Tuesday 12 June 2018

ዶ/ር ዐቢይና ሥር ነቀል ለውጥ በኢትዮጵያ


/ር ዐቢይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ አመለካከቶችን በማንጸባረቅ ላይ ይገኛሉ ጠቅለል ባለ ዳሩ ግን ጥናታዊ ባልሆነ መልኩ ሲታይ ዶ/ሩ ከሚናገሯቸውና ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች አንጻር ኢትዮጵያውያንን በአመለካከታቸው በአራት ምድብ ማስቀመጥ ይቻላል የመጀመሪያዎቹ  ለውጡን በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው የሚወዱ ዶ/ሩንም እንደ መሲህ የሚመለከቱ ናቸው የዶ/ሩን ንግግሮችና ሥራዎች በመዘርዘር ራሳቸውን በአውንታዊ መልኩ አሳምነው ሌሎችንም ለማሳመን ይጥራሉ ከአሁን በኋላ አስተማማኝና ዘላቂ ለውጥ የሚመጣው በጦር ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ በመታገል እንደሆነ ዐቢይን ተምሳሌት አድርገው ያቀርባሉ በቅርቡ ኢትዮጵያ የገቡ የተቃዋሚ አመራር አባላትን ጨምሮ ቀላል ሊባል የማይችል ሕዝብ በዚህ የአመለካከት ጎራ ሊመደብ ይችላል      


ከዚህ በአንጻሩ የቆሙ ኢትዮጵያውያን አሉ ዶ/ር ዐቢይ በኢሕአዴግ በተለይም በሕወሓት ስውር ሥራ አገዛዙን በሥልጣን ለማቆየት የተዘጋጁ ማዘናጊያ እንደሆኑ ያምናሉ ለማሳመንም ይጥራሉ ከዚህ በፊት ኢሕአዴግ እና ወይም ሕወሓት በሥልጣናቸው ለመቆየት ያደረጓቸውን ታክቲኮች በማስረጃነት ያቀርባሉ በመሆኑም ዶ/ሩ የሚናገሯቸው እንዲሁም የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ሁሉ ማታለያና ጊዜ መግዣ ሕዝባዊ ትግሉንም ማቀዝቀዣ እንደሆኑ አድርገው ያቀርባሉ ይህን አመለካከት አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ጸሐፊዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲያስተጋቡ ይታያል             

ሌላኛው አመለካከት ከላይ የተጠቀሱ ሁለቱን አመለካከቶች ያዳቀለ ይመስላል ማለትም ዶ/ር ዐቢይ እስካሁን ያደረጓቸውና የተናገሯቸው መልካም እንደሆኑ ያምናሉ ምስጋናቸውንም ለዶ/ሩ ያቀርባሉ ይሁንና የተጀመረው ለውጥ ጥልቀት የሌለውና አስተማማኝ እንዳልሆነ ይሞግታሉ እስካሁን ድረስ ወሳኝ የሆኑ የመንግስት መዋቅሮች በአምባ ገነንና ሙሰኛ መሪዎች እንደተያዙ የብሔር ግጭቶችና መፈናቅሎች እንዳሉ በመጥቀስ የሚኒስትሩን ሥራ ውሱንነት ያብራራሉ ሥር ነቀል ለውጥም በቶሎ እንዲመጣ ይፈልጋሉ        

አራተኛው አይነት አመለካከት ደግሞ ከላይ ከተዘረዘሩት ሦስቱ አመለካከቶች ውጭ የሆነ ነው ለውጡን በአይነትና በጥራት ለመገምገም እንዳልቻሉ የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን አሉ የዶ/ሩን አካሄድና አንደምታ ለማጤን በቂ ጊዜ እንደሌለ የሚናገሩ ናቸው ማለትም ተጨማሪ ለውጦችን እስኪያዩ ድረስ የዶ/ሩን ንግግርም ሆነ ሥራ ከማድነቅም ከማውገዝም የሚቆጠቡ ናቸው       

የመጀመሪያውን አመለካከት ከያዙት ኢትዮጵያውያን በስተቀር ሦስቱን አመለካከቶች የያዙት የሚጋሩት ወሳኝ ነጥብ ያለ ይመስላል /ር ዐቢይ ከነዚህ ኢትዮጵያውያን ሙሉ ድጋፍና ማበረታቻ ለማግኘት ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት እንዳለባቸው ያመላክታል ሥር ነቀል ለውጥ ማለት ምን እንደሆነ ግን የጠራ አተያይ ያለ አይመስልም መገለጫዎቹ ግን የኢሕአዴግን እና ወይም የሕወሓትን ባለሥልጣናት ከሥራ ጠራርጎ ማባረርና በፈጸሟቸው በደሎች ፍርድ ቤት ማቆምን ታሳቢ ያደረገ ይመስላል የኢሕአዴግ እና ወይም የሕወሓት የሆነን ነገር ሁሉ ሰርዞና ባለሥልጣናትንም ተበቅሎ በአዲስ ጉዞ መጀመርንም የሚያመላክት ትርጉም ያለው አመለካከት ይንጸባረቃል ይህ አይነት ለውጥ ሥር ነቀል ሳይሆን ቂም በቀል ነው!

ወሳኙ ጥያቄም ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው ይህ አይነት ሥር ነቀል ለውጥ (አንዳንዶችም መሠረታዊ ለውጥ የሚል ሐረግ ይጠቀማሉ) ማድረግ ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ይቻላል? ለነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልሶች ላይገኙ ይችል ይሆናል ታሪካችንና አሁን ያለንበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ ካስገባን ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት አይቻልም ቢቻልም ባክኖ እንደማይቀር ማረጋገጫ የለንም ለዚህም ታሪካችን ምስክራችን ሊሆን ይችላል    
ከዚህ በፊት የተካሄዱት ሥር ነቀል ለውጦች ወይም አብዮቶች በጥሎ ማለፍ በጥቃትና በበቀል ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ደርግ የጃንሆይን መንግስት የለውጡ አካል ለማድረግ ጥቂት ሞከረና ወደ እብሪት ተሸጋገረ። በደመ ነፍስ ንጹሐን ኢትዮጵያውያንን ሳይቀር በጅምላ ረሸነ። የደርግን ጥሩነት ለማሳየት የጃንሆይ የነበሩትን ሁሉንም ሥራዎች ማውገዝን ተያያዘው። በዚያም የተነሳ ቀላል የማይባል የሕዝብ ድጋፍ አጣ። አይወድቁ አወዳደቅ ወደቀ። ያሁኑ መንግስትም 27 ዓመት ሙሉ ደርግን በማውገዝ የራሱን ንጽህናና ልማታዊነት ለማሳየት ይጥራል። ከዚያም አልፎ ስህተቱን የሚነግሩትን ወገኖች ነፍጠኛና ያለፈው ሥርዓት ናፋቂ በማለት ያሸማቅቃል። ባጠቃላይ በዚህ መንግስት ዐይን ሲታይ የደርግ የነበረው ሁሉና  ስለኢትዮጵያ የሚናገር የተወገዘ ነው። የደርግ ደጋፊዎች የነበሩም እንደ ዜጋ አይቆጠሩም። ይህ አስተሳሰብ ግን ለመንግስት ኪሳራ እንጅ ትርፍ አላስገኘለትም።         

ያሁኑ ሕዝባዊ ትግል ግን ፍጹም የተለየ መሆን አለበት። ለእኔ ሥር ነቀል ለውጥ ዘላቂ ሰላም እውነተኛ ዴሞክራሲና ነጻነት ማምጣት ነው ይህ አይነት ለውጥ የሚመጣው በጥበብ በሆደ ሰፊነትና በትዕግስት ነው! ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ሰላም እውነተኛ ዴሞክራሲና ነጻነት እንዳይኖር የጣረውና የሚጥረው መንግስትና ደጋፊዎቹም መካተት አለባቸው። ይህም የታሰበው ከዚህ በፊት በሌላ ጽሑፍ እንደገለጽኩት ስለአራት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው። አንደኛ በመንግስት መዋቅርና በሽርክና የሚሠሩ በሀሳብና በሞራልም የሚደግፉ ምናልባትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። እነሱም የለውጡ አካል ቢሆኑ ትግሉ ዓላማውን በቶሎ ያሳካል። ሁለተኛ መንግስትና ደጋፊዎቹም ቢሆኑ እውነተኛ ነጻነት ፈላጊዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ዶር ዐቢይና ለማ እንዲሁም በቅርብ ለውጡን ደግፈው ብቅ ያሉት ባለሥልጣናት  ለዚህ ነጥብ ሕያው ምስክር ናቸው ሦስተኛ በብድርና በእርዳታ እስከ አፍንጫው ድረስ የታጠቀውን መንግስትን የለውጡ አካል ማድረግ የይቅርታና የርህራሄ መንፈስን ስለሚያንጸባርቅ ትግሉ ሰላማዊ ይሆናል። አላስፈላጊ የሕይወት መስዋዕትነትንና የንብረት ውድመትን ያስቀራል። አራተኛ መንግስትንና ደጋፊዎችን የለውጡ አካል ማድረግ ለነገው ትውልድ የማይረሳ ትምህርትን ይሰጣል። ለውጥ የሚመጣው በማጥቃትና በማግለል ሳይሆን በዳይንም ተበዳይንም በፍትሐዊነት በማሳተፍ እንደሆነ ትውልዱ ይረዳል። እንደ ባህልም ይይዘዋል።       
    
ዳሩ ግን መንግስትና ደጋፊዎቹ የለወጡ አካል ሊሆኑ የሚችሉት ለሥልጣን ከመስገብገብና ከስሜት ወጥተው ለምስኪኑ ዜጋ ይልቁንስ ለራሳቸውም ማሰብ ሲጀምሩ ነው። የተገነቡ ሕንፃዎችንና መንገዶችን እንዲሁም የተመሰረቱ ብሄር ተኮር ፓርቲዎችን እያነሳሱ መመፃደቅ የትም እንደማያደርስ መታወቅ ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ያለባትን የገንዘብ እዳ የህዝቡን ተጨባጭ የዕለት ተዕለት ሕይወትየእስር ቤቶችንና የታሳሪዎችን ብዛትና የደረሰባቸውን የሞራልና የአካል ጉዳቶች የተሰደዱትንና በሂደቱም የሞቱትን ወዘተ በማስታወስ የማዘንና የመጸጸት ከዚያም ለውጥ ለማምጣት የማመን አዝማሚያ መታየት አለበት። ጊዜው የፈለጉትን ገሎና ዘርፎ ውጭ አገር በሰላም መኖር የሚቻልበት እንዳልሆነ ማሰብም ይጠቅማል። መንግስትና ደጋፊዎቹ በዚህ ወሳኝ የለውጥ ሂደት ቢሳተፉ ታሪክና ልጆቻቸው በበጎ እንደሚያነሷቸው እስካሁንም ለተሠሩ ስህተቶችና ግፎች ማርከሻ ወይም ንስሃ እንደሚሆን ማወቅ አለባቸው። ዛሬና ነገ እውነተኛና ዘላቂ ለውጥ ለማድረግ ያሰበን አካል ሕዝቡ በትናንት በደሉ ሊፈልገው አይችልምና! ስለዚህ ባለቀ ሰዓት መንግስት የማይረሳ እንቁ ታሪክ የመሥራት እድሉ አለው።   
    
መንግስት ተሳትፎውን በልዩ  ልዩ  መንገዶች  መግለጽ መጀመር ይችላል። ወደ እውነተኛ ብሔራዊ ውይይት እርቅና ስምምነት ከዚያም ምርጫ የሚያደርሰውን ጉዞ በገለልተኝነት የሚያስተባብር ልዩ ብሄራዊ ግብረ ኃይል ቶሎ እንዲቋቋም መፍቀድ በሱም መሳተፍ ሃሳብን ያለምንም ፍርሃት መግለጽ እንዲቻል ማድረግ በትግሉ ምክንያት የታሰሩትን ያለቅድመ ሁኔታ መፍታት የመንግስት መገናኛ ብዙኅን ገለልተኛ ማድረግ ሌሎችም የመንግስት ተቋማት ነጻና ገለልተኛ እንዲሆኑ ማድረግ ባጠቃላይ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሕግ ከለላ ማድረግ የሚቋቋመው ግብረ ኃይል ዝግጅት ሲጨርስ ሥልጣንን በሰላም ማስረከብ ወዘተ ሊሆን ይችላል። በዚህ መልኩ የሚካሄድ ለውጥ እውነተኛ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ይሆናል

/ር ዐቢይ ይህንና የመሳሰለውን እንዲያደርጉ ማበረታታትና መጠየቅ የዜግነት ግዴታን መወጣት ነው እርሳቸው መሪ በሆኑባቸው አጭር ጊዜያት ኢትዮጵያዊነት በውጭው ዓለማት ሳይቀር እንደገና በመልካም ጅምሮች መነሳት ጀምሯል ብዙዎች ከእስር ተፈተዋል ሌቦች የሰረቁትን ገንዘብ እንዲመልሱ ያም ካልሆነ በሕግ እንደሚጠየቁ በጠራ ቋንቋ ተነግሯቸዋል ብሔርን ጠገግ ያደረጉ ዘረኞችና ጠባቦች ተገስጸዋል  ያለ አግባብ ከሥራቸውና ከማዕረጋቸው የተባረሩ ክብራቸው ጥቅማቸው ተመልሷል የሚነኩ የማይመስሉ ጨካኝ መሪዎች ከሥልጣናቸው ተነስተዋል ለውጡን ለማፈን የሚጥሩ የአገዛዙ አካላት ከመጥፎ  ሥራቸው እንዲታቀቡ በይፋ ተነግሯል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነስቷል ወዘተረፈ ይህም  ማለት የተከሰቱ ወይም የሚከሰቱ ችግሮች የሉም ማለት አይደለም አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ባጭር ጊዜ እያንዳንዷን ክስተት የመቆጣጠር አቅም የለውም  ሓላፊነትም የለበትም ትልቁን ሥዕል በመመልከት የራስን አበርክቶ ወይም ድርሻ መጨመር እጅግ ወሳኝነት አለው እርሳቸው የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው! ተመሳሳይ ጥረት ከኢትዮጵያውያን ሁሉ ይፈለጋል   
      
ፎቶው ከኢንተርኔት የተወሰደ

ወሳኝና አስተማማኝ ለውጥ እንዲመጣ ሁላችንም እንደ ግለሰብም እንደ ድርጅትም የምናበረክተው ይኖራል /ር ዐቢይና ድርጅታቸው እንዲያመጡት የምንመኘውን ሥር ነቀል ለውጥ በድርጅታችን በግል ኑሯችን መጀመር አለብን /ሩ እንዳሉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በትካዜና በቁዛሜ የሚያመጡት ለውጥ አይኖርም ወቅቱን አጢኖ የግራና የቀኝ ፖለቲካ ሳይሉ ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ያስቡ ያድርጉም  የሃይማኖት ተቋማትም የሙስናና የዘረኝነት የአፈናም መገለጫ ማማ ከመሆን መውጣት አለባቸው /ር ዐቢይም የሃይማኖት መሪዎች ሙስናንና ዘረኝነትን በመዋጋት ለመንግስት የሞራል ልዕልና ተምሳሌት እንዲሆኑ ጠይቀዋል የሃይማኖት አማኞችም የተቋማቸውን አሠራርና የመሪዎቻቸውን ስብእና ወይም ምግባር መመርመር አለባቸው ፍትሕን ቅንነትን አንድነትን ግልጽነትን ተጠያቂነትን በሃይማኖት ተቋሞቻቸው ማስፈን አለባቸው ግለሰቦችም በግልና በቤተሰብ ሕይወት ዙሪያ እውነትን ነጻነትን አንድነትን ተጠያቂነትን ይለማመዱ ይህ አይነት የአስተሳሰብና የባሕርይ ለውጥ መንግስትን አስጨንቆ በመያዝ እንዲለወጥ ማስገደድ ይችላል ዘረኛና ሙሰኛ አምባ ገነንም የሆነ ዜጋና ድርጅት መንግስት ከዘረኝንትና ከሙሰኛ ከአምባ ገነንነትም እንዲወጣ የመጠየቅ የሞራል ልዕልና አይኖረውም

ከዚህ ውጭ ዶ/ር ዐቢይ እስካሁን ያደረጉት አስተዋጽዖ በቀላሉ አይታይም እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ምሳሌያዊ ገለጻ ኢትዮጵያ በተደናበረና በተደናገጠ የባቡር ነጂ አማካኝነት በፍጥነት ወደገደል ለመግባት እየተጓዘች ነበር በእኔ እይታ ያን ፈሪና አላስተዋይ ነጂ ዶ/ር ዐቢይ ተክተውታል እርሳቸውም በፍጥነት ማቆሚያውን ማለትም ብሬኩን በመያዝ የባቡሩን ፍጥነት ገተውታል ተሳፋሪዎች ገደል ከመግባት ተርፈዋል /ሩም የባቡሩን አቅጣጫ ቀይረው እየነዱ ነው ባቡሩም በየፌርማታው ይቆማል ጥቂቶች እየወረዱ ብዙዎችም እየተሳፈሩ ባቡሩ ጉዞውን ቀጥሏል ባቡሩ ውስጥ የሚሠሩ ብዙዎቹ ሠራተኞች የአዲሱን ነጂ ውሳኔና ድፍረት አድንቀው ከተሳፋሪዎች ጋር አብረው መጓዝን መርጠዋል ጥያቄው የባቡሩ መዳረሻ ነው! ያን የሚወስነው ደግሞ የባቡሩ ነጂ ብቻ ሳይሆን ተሳፋሪዎችም ናቸው ተሳፋሪዎች ቶሎ ብለው በአንድ ድምጽ የትና እንዴት መጓዝ እንዳለባቸው ለነጂው መንገር ያንንም ማስፈጸም ይገባቸዋል ከዚህ ውጭ በባቡሩ ሳይሳፈሩ የባቡሩን ፍጥነትና መድረሻ የመወሰን እድል አይኖርም የእርስዎስ ድርሻ ምንድን ነው?
       

No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...