Sunday 5 January 2014

ጎጂ ባህሎቻችን (የመጨረሻው ክፍል)

በዚህ የመጨረሻ ክፍል ከአስተሳሰባችንና ከአመለካከታችን ጋር ቀጥታዊ ግንኙነት አለው ብዬ የማስበውን ጎጂ ባህል አቀርባለሁ:: ይህን ጎጂ ባህል በሚገባ መመርመርና ማስወገድ ከቻልን አገራችን ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ሁለንታዊ ችግሮችና ቀውሶች ለመላቀቅ የሚያስችላትን ትክክለኛ መንገድ ልትይዝ ትችላለች:: ቀጣይነት አስተማማኝና ሁሉን አቀፍ የሆነ የእድገታዊ ለውጥ መሰረት ሊጣል ይችላል:: ነገር ግን ይህን ጎጂ ባህል ተቋቁሞ ማለፍና ለቀጣይ ብሄራዊ ለውጥ መስራት ፈታኝ እንደሆነ ግልጽ መሆን አለበት:: ይህን ጎጂ ባህል አጠር አድርጌ ከገለጽኩ በኋላ መፍትሄ ጠቋሚ ሃሳቦች ላይ አተኩራለሁ::

የሥርዓት ለውጥ ባህላችን 

የአገራችንን የሩቅና የቅርብ ታሪክ ስናነብ ጎልቶ የሚታይ ሃቅ አለ:: ኃይል የሥልጣን ሁሉ መገኛ ማግኛና ማቆያ መሆኑ:: ይህ ሃቅ ሁሉንም መንግስታት በደንብ ይገልጻቸዋል:: ሌላው ቀርቶ ሰለሞናዊ ሥርዎ መንግስት በሰላም እንቀባበላለን የሚሉ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ሳይቀሩ በዚህ መንገድ መሪያቸውን ሲያስቀምጡ ኖረዋል:: የሰው ደም ሳያፈስ የነገሠ ንጉሥ የለም:: ሥልጣን ሊቀናቀን ይችላል ተብሎ  የተገመተ በአጭሩ ሲቀጭ ኖሯል::

ከዚያም ደርግ በጊዜው የነበረውን የህዝብ ብሶት ምክንያት በማድረግ ኃይል ተጠቅሞ ጃንሆይን ከመንበራቸው አወረደ:: በስንት ድካም ኢትዮጵያ ያፈራቻቸውን ሚኒስትሮችና ሌሎች ባለሥልጣናትን በጥይት ደብድቦ ገደላቸው:: ሌላው ቀርቶ ደርግን የመሰረቱት ቁልፍ ሰዎች ሳይቀሩ እየተመረጡ "አብዮታዊ እርምጃ" ተወሰደባቸው:: በዚህ ሁኔታ ይህ ኃይል ያለው አካል ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን አስጨንቆ ገዛት:: በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደመ ከልብ ሆነው ቀርተዋል::

ሁሉም ነገር የራሱ የሆነ የመቆያ ጊዜ አለውና ደርግን ሌላ ኃይል ተካው:: "ብሶት የወለደው ጀግናው የኢሕአዴግ ሠራዊት" እስከአፍንጫው የታጠቀውን የደርግ ሠራዊት ድባቅ መታ ተባለ:: የኢትዮጵያ ህዝብ አውንታዊ ለውጥ ይመጣል ብሎ ጓጓ:: ይህ ጉጉት ብዙም ሳይቆይ ከሰመ:: ይህ መንግስትሥልጣን ላይ እያለ ኃይል ፍቱን ዘዴ እንደሆነ ደጋግሞ አሳየን:: ህዝብ ያልተሳተፈባቸውና ያልወደዳቸው ህጎችና ፖሊሲዎች ተረቀቁ:: ህዝብ በቋንቋና በዘር መስመር እንዲጓዝና ሁሉንም ነገር ከዚያ አኳያ እንዲተረጉም ተደረገ:: ትችት ያቀረቡና የተቃወሙ የኃይል ሰለባ ሆኑ:: በርካቶች የምድር ሲዖል በሆኑ እስር ቤቶች ተቆለፈባቸው:: ሌሎች ብዙዎች ወደባዕድ አገር ተሰደዱ:: ብዙዎች ተደበደቡ ተገደሉ:: ኃይል ያልገታው ምንም ነገር የለም:: በምርጫ ውስጥ ሳይቀር ኃይል አለ:: ኃይል ስላለ መንግስት ክፉኛ የተዳከመበት ምርጫ ሳይቀር እንዳልሆነ ሆነ::  

ባጠቃላይ ሲታይ መሪዎቻችን ሥልጣን በኃይል ሲይዙ ኖረዋል:: የሚያስፈራቸው ነገር ቢኖር ኃይል ያለው ሌላ አካል ብቻ ነው እንጅ ህዝብ አይደለም:: አብዝተው የሚጨነቁት ለህዝቡ ለውጥና እድገት እንዴት መምጣት እንዳለበት ሳይሆን ተቀናቃኝ ኃይልን መምታት ላይ ነው:: እንደፈሪሳውያን ራሳቸው የማያከብሩትን ህግ እየጠቀሱ በነጻነት የሚያስቡና የሚናገሩትን ያድናሉ:: ይህ ባህል ማኅበራዊ ባህላዊ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እንዳይመጣ ከማድረጉም ሌላ በምንም የማይተካውን የሰው ልጅ ህይወትን ቀጥፏል:: በነጻነት ቀና ብሎ  የመኖር ጸጋን  ገፏል:: ምንም እንኳን በብሄራዊ ደረጃ በማንም ቅኝ ያልተገዛንና ነጻ ብንሆንም በመሪዎቻችን ወጠምሻ ጡንቻዎች ስንታሽ የኖርን ባሪያዎች ግን ነን::

ጦርነት ወይስ ምርጫ?

ሁለንታዊ እድገታዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው እንዴት ነው ተብለን ብንጠየቅ መልሳችን ከሁለት አንዱ ላይ ያርፋል:: ሰላማዊ በሆነ መንገድ ታግሎ በምርጫ መንግስትን ማሸነፍ እንደሚቻል የሚያምኑ አያሌ ናቸው:: አብዛኞቹ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን መስመር ተከታይ ናቸው:: እሾህን በእሾህ እንዲሉ ጦርነት በመንግስት ላይ በማካሄድ ለውጥ ይመጣል ብለው የሚያምኑ በየጫካውና በየረሃው የሚማስኑ አሉ:: የትኛው መንገድ አትራፊ እንደሆነ መናገር እጅግ ከባድ ነው:: ነገር ግን ታሪካችንንና አመክንዮን ከግምት ውስጥ በማስገባት እነዚህን አማራጭ መንገዶች መገምገም እንችላለን:: ለኢትዮጵያ ሰላማዊ ዘለቄታዊና ፍትሃዊ ለውጥ (ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ማለቴ ነው) ማምጣት የሚያስችል አቅጣጫ መጠቆም ይቻላል::

እኔ ግን የመጀመሪያው መንገድ (በምርጫ ማሸነፍ) በፍጹም እውነተኛ ለውጥ አያመጣም ብዬ አምናለሁ:: በምርጫ መሸነፍ ሥልጣን ላይ ላሉ ግለሰቦች ቀጥታዊ አስጊ ሁኔታ ሊፈጥ ይችላል:: ብዙ ባለሥልጣናት በተለያዩ ወንጀሎች ሙስናን ጨምሮ የተሳተፉ ናቸው:: ከተሸነፉና ሥልጣን ከለቀቁ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ወይም በቀል እንደሚፈጸምባቸው ያምናሉ:: በጃንሆይና በደርግ ባለሥልጣናት ላይ የተደረገውን በማሰብ ከተመሳሳይ ጥቃት ሊድኑ የሚችሉበትን መንገድ ይከተላሉ:: በሰላም ቀሪ ህይወታቸውን መምራት እንደማይችሉ በመገመት ያለ የሌለ ኃይል ተጠቅመው ሥልጣን ላይ መቆየት ይመርጣሉ:: ምርጫን ለማሸነፍ በህዝብ ገንዘብ ፕሮፓጋንዳ ይሰራል:: አበል ለመራጩ ይከፈላል:: ሌላ ፓርቲ ሊመርጡ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች ማስፈራሪያና ዛቻ ይደርስባቸዋል:: ይህ ሁሉ ተደርጎ ገዥው ፓርቲ ቢሸነፍ እንኳን የህዝብ ድምጽ ይሰረቃል:: ሥልጣን አለቅም ማለት ይመጣል:: የ1997ቱ ምርጫ ለዚህ ሃተታ ህያው ምስክር ነው:: በመሆኑም ባለሥልጣናትን ጭምር ነጻ የሚያወጣ የፖለቲካ መፍትሄ እስካልተገኘ ድረስ በምርጫ ማሸነፍ ይቻላል ብሎ ማሰብ የህልም እንጀራ ነው::   

ጦርነትም ቢሆን ዘለቄታነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም:: በዘመናችን ያሉትን ከባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ መንግስትን በኃይል ማሸነፍ ቢቻል እንኳን ሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎችና ደጋፊዎቻቸው አስጊ ሁኔታ እንደተፈጠረባቸው ያስባሉ:: አሸናፊው ኃይል አራት ኪሎ ሲገባ እነሱ ወደበረሃ የሚገቡበት አጋጣሚ ይኖራል:: ይህም ባይሆን ወደምዕራቡ አገራት መሸሽና ከዚያ ሆኖ ትግል መጀመር የተለመደ ነው:: በተጨማሪም በኃይል የገባ እስካሁን እንዳየነው በቀላሉ ሥልጣን ሊለቅ ወይም እውነተኛ ዴሞክራሲ ሊያሰፍን ይሳነዋል:: ሲደመር አሁን ያለንበት ወቅት ዘርን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ እንቅስቃሴን ደጋፊ ነው:: በመሆኑም በጦርነት የሚገኝ ፖለቲካዊ ድል በአንድ ብሄር ላይ የተገኘ ድል መስሎ ሊታይ ይችላል:: ይህም መራራ ብጥብጥና  ቀውስ ይፈጥራል:: የአንዳንድ ብሄረሰቦችን የመገንጠል እድልን ያሰፋል:: መገንጠሉ ደግሞ  የራሱ ምስቅልቅሎች አሉት:: ከተገነጠሉም በኋላ በድንበርና በሃብት የተነሳ ወደጦርነት የመግባት እድሉ ሰፊ ነው:: ለዚህ ኤርትራ ጥሩ ምሳሌ ናት:: ሌላው ጦርነትን ያህል ጎጅ ባህል ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ  ለኅሊና የማይመች ነው:: ምንም ይሁን ምን በጦርነት የሚመጣው ለውጥ እጅግ መስዋዕትነት የበዛበትና ጊዜያዊ ነው የሚል እምነት አለኝ::          


ሦስተኛው መንገድ 


ጦርነትና ምርጫ ሁሉን አቀፍና ዘለቄታዊ ለውጥ የማያመጡ ከሆነ መፍትሄው ምንድን ነው? ለብሄራዊ መግባባት ከዚያም እርቅ የሚያበቃ ክርክርና ውይይት ማካሄድ መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ:: ይህ መንገድ ከላይ ከተጠቀሱት ሁለቱ አማራጮች ቀጥለው በተዘረዘሩት ምክንያቶች የተነሳ እጅጉን የተሻለ ነው:: 

  • ይህ መንገድ በሚገባ ከተያዘና ከተጠናቀቀ አምባገነኖችን ሳይቀር ነጻ የሚያወጣ ነው 
  • ይህም በመሆኑ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽዖ ያደርጋሉ 
  • ሁሉም ተሳታፊ ስለሚሆን ጦርና የጦር ወሬዎች ታሪክ እየሆኑ ይሄዳሉ
  • ይህ መንገድ የሰው ህይወትም ሆነ ንብረትና ሃብት አያጠፋም በመሆኑም ይህ የፖለቲካ መስመር ጭስ አልባ ሊባል ይችላል
  • ስለሆነም በሚያስፈራ ዝምታ ውስጥ ያለውን የሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ ቀልብ ሊስብ ይችላል 
  • ለመግባባትና ለእርቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ስላለው አስፈላጊውን ድጋፍና  ማበረታቻ ማግኘት አይከብድም          
  • በመጨረሻም ይህ የትግል ስልት ቀጣይነት ያለው ሰላምና እድገት ለኢትዮጵያ ያስገኛል  

አመቺ ሁኔታዎች አሉ? 

ብዙዎች ይህን ሦስተኛውን የፖለቲካ ስልት በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ይደግፋሉ:: ዳሩ ግን እርቅ ለማካሄድ አስገዳጅ ወይም አመ ሁኔታዎች የሉም ሲሉ ይሞግታሉ:: የተወሰነ እውነታ ሊኖረው ይችላል:: ነገር ግን አመ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው ብለን መጠየቅ ይገባል:: ምን አይነትና ምን ያህል አመቺ ሁኔታዎች ያስፈልጋሉ? እኔ ግን ብሄራዊ እርቅ ለማድረግ ከበቂ በላይ ተፈላጊ ሁኔታዎች አሉ እላለሁ:: ለምሳሌ ያክል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል:: 

  • የገዥው ፓርቲ ሞተሩ አቶ  መለስ ከሞቱ በኋላ ፓርቲው ጀርባውን እንደተመታ እባብ ክፉኛ እየተልፈሰፈሰ ነው
  • ባለሥልጣናቱም በሙስና ተነክረዋል መውጫ በር ካገኙ አይናቸውን አያሹም  
  • ጣሪያ የነካ የኑሮ  ውድነት ህዝቡን ክፉኛ አድቅቆታል ይህም ባለሥልጣናቱን አሳስቧቸዋል  
  • የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች እውነት መናገርና መልቀቂያ ማስገባት ጀምረዋል 
  • የአመራሩ እድሜ መግፋትና የጤና መታወክ ለሰላማዊ ለውጥ ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል የማታ እንጀራ ከሰላም ጋር የሚጠላ የለም
  • የውጭ ምንዛሬ እጥረት የመንግስትን እንቅስቃሴ ገትቷል ቢዝነሶች እየቆሙ ነው 
  • የሃይማኖት ተቋማት በተለይ ኦርቶዶክስና እስላም በመንግስት ላይ ተቃውሞ ማሰማት ጀምረዋል  
  • ከ90% በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃይማኖተኛ ስለሆነ ይቅርታ ለማድረግና በአንድነት ለመኖር አይከብደውም 
  • አገር ቤት ያሉ ተቃዎሚ ፓርቲዎች እምቢታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል 
  • የታጠቁ ኃይሎች መንግስትን እያሳሰቡት ነው 
  • የምዕራባዊያን አንዳንድ መንግስታትና ተቋማት ሰብአዊ መብት እንዲከበርና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እየጠየቁ ነው 
  • ዲያስፖራው ኢትዮጵያዊ የመንግስት ባለሥልጣናት ውጭ አገር ሲወጡ አላንቀሳቅስ ብሏል ገንዘብ መሰብሰብ ቀርቶ ሻይ ቡና ማለትና መዟዟር አልቻሉም 
  • አምባገነኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊከሰሱበት የሚችል አጋጣሚ አለ ሃብታቸውም እንዳይንቀሳቀስ እየተደረገ ነውና ይህ ለባለሥልጣናቱ አስጊ ነው 
  • በአጠቃላይ የእነዚህና የሌሎች ሁኔታዎች ድምር መንግስት ሁሉን አቀፍና ጭስ አልባ ድርድር እንዲቀበል ያደርጉታል 

ይህ ሦስተኛው የትግል ስልት እንዴት በማንና መቼ መጀመር እንደሚችል ከወራት በፊት የቀረበን ጽሁፍ ይህን በመጫን ያንብቡ http://tekluabate.blogspot.no/2013/07/inclusive-debate-prelude-to-national.html#more  

ማጠቃለያ 

በዚህ ጽሁፍ ሦስተኛ የተባለው ለውጥ ማስገኛ ዘዴ ከሌሎቹ ከተለመዱት የትግል ስልቶች የሚለየው ሁሉን አቀፍ ዘለቄታዊና አፋጣኝ እድገትን ሊያመጣ እንደሚችል በመታሰቡ ነው:: በሰው ልጅ ህይወትና በንብረት ላይ ምንም አይነት ውድመት አያመጣም:: ይህ መንገድ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገባ አልተኬደበትም:: የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች እንዲሁም ሲቪክ ድርጅቶች ከግምት ውስጥ ሊያስገቡት የሚገባ አማራጭ ነው:: ነገር ግን ከጦርነት ያላነሰ ርብርብና ስትራቴጅ ይፈልጋል:: በዋናነት የነገዋን ኢትዮጵያን እንጅ የዛሬዋንና የትናንትናዋን አይስልም:: ይህንም ለማድረግ ላቅ ያለ የሰብአዊነትና የሞራል ብቃትንና ብስለትን ይጠይቃል:: ይህን የለውጥ ስልት እንድንወያይበት ሳሳስብ ግን ሌሎች በመደረግ ላይ ያሉ ትግሎችን ማንቋሸሼ ወይም እንዲቆሙ መጣራቴ እንዳልሆነ አንባቢ ይረዳልኝ::     

2 comments:

  1. I wish this article is sent to TPLF øeaders and Ethiopian ministry of foreign affairs. They will learn a lot from it. who knows may be they change their view. Reconciliation is much better for the Tigrean ruling class to get forgiveness as well as to enjoy the billions of dollars they looted from Ethiopian people for the past 23 years, the aid money and the money they received in relation to invasion of Somalia, sell of land to Saudis and Chinese, and the wealth they accumulated by privatizing national economy.

    ReplyDelete
  2. This third option for freedom and democracy looks real clean but am afraid we do have far-thinking people to materialize this. I could not think of TPLF and the opposition coming into terms with our deadly politics. I appreciate Ato Teklu for his insight and courage though!
    Thanks.

    ReplyDelete

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...