Saturday 26 January 2019

የተማረ ይግደለኝ! ዩኒቨርስቲዎቻችንን በጨረፍታ


ከሦስት ሳምንታት በፊት ከለውጡ ጋር መደመሬን ለራሴ በራሴ ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ሄጄ ነበርበነበሩኝ አራት መናጢ አጫጭር ቀናት ለዓመታት ያላየኋቸውን ቦታዎች ተዘዋውሬ ጎበኘኋቸው። አዲስ አበባ እንደተባለውም ድንገት ከእንቅልፏ ተነስታ ራሷን በመገንባት ላይ ያለች ትመስላለች። ረጃጅም ሕንጻዎች በሁሉም የመዲናይቱ ክፍሎች ተገትረዋል። ገና ያላለቁ ጅምር ሕንጻዎችና በውስጣቸው ምን እንደያዙ የማያሳዩ የታጠሩ ቦታዎችም እንደ ልብ ይታያሉ። እነዚያ የምናውቃቸው ሰፋፊ መንገዶች በባቡሩ መስመር የተነሳ ተለዋውጠዋል። የቆየ ውበታቸው ከስሟል። የባቡሩን ሀዲድ ግራን ቀኝ አቅፈው የያዙ ከፍታ ያላቸው አስቀያሚ ብረቶች የከተማዋን ውበት ለመሻማት ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ።  መንገድ ለማቋረጥም እቅድ ያስፈልጋል። የሆቴሎች፣ የሬስቶራንቶች፣ የካፌዎች፣ የሞቴሎችና የባሮች ብዛት አስገራሚ ነው! የኑሮው ውድነት አይጣል ነው። መሳደብ መሸነፍ ነው! መግደል መሸነፍ ነው! ዘረኝነት መሸነፍ ነው! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! ዐቢይ መሲህ ነው! ወዘተ የሚሉ መፈክሮችን ከታክሲዎችና ከግንቦች ላይ አነበብኩ።


ዋናው የዛሬው ጉዳዬ መነሻ ግን አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው! ከጎበኘኋቸው ቦታዎች መካከል ትልቁን ዋጋ የሰጠሁት ለዩኒቨርስቲው ነው። በዩኒቨርስቲው ለአራት ዓመታት ከመማሬም በተጨማሪ ለሦስተኛ ድግሪዬ ማሟያ የሆነውን ምርምር ለግማሽ ዓመት ያደረግሁት በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ነበር።  አሁንም በቀጣይነትም ሥራዬ ወይም ሙያዬ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከማጥናት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለዩኒቨርሲቲው ልዩ ፍቅር አለኝ።

ይህች ጽሑፍ በጉብኝቴ ወቅት የታዘብኩትን በማስቀደም ትጀምርና አጠቃላይ ዩኒቨርስቲዎቻችን የሚገኙበትን ሁኔታ ባጭሩ ትቃኛለች። አንባቢዬን የማስገነዝበው ጉዳይ ቢኖር ጽሑፏ የምታተኩረው በጥናትና ምርምር በተገኘ ውጤት ላይ ሳይሆን ግላዊ ምልከታና ሚዲያ ዘገባ ላይ ነው። ዓላማዋም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዩኒቨርስቲዎቻችንን በተመለከተ ያለውን ተሞክሮና ግንዛቤ እንዲፈትሽ ከዚያም ለትምህርት ጥራትና አግባብነት ሁሉም እንደሚመለከተው ለማስገንዘብ ነው። ከዚህ በፊት በርካታ ጽሑፎች ስለትምህርት ጥራትና አግባብነት መውደም ተጠቃሽ ምክንያቶችንና መንሰኤዎችን አቅርበዋል። ብዙ ጽሑፎች መንግስት ወይም ትምህርት ሚኒስቴር ማድረግ የነበረበትንና ያለበትን ጉዳዮች ያብራራሉ። ይህች አጭር ጽሑፍ ግን ችግሩን ወደታች አውርዳ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የራሱን አበርክቶ እንዲያጤን ታነሳሳለች። ይህን ዓላማ ለማሳካት ከላይ ከተገለጸው ጉብኝት ትጀምራለች።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው በር 

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  ስድስት ኪሎ ዋናው ግቢ መግቢያ በር ላይ አራት የካምፓስ ፖሊሶች ገቢውንና ወጭውን ያስተናብራሉ። ሰላምታዬን ካቀርብኩ በኋላ ግቢውን ለመጎብኘት እንደምፈልግ በትህትና ተናገርኩ። ቁጭ ብሎ የነበረው ፖሊስ ቶሎ ብሎ ተመለከተኝና መግባት እንደማልችል ተናገረ። እኔም መታወቂያ ማስያዝ እንደምችል ጉብኝቴም አጭርና ማንንም የሚረብሽ እንደማይሆን አብራራሁ። ፈቃደኛ አልሆነም። አብሮ የነበረው ጓደኛዬ ትንሽ እየተናደደ እንደመጣ ታዘብኩ። ፈጠን ብዬ ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት የተማርኩበት ዩኒቨርስቲ እንደሆነ ሳልጎበኘው ወደመጣሁበት ብመለስ ክፍተት እንደሚሰማኝ አስረዳሁት። ፖሊሱም «ምን የሚያጓጓ ነገር ያለ መሰለህ! ድንጋይ ብቻ ነው አንተ የምትፈልገው ዩኒቨርስቲ የለም» አለኝ ኮስተር ብሎ ሌሎችን ፖሊሶች እየተመለከተ። ያልተጠበቀና አነጋጋሪ መልስ ነበር። 

እኛም አምርረን ከለመን በኋላ ተፈቀደልንና መታወቂያ አስይዘን ገባን። ኬነዲ ቤተ መጽሐፍት ቤትን፣ የተማሪ መኝታ ክፍሎችንና የመማሪ ክፍሎችን እንዲሁም የአስተዳደሩን ጽ/ቤት ከውጭ ጎበኘናቸው። ያው እንደ ከተማዋ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥም አዳዲስ የተጠናቀቁ  የተጀመሩም ሕንጻዎች አሉ። ከዚህ ውጭ ብዙም የተቀየረ አልነበረም። ተማሪ ሆኜ የምመላለስባቸውን መንገዶችና የተማርኩባቸውን ጥቂት ክፍሎች ጎበኘኋቸው። የተማሪነት ዘመኔን እንደገና ለመኖር በሚመስል መልኩ የጊዜን ባቡር ተሳፍሬ ወደ ኋላ ጋለብኩኝ!

ግቢውን ለቀን ስንወጣ ጀምሮ ፖሊሱ ስለዩኒቨርስቲው የተናገረው ከአእምሮዬ አልጠፋም። «ድንጋይ ብቻ ነው ያለው! አንተ የምትፈልገው ዩኒቨርስቲ አሁን የለም» ወዘተ። ከባድ ንግግር ነው። በእርግጥ ከዚያ በፊት ከዚያም በኋላ በሚዲያዎች ስለ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቃለ መጠይቆችና ጽሑፎችም ቀርበዋል ይቀርባሉም። ይሁንና የፖሊሱን አነጋገር መነሻ በማድረግ ስለዩኒቨርስቲዎቻችን አንድ ነገር ማለት እንዳለብኝ እያሰብኩ ቀናት ነጎዱ። ይህ በእንዲህ እያለ ዛሬ ጥር 18 ቀን 2011 ዓ/ም በሸገር ኤፌኤም ሬዲዮ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አንድ ዝግጅት አዳመጥኩ።

የዝግጅቱ ትኩረት በኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ስለሚያስተምሩ ሕንዳውያን መምህራን ነው። ዋናው የጋዜጠኛው አንኳር ነጥብ ከሕንድ የመጡ መምህራን ችሎታና ብቃት እንደሌላቸው ይህም ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል አስተዋጽዖ እንዳደረገ የሚያትት ነው። ይህን ሃሳብ ለማጠናከር አንድ የዩኒቨርስቲ ኢትዮጵያዊ መምህር የራሱን ተሞክሮ እንዲያቀርብ ተጋበዘ። መምህሩም ተማሪ እያለ ሕንዳውያን መምህራን ከኢትዮጵያውያን መምህራን ባነሰ መልኩ ያስተምሩ እንደነበር አሁን ደግሞ በመምህርነቱ የሚያውቀው ሕንዳዊ የሥራ ባልደረባው ኢትዮጵያ የሚመጡት ሕንዳውያን በሀገራቸው ተወዳድረው ሥራ ማግኘት ያልቻሉት እንደሆኑ እንደነገረው አብራራ። ተማሪዎችም ከሕንዳውያን ይልቅ ኢትዮጵያውያን መምህራንን እንደሚመርጡ አሰመረበት። ይህን በተመለከተ ጋዜጠኛው ከትምህርት ሚኒስትር የሚመለከተው አካል ማብራሪያ እንዲሰጥበት ለሁለት ሳምንታት ያህል ቢጥርም እንዳልተሳካለት አሳወቀ። የሚመለከታቸው አካላት ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል ምክንያት መረጃ እንዳላገኘ አጥብቆ ተናገረ። ይሁንና በቀጣይነት መረጃ የሚሰጥ ከተገኘም እድሉ እንደሚሰጥ በማሳወቅ ዝግጅቱ ተጠናቀቀ። 

ይህ የሸገር ሬድዮ ዝግጅም ሆነ የፖሊሱ ንግግር ስለ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማለትም ዩኒቨርሲቲዎች፣ ዩኒቨርስቲ ኮሌጆችና ኮሌጆች አያሌ ጥያቄዎችን እንድናነሳና መልስ እንድንሰጥ ይጋብዙናል። የትምህርት ጥራትና አግባብነት ሲባል በዋናነት ምንን አካታች ነው? ጥራትና አግባብነት ማሽቆልቆሉን የሚጠቁሙ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ለጥራትና አግባብነት ማሽቆልቆል ተጠያቂው ማነው? ለነዚህ ጥያቄዎች ወጥና ሁሉንም የሚያስማሙ መልሶች ላይኖሩ ይችላል። ይሁንና ጥናቶችን፣ ግላዊ ምልከታዎችንና የሚዲያ ውይይቶችን መነሻ በማድረግ አማራጭ ሀሳቦችን ማቅረብ ይቻላል። በተለይም ተጠያቂነትን በተመለከተ ካሁን በፊት በሚዲያ ከተላለፉት ውይይቶች ለየት ያሉ ጉዳዮችን በክፍል ሁለት ለማቅረብ እሞክራለሁ።  ይህም ምናልባትም ቀጣይ ውይይቶች እንዲነሱ ሊያግዝም ይችላል።  

እንደ መግቢያ ያህል ግን ስለኢትዮጵያ  ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥቂት ማለቱ ግንዛቤን ያሰፋል። በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተጀመረው ዘመናዊው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እድገት ፈጣን ሊባል የሚችል ነው። ለየት ባለ መልኩ በአንድ ጊዜ እስከ 10 የሚጠጉ የሕዝብ ዩኒቨርሲቲዎች ድንገት የተከፈቱባት ሀገር ነች ኢትዮጵያ። የግል ዩኒቨርስቲዎችም እንደዚሁ! ባሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ 50 የሕዝብና 130 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሏት። በተጨማሪም 1500 የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ይገኛሉ። አጠቃላይ የተማሪው ብዛት እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ሪፖርት ከሆነ ከ860, 000 በላይ ደርሷል። በዓመት በአማካኝ 100, 000 ተማሪዎች ይመረቃሉ። ክፍል 2 ይቀጥላል!

    

           




      
          

No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...