Friday 9 September 2016

ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ!

በአገራችን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ አሳሳቢ አጓጊም ሆኗል ፈጣሪ በኋላም ዓለም አቀፍና ብሄራዊ ሕግጋት የሰጧቸውን በፍጹም በነጻነት የመኖር መብታቸው እንዲከበርላቸው የጠየቁ ወገኖቻችን በመሰዋታቸው አካለ ስንኩላን በመሆናቸው የሲዖል አምሳያ በሆኑ እስር ቤቶች በመጋዛቸው መከራ ለበዛበት ስደት በመዳረጋቸው ባጠቃላይ እንደ ሰው በሰላም መኖር ባለመቻላቸው ሃዘናችን ወሰን የለውም  በአንጻሩ ደግሞ ለመኖር እየተደረገ ያለው አለመኖር ማለትም ትግል መንግስትን ክፉኛ ስላሸበረውና ደካማነቱን ከምንም ጊዜ በላይ አጉልቶ በማሳየቱ ሁኔታውን አጓጊ አድርጎታል ምንም ይሁን ምን ካሁን በኋላ መንግስትም ሕዝብም በነበሩበት የመግዛትና የመገዛት ሂደት ውስጥ መቀጠል አይችሉም ይህም አንዳች ለውጥ ሊመጣ እንዳለው አመላካች ስለሆነ ትግሉ ውጤታማ እየሆነ እንደመጣ ይገነዘቧል 


ዳሩ ግን የትግሉ ፍጥነት አቅጣጫና መድረሻ በውል ባለመታወቁ ስጋትን መጫሩ አልቀረም   በተለይ ገዥው ፓርቲ ለዘመናት ሲነግረን የቆየው «እኔ ከሌለሁ አገሪቱ ትበታተናለች የሚለው ግብታዊ ፕሮፓጋንዳ ሳናስበው ያሳሰበን ይመስላል የኢትዮጵያን ሕዝቦች ታሪካዊ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትስስር ግምት ውስጥ ካስገባን መጪው ሁኔታ ከነበርንበትና ካለንበት ኑሮ የከፋ እንዳይሆን ማድረግ እንደምንችል ማመን እንችላለን  በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን አንዱ ለሌላው ያለውን ዘመዳዊ መንፈስ ማሳየታቸው ትልቁ ተስፋ ሰጭ ምልክት ነው በዚህ አይነት ትብብርና መናበብ እጅግ የተሻለ ሁሉን አሳታፊ ሕዝባዊ መስተዳድር መዘርጋት እንደሚቻል መታመን አለበት    

ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ሁሉም ያገባኛል ባይ አካል ለሚናገረው ለሚጽፈውና ለሚያደርገው ነገር ሁሉ ሲጠነቀቅ ብቻ ነው ያለውን መንግስታዊ ወንበዴነት ለማስወገድ ጉልበትና ስሜት በቂ አይደለም ይህንማ መንግስትም ከበቂ በላይ አለው! የሰከነ አስተሳሰብ አመለካከትና ምግባር እንዲሁም የሞራል ልዕልና ያስፈልጋል የተሻለ ሥርዓት የምንናፍቅ ከሆነ መንግስት እስካሁን ድረስ ካሳየን የአስተሳሰብና የሞራል ድህነት መውጣት ይኖርብናል ይህ አይነት ልዕልና ያለውን ሥርዓት ጡረታ ለማውጣት ብቻ ሳይሆን ወደፊት ሊመሰረት ለሚገባው ነጻና ሕዝባዊ መንግስት የማይናወጥ መሠረት ይጥላል       

ይህን ታሳቢ በማድረግ ከዚህ በታች እውነተኛ የነጻነት ታጋዮች ሁሉ ቢያደርጓቸው የሚጠቅሟቸውን ከአስተሳሰብ ከአመለካከትና ከሞራል ጋር ተያያዥ የሆኑ ጥቂት ነጥቦች ተዘርዝረዋል ነጥቦቹ  ኢትዮጵያዊያን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኅን በአካልም የሚያነሷቸው የሚጥሏቸው ትኩስ ድንቾች ሆነው ይስተዋላሉ ይህም ነጥቦቹ እጅግ አወያይና አከራካሪ መሆናቸውን ያመላክታል ዓላማችን ሁሉን አሳታፊና ዘለቄታ ያለው ነጻነት እኩልነትና እድገት ለማምጣት ብቻ ከሆነ ግን መግባባት ላይ መድረስ የከበደ አይሆንም አለመግባባቱ የሚከሰተው ግላዊና ጊዜያዊ ውጤቶች ወይም ጥቅሞች ላይ  ብቻ ካተኮርን ነው ከዘር ከሃይማኖትና ከድርጅት የአስተሳሰብ ማእቀፍ ወጥተን በነጻ አእምሮ መመራመርና ለአገራችን የሚበጀውን ማሰብ እጅግ ያስፈልገናል ቀጥለው የተዘረዘሩትን ተግባራዊ ብናደርግ እጅግ እንደምንጠቀም አልጠራጠርም።

  •  ሕወሓት ሁሉ ትግሬ ነው ትግሬ ሁሉ ግን ሕወሓት አይደለም! ቢያንስ በገጠሪቱ ትግራይ የሚኖረውን ሕዝብ ማስታወስ ያስፈልገናል ስድስት ሚሊዮን የሚሆነውን የትግራይ ሕዝብ በሙሉ ሕወሓት እንደሆነ በመገመት ማግለል ስህተትና ጎጂ ነው። ይህ ሕዝብ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ እንደሚገኝ ተረድቶ ይበልጥ መግባባትና አብሮ መሥራት ያስፈልጋል የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል መሰሪ ከሆነው ከሕወሓት አስተሳሰብና አመለካከት እንዲሁም ግፍ እንጅ ከትግራይ ሕዝብ ጋር እንዳልሆነ በማያሻማ መንገድ ማሳየት ያስፈልጋል 
  •  ሕወሓትን ብቸኛው የሕዝብ ጠላት አድርጎ ማየት ስህተት ነው ወደውም ይሁን ተገደው ወክለናል በሚሉት ሕዝብ ስም መንግስት መስርተው የግፍ አገዛዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ብአዴን ኦሕዴድና ደሕዴንም ተጠያቂዎች መሆን አለባቸው   
  •  ዳሩ ግን የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ሁሉ ይወገዙ ማለት አይደለም! አባል ወይም ደጋፊ መስለው ለሕዝብ ፍላጎት የሚጥሩ ስለሚኖሩ እነሱን መለየትና ማበረታታት ያስፈልጋል 
  • የኢሕአዴግ አባል ወይም ደጋፊ ያልሆኑ በስውር ግን ሕዝብን አሳልፈው የሚሰጡ መለየትና መወገዝ አለባቸው 
  •  ፖሊሱና ወታደሩም ሕዝቡ የሚደርስበት ግፍ ሁሉ ቀማሽ ነው! ዳሩ ግን ደመ ዎዙን ለማግኘት አድርግ የተባለውን ሁሉ እያደረገ ነው በእርግጥም መግደልና መደብደብ የሚያረካቸው ፖሊሶችና ወታደሮች አሉ ይህም ቢሆን ከሕዝብ ጋር እንዲቆሙ ማግባባት ጥበብ ነው  
  • መንግስትን ደግፈው ሕዝብን የሚገስጹ የሃይማኖት አባቶችን ማግለልና የሃይማኖት አባትነታቸውን አለመቀበል ወሳኝ ነው እነዚህ ለሥጋቸው ያደሩ አባቶች ወክለናል የሚሏቸውን ሃይማኖቶች እንደማይወክሉ ማወቅ ያስፈልጋል  
  • ትግሉ የፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም በመቋቋም ላይ ያሉ ድርጅቶችና ኅብረቶች አሉ መነሻና መድረሻቸው ማለትም ማንነታቸውና ምንነታቸው በደንብ እስኪታወቅ ድረስ በጥንቃቄ መከታተል ያስፈልጋል ዳሩ ግን በቅንነት ወገኖቻችንን ለመታደግ የሚጥሩም ይኖራሉ   
  • ሰላማዊ ሰልፍ እየወጡ የጥይት ሰለባ መሆን አላዋጣምና ሌሎች ስልቶችን (ለምሳሌ የሥራ ማቆም አድማ በመንግስት ተቋማት ላይ ዘለቄታ ያለው ማዕቀብ መጣል ግብር አለመክፈል ሰላዮችን መሰለልና በቁጥጥር ስር ማድረግ) እንደ ሁኔታው መጠቀም ያዋጣል 
  • ትናንት የቀኑ ክፋት ይበቃዋልና ዛሬንና ነገን እያሰብን ለሁሉ የምትመች ኢትዮጵያን ለመመስረትና ለማጽናት እንታገል! ለሥልጣንና ለግል ጥቅም ሲሉ ሕዝብን በዘር በሃይማኖት ወዘተ የሚከፋፍሉ አካላት ይገሰጹ  
  • ሁሉም አይነት ትግላችን መጥፎ ሀሳብንና ምግባርን እንጅ ግለሰብን ወይም ድርጅትን ለማጥፋት አይሁን! ግለሰብ ቢሞት ወይም ድርጅት ቢዘጋ አስተምህሮአቸው ግን ይቀጥላል መለስ ዜናዊ ሲሞት ለውጥ ለአገራችን እንደሚመጣ ገምተን ነበር አቡነ ጳውሎስ ሲሞቱም ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀን ወጣላት ብለን ነበር ዳሩ ግን ኃይለ ማርያምና አቡነ ማቲያስ በሌላ ቁመና  የነበረውን ቀውስና ግፍ ቀጥለውበታል ስለዚህ ትግላችን የሕወሓት ባለ ሥልጣናት እንዲሞቱ  ወይም እንዲሰደዱ ወይም እንዲታሰሩ ሳይሆን የቆሙለት እኩይ ሀሳብና ሥራ ከራሳቸውና ከሕዝብ ኅሊና እንዲጠፋ ነው ይህን ማድረግ ከቻልን ራሳችንን  ብቻ ሳይሆን ጨቋኞቻችንንም አርነት እናወጣቸዋለን ይህን በማድረጋችን ለቀጣዩ  ትውልድ የማይረሳ ትምህርትን እንሰጣለን ከማህተመ ጋንዲ ከኔልሰን ማንዴላ ከማርቲን ሉተር ኪንግ ከአንሳን ሱቺና ከሌሎችም  የነጻነት ታጋዮች የምንማረው ይህን ነው በመሆኑም በየትኛውም ደረጃ ትግሉን የሚመሩና የሚያስተባብሩ አካላት ከላይ የተዘረዘሩትንና ሌሎችንም ላቅ ያሉ የእእምሮ ሥራዎችን የሚሠሩና የሚያሠሩ መሆን አለባቸው     

ማጠቃለያ
ባጠቃላይ ሲታይ የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግስታዊ ሽብርን መሸከም ከሚችለው በላይ ስለሆነበት ላይመለስ ተነስቷል ላንቃቸውን የከፈቱ መትረየሶችን ሳይፈራ ራሱን ለመስዋእትነት አቅርቧል እስካሁን ድረስ ስንት ውድ ኢትዮጵያዊያን እንደተሰው እንደታሰሩ እንደተሰወሩ እንደተሰደዱ የአካል ጉዳተኛ እንደተደረጉ የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው ለውድ ቤተሰቦቻቸው ፍጹም መጽናናትን እየተመኘን እነሱ የሞቱለት ዓላማ ግን እንደሚሳካ ማመንና ለሱም መትጋት አለብን ከማንኛውም ፍርሃትና ይሉኝታ ራሳችንንና ቤተሰባችንን ቀጥሎም ጓደኞቻችንንና ጎረቤቶቻችንን ነጻ እናውጣ በተቻለን አጋጣሚ ሁሉ የመንግስትን እብድነት እናጋልጥ አትሌቶቻችን ድል ባገኙባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚደርስበትን መከራ መስክረዋል አርቲስቶቻችን ስለሞቱት ወገኖቻችን በማሰብ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙላቸውን የሙዚቃ ዝግጅቶቻቸውን ሰርዘዋል እያደረጉት ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው! ይህን እንደ አርአያ እንመልከተው! አብዝተው ለሚታገሉ ክብርና ድጋፍ እንስጥ! ውሸትን ሽንገላን ዘረኝነትን የሚሰብኩትን እንገስጽ! በየመስጊዱና ቤተ ክርስቲያኑ ለሕዝብ ከመጮህ ዝም እንድንል የሚያደርጉንን ሰዎች ዝም እናሰኛቸው! ባጠቃላይ እውነትንና ፍትህን በመያዝ ትግላችንን እንቀጥል! አዲሱ የኢትዮጵያ 2009 ዓመት የምር አዲስ እንዲሆን እንጣር! ለምንናገረው ለምንሠራው ለምንጽፈው ሁሉ ጥንቃቄ እናድርግ! ይህን ብናደርግ ራሳችንንና ሌሎችንም እናድናለን!  


   


No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...