Friday 22 June 2018

የሁለቱ ሲኖዶሶች ፈተና


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕወሓት- መሩ መንግስት ከመጣ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመጋፈጥ ላይ ትገኛለች። ኦርቶዶክስንና አማራን በተለየ መልኩ ለማዳከም ከተቻለም ለማጥፋት የትግሉ ዓላማ አድርጎ የተነሳው ቡድን ሥልጣን በያዘ ማግስት ያለምንም ፍርሃትና ይሉኝታ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ገብቶ ማወክ ጀመረ። ባለሥልጣናቱ ኦርቶዶክስነትንና አማራነትን ብሎም ኢትዮጵያዊነትን በመድረክ በሚዲያ መደብደብ በገሃድም ማፈን ጀመሩ።    


ይህ ቤተ ክርስቲያኗን የማዳከም ሴራ የአሁኑ ፓስተር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር በነበሩት በአቶ ታምራት ላይኔ ፊርማ በይፋ ጸደቀ። ማለትም 4ኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ የተሰጣቸውን ታላቅ ሓላፊነት እንደሚወጡ በደብዳቤም በቃልም ቢያስታውቁም ከሥልጣናቸው በግድ እንዲነሱ ተደረገ። 



                                          ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ

እርሳቸው እያሉም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ 5ኛው ፓትርያርክ ተብለው ተሾሙ። እርሳቸውም በካህናትና በምእመናን ተቀባይነት ሳይኖራቸው መንግስትን ምርኩዛቸው መመኪያቸው አድርገው ኖሩ። ድንገትም አረፉ። ይህን ተከትሎ በጉልበት የተባረሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ወደቀደመ ሥልጣናቸው እንደሚመለሱ ተስፋ ተሰንቆ ነበር። የእርቅም ጉባኤ ተካሂዶ ሳይሳካ ቀረ። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀጣዩ ፓትርያርክ ሆነውም ተሾሙ።      

የቤተ ክርስቲያን ቀኖና እንደተጣሰ መቅረት የለበትም በማለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስም በስደት ዘመናቸው በአሜሪካን አገር ቅዱስ ሲኖዶስ አቋቋሙ። ጳጳሳት ተሾሙ። አሕጉረ ስብከቶች ተቋቋሙ። ይህን ተከትሎም ሁለቱ ሲኖዶሶች ተወጋገዙ። ሁለት ተፎካካሪ ሲኖዶሶች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ስም በአካል ገዝፈው በስም ተስተካክለው ምእመናንን ተከፋፍለው በማስተዳደር እስካ ዛሬ ደርሰዋል። ይሁንና ቅዱስ ሲኖዶስ እንዴት በማንና መቼ እንደተከፈለ ለበርካታ ዓመታት የተነገረ የተጻፈም ስለሆነ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት አይደለም።

         

                          ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ

ይህ ጽሑፍ በመጀመሪያው ክፍል የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በሁለት ሲኖዶሶች መከፈል ያስከተላቸውን ዐበይት ችግሮች ባጭሩ ይዘረዝራል። ችግሩ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ ያመላክታል። ይህም በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ስር የሁለት ሲኖዶሶች መኖር ያስከተለው ችግር አዘወትሮ ከሚነገረው ወይም ከሚሰማው በላይ መሆኑን እንድንመለከት ሊረዳ ይችላል። የችግሩን ጥልቀት  በሚገባ ተረድተን መፍትሔ እንድንሽት ሊያነሳሳን ይችላል። ሁለተኛውና ዋናው የጽሑፉ ክፍል የሚያተኩረው ለዓመታት የጠፋውን አንድነትና ሰላም ለማምጣት አቅሙ ያላቸውን ባለድርሻዎች በመዘርዘር ላይ ነው። ዓላማውም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለሲኖዶስ አንድ መሆን የበኩላቸውን አበርክቶ እንዲያደርጉ ማስገንዘብ ማነሳሳትም ነው። በመጨረሻም ቶሎ ብሎ እርቅና አንድነት ካልመጣ ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ በአይነታቸውና በይዘታቸው እጅግ ልዩና ከባድ የሆኑ ክስተቶች ሊመጡ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።       

የሲኖዶስ ሁለትነት ያስከተላቸው ችግሮች 

 በእርግጥ አንዳንዶች ሲኖዶስ እንዳልተከፈል፣ እንዳልተሰደደ፣ መሰደድም እንደሌለበት ይከራከራሉ። ይሁንና ይህ አስተሳሰብ ለአንዱ አካል ወገኝተኝነትን ለመግለጽ ካልሆነ በስተቀር እውነትነት የለውም። ለቤተ ክርስቲያኗም በምንም መልኩ የሚጠቅም አይደለም። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስን ጨምሮ በውጭ ያሉ አንጋፋ ሊቃነ ጳጳሳት በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሲኖዶስ አባል ነበሩ። በእርግጥ ጥቂቶች ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስ በመንግስት አሳላጭነት እንዲሁም ጥቅም ባሳወራቸው የቤተ ክህነት ሰዎች ሥልጣናቸውን ሲቀሙ በመስማማት እንደፈረሙ በኋላ ግን አሜሪካ ቅዱስ ሲኖዶስ አብረው እንዳቋቋሙ ይነገራል። 

ይህን ለታሪክና ይህን አድርገዋል ለተባሉ እንተወውና አሁን በሚሊዮኖች ምእመናን የሚተዳደሩባቸው ሁለት ሲኖዶሶች እንዳሉ ማወቁና ማመኑ መፍትሔም መሻቱ ብቻ ነው የሚያዋጣው። ቤተ ክርስቲያኗ በሁለት ሲኖዶሶች መከፈሏ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አስከትሏል። እነዚህ ችግሮች የሁለቱ ሲኖዶሶች አባላት እስካሁን ድረስ እርቅ ባለማውረዳቸው በአንድም በሌላም መልኩ የተከሰቱ ናቸው። ዐበይት የሆኑትን ብቻ እንዲህ ተዘርዝረዋል። 

  • ሲ ኖዶስን አባላትና ተዋሕዶ ሃይማኖትን በሚገባ ለይተው መመልከት ያልቻሉ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ለመቀየር ወይም ፈጽሞ ለመተው ምክንያት አግኝተዋል። ቤተ ክርስቲያን ስለእርቅና ሰላም እያስተማረች በበላይነት የሚመሯት ግን ለዚህ የተመቹ ባለመሆናቸው የብዙዎችን አማኒያን እምነት ተፈታትነዋል። ቤተ ክርስቲያንም እምነትንና ምግባርን ይዛ እንዳላገኟት በመናገር ራሳቸውን ከቤተ ክርስቲያን የለዩ ብዙዎች ናቸው    
  • የቤተ ክርስቲያኗ የሞራል ልእልና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ከፍተኛ ባለሥልጣኖቿ ለይቅርታ፣ ለእርቅና ለሰላም የተገቡ ሆነው ስላልተገኙ ቤተ ክርስቲያኗ በነዚህ እሴቶች ዙሪያ ተሰሚነቷ በእጅጉ ቀንሷል። ሁለቱም ሲኖዶሶች ስለ ይቅርታ፣ እርቅና አንድነት ማስተማር የሚያስችላቸው መንፈሳዊና ሞራላዊ ብቃት ጎድሏቸዋል   
  •  ታላላቁ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለይቅርታ፣ ለአንድነትና ለሰላም ቆራጥ ሆነው አለመገኘታቸው በየአብያተ ክርስቲያኑ ያሉትን አገልጋዮችም በእጅጉ ጎድቷል። ስለይቅርታ፣ አንድነትና ሰላም ለማስተማር ይቅርታ ማድረግ፣ አንድ መሆንና ሰላማዊ ሆኖ መገኘት እንደማያስፈልግ  ከአባቶቻቸው የተማሩ በርካታ አገልጋዮች እየታዩ  ነው። ይህም የአገልጋዮችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ከመጉዳቱ አልፎ  ለምእመናንም መጥፎ አርአያ እየሆነ ነው። የተጣሉ አገልጋዮችንና ምእመናንን ለማስታረቅ አዳጋች ሆኗል 
  • ተሰምቶ የማይታወቅ ገለልተኛ የሚባል ሦስተኛ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ተፈጥሯል 
  • በሦስቱ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደሮች ስር ያሉ አገልጋዮችና ምእመናን በመንፈስም በአካልም ተለያይተዋል። ይህ ችግር በውጭው ዓለም ያሉትን ይመለከታል። በኢትዮጵያው ሲኖዶስ ስር ያሉ አገልጋዮችና ምእመናን በአሜሪካው ሲኖዶስ ስር እንዲሁም በገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ስር ካሉት አገልጋዮችና ምእመናን ጋር አይተባበሩም። አንዱ ለሌላው ስም ሰጥቶ ግንብም አቁሞ  ይኖራል። በኢትዮጵያው ሲኖዶስ ስር ያሉ ወያኔ ደጋፊ ሲባሉ በአሜሪካው ሲኖዶስ ስር ያሉት ደግሞ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ደጋፊ ይባላሉ። ገለልተኞች ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ስም ቢዝነስ የሚሠሩ ሆነው ይሳላሉ። ባጠቃላይ የሲኖዶስ መከፋፈል የአንዲት ሃይማኖት ተከታዮች ከአንድነት ይልቅ ሦስትነትን፣ ከሰላም ይልቅ ጭቅጭቅን፣ መካሰስን፣ ጠብን እንዲመርጡ ምክንያት ሆኗል  
  • አንዲት ቤተ ከርስቲያን ገንብተው በአንድነት ይገለገሉ የነበሩ አማኞች በኢትዮጵያውና በአሜሪካው ሲኖዶስ ስር ከመሆንና ካለመሆን ጋር በተያያዘ ለሁለት ተከፍለው ፍርድ ቤት ቆመዋል። ምእመናን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ያዋጡት ገንዘብ ለጠበቃ ክፍያ ውሏል። ከገንዘቡ ብክነት በተጨማሪ ምዕራባውያን የፍርድ አካላትና ዜጎቻቸው ሃይማኖታችንና ኢትዮጵያዊነታችንን በንቀት እንዲመለከቱ አስተዋጽዖ አድርጓል። ቀድሞ በብዙ ድካም የተገነባው የሃይማኖታችንና የአገራችን መልካም ገጽታ ተበላሽቷል 
  • ልዩ ዓላማ ያላቸው አካላት አጋጣሚውን ተጠቅመውበታል። ክፍፍሉ ለሌቦችና ለዘረኞች ለምግባረ  ብልሹ ሰዎችም መልካም አጋጣሚን ፈጥሮላቸዋል። የቤተ ክርስቲያኒቷን ሹመትና ማዕረግ ይዘው ልብሷንም ለብሰው ድሆች ተቸግረው የሚሰጡትን መባ ለግላቸው ጥቅም ያውላሉ። ሲነቃባቸውም ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ምእመናንን ካህናትን ያፍናሉ፣ ያፈናቅላሉ፣ ያስደበድባሉ። ሃይማኖት  መታደስ አለበት ብለው የሚያምኑም በቤተ ክርስቲያኒቷ መዋቅር ተሰግስገዋል ወዘተረፈ። ይህ ሁሉ አሳፋሪ ሥራ የተከሰተው የሞራልና የመንፈስ ልዕልና ከከፍተኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ስለጎደለ ስለጠፋ ነው    
  • ከላይ በተጠቀሱት ችግሮች የተነሳ ቤተ ክርስቲያኒቱ ልታበረክተው የሚገባት መንፈሳዊና ማኅበራዊ አስተዋጽዖ ተገቷል። ክፍፍሉ፣ ዘረፋው፣ ቅሰጣው፣ ጎሰኝነቱ፣ ወዘተ መንፈሳዊ አገልግሎትን አንቆ  ይዟል። ቤተ ክርስቲያን ለተከታዮቿ በሚገባት መጠን ጥራት ያለው አገልግሎት ማቅረብ ይሳናታል። ለአገራችን ለኢትዮጵያም ይቅር ባይነትን፣ ሰላምን፣ አንድነትን፣ እድገትን ማስተማር  ማሳየትም ተስኗታል። እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስር ዶ/ር ዐቢይ የሲኖዶሶች ክፍፍል በሃይማኖት ሰበብ የዘር ጣጣ እንዳለበት፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከዚህና ከሙስና ወጥተው ለመንግስት አርአያ እንዲሆኑ በተግሳጽም በምክርም መልክ ተናግረዋል    


                                     በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የሚመራው ሲኖዶስ

ለሲኖዶሶች እርቅ ባለድርሻዎች

ቤተ ክርስቲያኗን ከዚህ ሁሉ ውርደት ለመታደግ በርካታ እንቅስሴዎች ተደርገዋል። እርቅና አንድነትን ለማምጣት 1ኛው ዙር የሰላምና የአንድነት ጉባኤ ያካሄደው ጥረት ዓላማው ባይሳካም የሚረሳ አይደለም።  ከዚያ በመለስ ግለሰቦችና ቡድኖች በተለያዩ ጊዜያት ለማስታረቅ ሞክረዋል። አሁን ደግሞ በሁለቱም ሲኖዶሶች እውቅና ተሰጥቶት የሚንቀሳቀስ አስታራቂ ኮሚቴ እንዳለ ከሚዲያ ተሰምቷል። ከሁለቱም ሲኖዶሶች እንዲሁም ከገለልተኝ አብያተ ክርስቲያናት የተወከሉ ካህናትና ምእመናን ያሉበት እንደሆነ ተነግሯል። ከሁለቱም ሲኖዶሶች ውክልና ተሰጥቷቸው በእርቁ የሚሳተፉ ሊቃነ ጳጳሳትም ተመርጠዋል። በሐምሌ ወር 2010 ዓ/ም የእርቁ ጉባኤ እንደሚካሄድም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እርቅ ወርዶ ፍጹም አንድነትና ሰላም እንዲመጣ ግን ድርሻቸውን መወጣት ያለባቸው በርካታ አካላት አሉ። ምንም እንኳን በሁለቱም ወገኖች ያሉ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ትልቁን ድርሻ ቢይዙም ሌሎች ተባባሪ ባለድርሻዎችም አሉ። ከዚህ በፊት የተካሄዱት የእርቅ ሙከራዎች ያልተሳኩት እርቁን የሚያመጡት የሲኖዶሶች ተወካዮች ብቻ እንደሆኑ በመታመኑ ነው።  በወቅቱ ድርሻቸውን መወጣት የነበረባቸው ሌሎች አካላት አልተካተቱም ነበር። ያሁኑ እርቅ ግን ከዚህ አመለካከት ወጥቶ ሌሎች አካላትም የበኩላቸውን ድርሻ  እንዲወጡ ማበረታታት ይኖርበታል። የሲኖዶሶች አንድነት እውን ይሆን ዘንድ ቀጥሎ የተዘረዘሩት አካላት ሚናቸውን በወቅቱና በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።    

                                     በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ የሚመራው ሲኖዶስ

የአስታራቂው ኮሚቴ

እርቅ እንዲወርድ በራሳቸው ፈቃደኝነት ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን መስዋዕት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኮሚቴው አባላት ልዩ ድርሻ ይኖራቸዋል። ከዚህ በፊት ከነበረው ተሞክሮ በመነሳት ኮሚቴው ቀጥለው የተዘረዘሩትን በዋናነት ቢያከናውን ይመረጣል።   
§  የእርቁ ጉዳይ የሚመለከተው ቅዱስ ሲኖዶስን ብቻ ሳይሆን መላው የቤተ ክርስቲያኗ አማኞችን  እንዲሁም ኢትዮጵያውያንንም እንደሆነ ማመንና ሁለቱ ሲኖዶሶች በዚያ ልክ እንዲያስቡበት እንዲዘጋጁም ማድረግ      
§  እርቁ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይካሄድ ዘንድ የሚገፋፋ የምእመናንንና የካህናትን ተማጽኖ መሰብሰብ፣ ለሲኖዶስ አባላትም ቀድሞ መላክ  
§  ምንም እንኳን ለሲኖዶስ መከፈል የመንግስት እጅ ቢኖርም ዞሮ ዞሮ ሙሉ ተጠያቂነቱን የሚወስዱት ሁለት ሲኖዶሶች እንደሆኑ ማመንና እርቅ እንዲወርድ በዚህ ልክ ጫናውን በሲኖዶስ አባላት ላይ ማድረግ
§  በየጊዜው የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ጉዳዩን ለሚከታተሉ ሁሉ ግልጽ ማድረግ። በዚህ መልክ  የሚገኝ መረጃ ጉዳዩ በምን ደረጃና ጥራት እንደተያዘ ያመላክታል። የምእመናንንና የሲኖዶስ አባላትም ድርሻቸውን በየጊዜው እንዲያውቁ አስፈላጊውንም እርምጃ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል። እንዲሁም የአስታራቂው ኮሚቴ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን እንደሚያሰፍን ምልክት ይሆናል
§  ምናልባት በማወቅም ባለማወቅም በእርቁ ጊዜ በተለያዩ ዘዴዎች ጣልቃ ሊገቡ የሚችሉ አካላት ሊኖሩ እንደሚችሉ ቀድሞ መገመት፣ ይህን የሚመክት መመሪያ ማውጣት፣ ይፋ ማድረግ፣ በሥራ ላይም ማዋል
§  ኮሚቴው የእርቁን ውጤት ያለምንም ማሻሻል ወዲያውኑ ለምእመናን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ማሳወቅ     

 ቅዱስ ሲኖዶስ

ዋናው ሓላፊነት ያለባቸውና በመጨረሻም በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ ተጠያቂዎች የሚሆኑት  ሁለት ሲኖዶሶች ናቸው። በመሆኑም ለእርቅ የሚያበቃውን ከፍተኛውን ድርሻ የሚወጡት እነሱ ናቸው።  
§  ለሲኖዶስ ሁለት መሆን መንግስት ትልቅ ሚና ቢኖረውም ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም አለመኖር የመጀመሪያና የመጨረሻ ተጠያቂዎች ሁለቱ ሲኖዶሶች እንደሆኑ ማመን። ሔዋን ውድቀቷን በእባብ፣ አዳም ደግሞ ውድቀቱን በሔዋን ማሳበባቸው ከፍርድ እንዳላዳናቸው ይመለከቷል
§  የቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም (ከምእመናን ሕይወት ጋር የተቆራኘ ስለሆነ) ከሕግና ከቀኖና በላይ እንደሆነ ማመን። ከላይ የተዘረዘሩት ቤተ ክርስቲያን በክፍፍሉ ምክንያት ያጋጠሟት በርካታ ችግሮች ለዚህ አተያይ ማሳያ ናቸው
§  የእርቁ ውይይትና ውጤትም ከትናንት ይልቅ ዛሬንና ነገን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ማድረግ
§  አላስፈላጊና ከባድ ቅድመ ሁኔታዎች ለእርቁ እንዳይቀርቡ ማድረግ። በአስጨናቂ ቅድመ ሁኔታዎች የታጀበ ውይይት የቤተ ክርስቲያንን የይቅርታ አስተምህሮ አያንጸባርቅም
§  ምን ጊዜም ይቅር ብሎ መታረቅ አለመቻል ማለት ከ50 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ምእመናን ይቅር ባይነት፣ አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር እንደማያስፈልጉ በአደባባይ ከማስተማር የበለጠ የከፋ መሆኑን መገንዘብ  
§  እርቅ ከወረደ የአባቶች ክብር፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንደሚመለስ፣ የምእመናን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወት እንደሚያብብና እንደሚያፈራ መገንዘብ    

አብያተ ክርስቲያናትና ማኅበራት
እያንዳንዷ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራትም የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸውበዚህ ስር የሰበካ ጉባኤ፣ የካህናትና መምህራን፣ የምእመናን እንዲሁም የሰንበት ተማሪዎች ድርሻ ወሳኝ ነው። በጋራም ሆነ በተናጥል  ክርስቲያናዊ ግዴታን መወጣት ያስፈልጋል 
  • እርቁ የካህናትና የመምህራን የምእመናን እንዲሁም የሰንበት ተማሪዎችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወት ስለሚነካ ጉዳዩ  ያገባኛል ብሎ ማመን ያስፈልጋል
  • ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሃሳብና ተማጽእኖ ማቅረብ አባቶችን መዳፈር ወይም አቅምን አለማወቅ ሳይሆን ክርስቲያናዊ ግዴታን መወጣት እንደሆነ ማመን  
  • ከአሁን ጀምሮ እርቁ እስኪጠናቀቅ ድረስ ጸሎት መያዝ
  • ስብከቶች፣ ትምህርቶችና መዝሙሮች ሁሉ ስለይቅርታ አንድነት ሰላም እርቅ እንዲያወሱ ማድረግ  
  • ሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ እንዲያወርዱ የሚማጸን፣ የሚያሳስብ፣ የሚያስጠነቅቅም ደብዳቤ ከፊርማ ጋር መላክ 
  • በሁለቱ ሲኖዶሶች ስር የሚገኙ አገልጋዮችና ምእመናን የጋራ ጉባኤ በማዘጋጀት ስለእርቁ መወያየት፣ አቅጣጫም ማስቀመጥ   
  • በሁለቱም ሲኖዶሶች እንዲሁም በገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ስር የሚገኙ ካህናትና ሌሎችም አገልጋዮች ምእመናንም እርቅ አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳየት አንድ ላይ ማስቀደስ፣ መማር፣ እርቅ እንዲመጣ የሚያስተባብር የጋራ ግብረ ኃይል ማቋቋምና ከአስታራቂ ኮሚቴው ጋር ማገናኘት 
  • አስታራቂ ኮሚቴውን በጸሎት በሃሳብ በገንዘብ በሞራል መራዳት  
  • አስታራቂ ኮሚቴው ግልጽነትንና ተጠያቂነትን እንዲያዳብር ማበረታታት  
  • ክፍፍሉን ተጠቅመው የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ ሌቦች፣ ዘረኞች ወዘተ ካሉ ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ መምከር፣ ካልሆነም ሥራቸውን ይፋ ማድረግ     

መንግስት

ከላይ እንደተጠቀሰው መንግስት ጫና በማሳደር 4ኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስን ከሥልጣናቸው አንስቷል። በዚህም ሳይቆጠብ በቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ሁሉ እጁን ሲያስገባ ኖሯል። ካህናት እንኳን መግባት በማይችሉበት የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እነ አቶ አባይ ፀሐዬ እንደፈለጉ ይገባሉ ይወጣሉ። ሊቃነ ጳጳሳትን ያስፈራራሉ ይገስጻሉ። ሌላም ብዙ በደልን በቤተ ክርስቲያን ላይ አድርሰዋል።

/ር ዐቢይ ከተሾሙ በኋላ ደግሞ ነገሮች ሁሉ ተለወጡ። ቤተ ክርስቲያን ሌብነትን፣ ዘረኝነትን ተዋግታ ለመንግስት ምሳሌ እንድትሆን ተነገረ። ሁለቱ ሲኖዶሶችም እንዲታረቁ ዶ/ሩ ወተወቱ። ለመተባበርም ዝግጁ እንደሆኑ አሳወቁ። ይህም ለሁለቱም ሲኖዶሶች መልካም አጋጣሚም ፈተናም ነው። እድል ነው ልዩነታቸውን ትተው ለመታረቅ ከወሰኑ። እርቁ ሳይሰምር ከቀረ ፈተና ነው። መንግስት ድጋፉን ሰጥቶ ሳለ እርቁ ያልሰመረው በሲኖዶሶቹ የሥልጣን ሽኩቻ ዘረኝነትም እንደሆነ በይፋ መሰበኩ አይቀርም። የሆነው ሆኖ መንግስት ለእርቁ ድጋፉን ሊሰጥ አተያዩንም ሊያጤን ይገባዋል
§  4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ሴራ የጠነሰሰ ያስፈጸመም መንግስት እንደሆነ በግልጽ ማመንና ቤተ ክርስቲያኗንም በይፋ ይቅርታ መጠየቅ
§  እርቁን በሞራል በገንዘብም መደገፍ
§  በፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስ ስር ባለው ሲኖዶስ ስር ላሉ ጳጳሳት፣ ካህናት አገልጋዮችና ምእመናን በሙሉ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መጋበዝ፣ የሕግ ከለላም መስጠት
§  ከዚህ በኋላ በምንም መልኩ በቤተ ክርስቲያን ሥራ ወይም ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ማረጋገጫ መስጠ

የፖለቲካና ሲቪክ ድርጅቶች
ከዚህ በፊት እንደታየው በምዕራቡ ዓለም ያሉ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ድርጅቶችም በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል እርቅ እንዳይኖር ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ ሲንቀሳቀሱ ነበር። ኢትዮጵያ ያለው ሲኖዶስ የመንግስት ደጋፊና ተላላኪ እንደሆነ በማመን በብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስ የሚመራው ሲኖዶስ ከነሱ ጋር እንዲያብር በተለያየ መልኩ ውስወሳ ነበር። አሁን ግን ሁኔታዎች ተቀያይረዋል። አንደኛ መንግስት የሕዝብን ፍላጎት ማዳመጥና በሰለጠነ መልኩ መፍትሔ መስጠት ስለጀመረ እርቅ ይበረታታል። ሁለተኛ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ከመንግስት ጋር መወያየት መሥራትም እንደሚችሉ ተነግሯል። በመሆኑም በርካታ ድርጅቶች አቋማቸውን እየፈተሹ ይገኛሉ። ሦስተኛ ሁለቱ ሲኖዶሶች በእርቅ አንድ ከሆኑ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም ለማጽናት በሚደረገ ርብርብ ቤተ ክርስቲያን የላቀ አስተዋጽዖ ማድረግ ትችላለች። በመሆኑም ድርጅቶች በተለያዩ መልኩ ለእርቁ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማድረግ አለባቸው
§  መንግስት በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት እንደሚያምኑት ሁሉ እነሱም በእርቁ ዙሪያም ሆነ በሌላ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት
§  እርቁ አሜሪካን አገር ስለሚካሄድ የአስታራቂ ኮሚቴውን ባስፈለገው ሎጂስቲክስ ሁሉ ማገዝ

 ሚዲያና ጸሐፊዎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት ሊኖሩ የሚችሉት መረጃና ማስረጃ በወቅቱ ሲለቀቁ ብቻ ነው። የሽፍንፍን ሥራ ማን ተጠያቂ መሆን እንዳለበት፣ ማን መመስገን እንዳለበት መለየት እንዳይቻል ያደርጋል። አምባ ገነንነትን ወገኝትነትን ያዳብራል። ይህ ተሰብሮ ግልጽነት መስፈን አለበት። ይህ ደግሞ በሚዲያዎችና በጸሐፍያን ሊያዝ የሚገባ ጉዳይ ነው። ምንም እንኳን አስታራቂ ኮሚቴው በሚፈልግበት ጊዜ መረጃ መልቀቅ ቢችልም ሚዲያዎችና ጸሐፍያን በዜና፣ በትንታኔና በአስተያየት እንዲሁም በቅሬታ መልክ ጉዳዩን በተመለከተ ዝግጅት ሊያቀርቡ ይገባል። ሃሳቦች ተንሸራሽረው እንዲወጡና በእርቁ ወይም በድርድሩ የሚሳተፉ ሁሉ ተጠያቂነትም እንዳለባቸው እንዲያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል።   

ማጠቃለያ

የሲኖዶስ አባላት መስዋእትነት ከፍለው እርቅ የሚያወርዱ ከሆነ ሐዋርያት የመሰረቱት ሲኖዶስ እንደገና ተገኘ ማለት ነው። የአባቶች ክብርና ተሰሚነት ይመለሳል። የምእመናን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወት ይሰምራል። በክፍፍሉ ምክንያት የባዘኑ ነፍሳት ወይም በጎች ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ። ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም በግንባር ቀደምትነት አስተዋጽዖ ለማድረግ የሞራል ልእልና ይኖራታል።

በአንጻሩ ግን በምንም ምክንያት ቢሆን እርቁ ካልተሳካ መዘዙ ብዙ ነው። የምእመናን ሞራልና ሕይወት እጅጉን ይጎዳል። የሚጠፉ በጎች ይበዛሉ። ስለእርቅ፣ አንድነትና ሰላም መስበክ ግብዝነት ይሆናል። ምእመናን ከዚህ ቀውስ ለመውጣት የራሳቸውን እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። የሲኖዶስን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባሉ። የራሳቸውን አስተዳደርም ከመመስረት የሚያግዳቸው የሞራል ተጠያቂነት አይኖርም። ከዚህ በፊት አንዳንዶች እንደጠቆሙት የምእመናን ውክልና ያለው ሕዝባዊ ሲኖዶስ ወይም ቦርድ የማይቋቋምበት ምንም አይነት ምክንያት ላይኖር ይችላል። ይህን አይነት እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ምልክቶች ታይተዋል። ቅዱስ ሲኖዶስ እርቅን አውርዶ ዘረኝነትንና ሌብነትን መዋጋት ስላቃተው ምእመናን የራሳቸውን እርምጃ  ወስደዋል እየወሰዱም ነው። የሰበካ ጉባኤ ቢሮዎችን ማሸግ ተጀምሯል። ምግባረ ብልሹ አስተዳዳሪዎችን በኃይል ማባረር ተጀምሯል። በአስተዳዳሪዎች ላይ ያነጣጠረው ሕዝባዊ አመፅ ቤተ ክህነትንና ቅዱስ ሲኖዶስን የማይጎበኝበት ምንም አይነት ማስተማመኛ የለም።  
ከዚህ በኋላ ሕዝብን የሚገዛው፣ የሚመራውም መልካም ክርስቲያናዊ ሥራ ወይም ምግባር እንጅ ሹመት ወይም ማዕረግ ብቻ እንዳልሆነ በግልጽ እየታየ ነው። የለውጥ ማዕበል ወደ ቤተ ክርስቲያንም ገብቷል። ቤተ ክህነት ማዕበሉን ለጊዜው በኃይል ለመቋቋም እየሞከረች ነው። ይህ ግን የሚያዋጣ አይደለም። ጉዳዩ  ያሳሰበው መንግስትም ቤተ ክርስቲያን ችግሯን ካላስወገደች ጣልቃ እንደሚገባ ደጋግሞ  በአደባባይ እያሳሰበ ነው።  

ይህ ምእመናንን ለዘመናት ያፍገመገመ ችግር የሚፈታው የምእመናንን ጥያቄ በማድበስበስ ወይም የተቃውሞ ሰልፋቸውን በጉልበት በማስበተን ወይም በመንግስት ማሳሰቢያም አይደለም። ወይም አባቶችን ተዳፈራችሁ ብሎ በማሳጣት አይደለም። ብቸኛው መፍትሔ ሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ አውርደው ፍጹም አንድነትንና ሰላምን ሲያውጁ ነው። ከዚያም ዶ/ር ዐቢይ ቤተ መንግስቱን ማጽዳት እንደጀመረ አንድ የሚሆነው ቅዱስ ሲኖዶስም ቤተ ክህነትንና አጥቢያዎችን ማስተካከል ይችላል። ከዚያ በኋላ ነው እግዚአብሔርም ምእመናንም የሲኖዶስ አባላትን ስም በሕይወት መዝገብ ማስፈር  የሚጀምሩት።

ማሳሰቢያ:- ፎቶዎች የተወሰዱት ከኢንተርኔት ነው!


No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...