን የሚቀስሟቸው ልምዶችና ትምህርቶች በቀላሉ ሊቀየሩ የሚችሉ አይደሉም:: ወላጆችና ቤተ ክርስቲያን ልጆችን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ስለኢትዮጵያዊነትና ስለ ሃይማኖታችን በሚገባቸው መልኩ ማስተማር አለባቸው:: የሰው ልጆች ስላሏቸው ልዩነቶችና አንድነቶችም ማስተማር በሥነ ልቡና ጠንካራ እንዲሆኑ ያደርጋል:: ዳሩ ግን የሚሰጣቸው ትምህርትና ምክር ምግባር ተኮር መሆን አለበት:: ልጆችን ስለኢትዮጵያ ለማስተማር ራሳችን ስለኢትዮጵያ ስናነብ ስንጽፍ ስንወያይ መመልከት አለባቸው:: ውብ የሆኑትን ታሪኮች እያጎላን ደካማ ጎናችንንም መደበቅ የለብንም:: ሁሉም አገር የራሱ ታሪክና ድክመትም እንዳለው ስንነግራቸው የእኛ እጅግ የተለየ ሆኖ አይታያቸውም:: እንዲሁም ስለቤተ ክርስቲያን ለማስተማር ልጆችን ቤተ ክርስቲያን ይዞ መሄድ ማገልገል እንዲሁም የሚከናወኑትን አገልግሎቶች በሚገባቸው ግን ትክክል በሆነ መልኩ ማስረዳት ተገቢ ነው::

ትምህርቱ ግን በሁሉም ቦታና ጊዜ እንዳስፈላጊነቱ መቀጠል ይኖርበታል:: ልጆች የተለያዩ ጉዳዮችን በተመለከተ ጥያቄ መጠየቅ ስለሚወዱ ከሃይማኖታችንና ከአገራችን ታሪክና ሁኔታ አኳያ አግባብ ያለው መልስ መስጠት አለብን::   «እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ:: ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው:: በቤትህም ስትቀመጥ በመንገድም ስትሄድ ስትተኛም ስትነሳም አጫውቷቸው:: እርሷንም እንዲሰጣቸው እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር እንደ ሰማይ ዘመን በምድር ላይ ዘመናችሁ የልጆቻችሁም ዘመን ይረዝም ዘንድ በቤትህ መቃኖችና በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው» (ዘዳ 11: 18) እንደተባልን ለልጆቻችን ያለመታከት ቃለ እግዚአብሔርን የማሳወቅ መንፈሳዊ ግዴታ አለብን:: በሚገባ ብናስተምራቸው የራሳችንና የልጆቻችን እድሜ እንደሚረዝም ጥቅሱ ያስረዳል:: ልጆቻችን ከመጥፎ ልምድና ባህል ርቀው ለቤተሰብና ለእግዚአብሔር ታዛዥ እንዲሆኑ አገራቸውንም እንዲወዱና እንዲጠቅሙ ያላሰለሰ ሥራ መሠራት አለበት:: በባዕድ አገር ያደገው ሙሴ ለእስራኤላውያንና እግዚአብሔርን ለሚያመልኩ ሰዎች ሁሉ ስለተገፉት በመቆም አርአያ ሊሆን የቻለው እናቱና እህቱ ስለአገሩ ስለእስራኤልና ስለአምላኩ ስለእግዚአብሔር ከሕፃንነቱ ጀምረው ስላስተማሩትና ምሳሌ ሆነውም ስላሳዩት ነው::

በአገልግሎት መሳተፍ

ክርስትና ለራስ ብቻ የሚሮጡት ሕይወት አይደለም:: ምእመናን ከካህናት አባቶች በመማርና መመሪያ በመቀበል በልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፎች መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል:: ቅዱስ ጳውሎስ «እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን... አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ” (ሮሜ 12: 7) እንዳለ ምእመናን ባላቸው ችሎታ ሁሉ ማገልገል አለባቸው:: ብዙዎች አገልግሎት ሲባል ቅዱስ ወንጌልን መስበክና መዘመር ብቻ ይመስላቸዋል:: ዳሩ ግን ምእመናን ባላቸው ሙያ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል::

በቤተ ክርስቲያናችን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ደንብ /ማለትም ቃለ ዓዋዲ/ መሠረት በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ክፍል የመንፈሳዊ ትምህርት ክፍል የካህናት አገልግሎት ክፍል የሰንበት /ቤት ክፍል የእቅድና ልማት ክፍል የምግባረ ሠናይ /በጐ አድራገት/ ክፍል የሕግና ሥነ ሥርዓት ክፍል የንብረት የዕቃ ግምጃ ቤትና የታሪካዊ ቅርስ ክፍል የሒሳብ ክፍል የገንዘብ ቤት የቁጥጥር ክፍል የሕንፃ ሥራ እድሳትና ጥገና ክፍል  የስታቲስቲክስ ክፍል እና ሌሎችም የአገልግሎት ዘርፎች አሉ:: በመሆኑም ምእመናን በክፍሎች ሁሉ ታቅፈው ቤተ ክርስቲያናቸውን ከዘመናዊ ትምህርት ተቋማት በቀሰሙት ዕውቀታቸው ማገልገል አለባቸው:: ቤተ ክርስቲያን በምህንድስና፣ በህክምና፣ በትምህርት፣ በሕግ ፣በሕዝብ አስተዳደርና ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በኮምፒዩተር ሳይንስ፣ በጥናትና ምርምር፣ በሂሳብ ሥራ በመሳሰሉት የዕውቀት ዘርፎች ሁሉ ማገልገል የሚችሉ ምእመናን ትፈልጋለች::


ይህም በቤተ ክርስቲያናችን ሕግ አጽንዖት ተሰጥቶታል:: ለምሳሌ በቃለ ዓዋዲ አንቀጽ 59 (7) ላይ «ምእመናንም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን በማይመለከቱ በማንኛቸውም የሥራ መስኮች እየተሰማሩ የመረጡትን የአገልግሎት ድርሻ በነጻ ፈቃዳቸውና በትርፍ ጊዜያቸው የሚገባቸውንና የሚፈለግባቸውን አገልግሎት ማበርከት ክርስቲያናዊ መብታቸውና ግዴታቸው ነው» ይላል:: እንዲሁም ቃለ ዓዋዲ አንቀጽ 61 (2) ላይ «የሰበካ ምእመናን በገንዘብ አስተዋጽኦ፣ በአስተዳደር፣ በትምህርት፣ በልማትና በማኅበራዊ ኑሮ አገልግሎት በጠቅላላው በሀብት፣ በዕውቀትና በጉልበት በመረዳት በሰበካው ልዩ ልዩ የክፍል ሥራዎች ውስጥ በመሳተፍ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ክርስቲያናዊ ግዴታቸው ነው» በማለት ምእመናን በችሎታቸው ማገልገል ግዴታ እንደሆነ በማያሻማ መልኩ ያብራራል፡፡ 

በመሆኑም ምእመናን የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔን በማማከር በሚፈልጉት የሥራ ዘርፍ ማገልገል አለባቸው:: ምእመናን በማስተዋል እየተወያዩ በችሎታቸው የሚሳተፉ ከሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን በማጠናከር ልጆቿን ከተኩላዎች ትጠብቃለች:: የማያምኑትንም ለማስተማር የላቀ አቅምና ተሰሚነት ይኖራታል:: አገልጋዮችም ዘላለማዊ በረከትን ያገኛሉ!

                                                     ክፍል 2  ሳምንት ይቀጥላል!

ማሳሰቢያ ይህ ጽሑፍ በኦስሎ  የቅዱስ ገብርኤልና አቡነ  ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያን በምትዘጋጀው ኅዳገ ተዋሕዶ  መጽሔት ላይ የወጣ ነው!

No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...