Saturday, 8 October 2016

የወቅቱ ፖለቲካዊ አሰላለፍና ፋይዳው

የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል እየሰፋና ቀጣይነቱን እያረጋገጠ ሲሄድ በውጭው ዓለም የሚገኙ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ባህርያቸውን ይበልጥ እየገለጡ መጥተዋል ግለሰብ ተኮር እንቅስቃሴዎች ወደ ድርጅት ወይም ማኀበር ወይም ኅብረት እየተለወጡ ነው ይበልጥ ትኩረት እየሳበ የመጣው ግን የድርጅቶቹ ብዛት ሳይሆን የተነሱበት ዓላማ ወይም ግብ ነው የአንዳንዶች የትግል ባህርይ ከተጠበቀው በአንፃሩ ሆኖ በመገኘቱ ጥቂት በማይባሉ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ቁጣና ግርምትን ፈጥሯል ይህን ተከትሎ ክርክሮችና ተግሳጾች በመገናኛ ብዙኃን እየወጡ ነው እኒህ አይነት እንቅስቃሴዎች ትግሉ ምን ያህል ሰላማዊና አንድነትን የተላበሰ እንደሚሆን ካሁኑ ግርታን ፈጥረዋል
ዳሩ ግን እስካሁን ድረስ ወቅታዊ የፖለቲካ አሰላለፎችን ባህርይ ከነዓላማቸው ዘርዘር ባለ መልኩ ያቀረበ የለም ይህ አጭር ጽሑፍ የፖለቲካው አሰላለፍ ምን እንደሚመስልና ንጹህና ውጤታማ ሽግግር ለማምጣት ሊኖረው የሚችለውን ፋይዳ ምን ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል ይህም ልዩነቶቻችንን ያለምንም መሸፋፈን በይፋ ለውይይት ለማቅረብ ሊረዳ ይችላል እንዲህ አይነት ውይይቶችም የጋራ መግባባትና ግንዛቤ በመፍጠር ትግሉን ይበልጥ ሊያቀላጥፉ ይችላሉ   

ቀጥታ ወደዋናው ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ቀጥለው የተዘረዘሩትን ማሳሰቢያዊ ነጥቦች ላንሳ! አንደኛ ይህ ጽሑፍ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዲሁም በቴሌቪዢንና በሬዲዮ የተደረጉ ውይይቶችንና ጽሑፎችን እንደ መረጃ ተጠቅሟል። ሁለተኛ ጽሑፉ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ ስለኢትዮጵያ ሕዝባዊ ትግል ስለሚያሳስባቸው ድርጅቶች ቢሆንም ሁሉንም ለመቁጠር ዓላማ የለውም ዋና ዋናዎችን ግን ለዐብነት ይጥቅሳል። ሦስተኛ ጽሑፉ የሚያወግዘው ወይም የሚደግፈው ድርጅት ወይም ግለሰብ የለም ዳሩ ግን ለምሳሌነት የቀረቡ ይኖራሉ ይህም ቢሆን ዓላማው አንባቢያን የራሳቸውን ግምት ወይም ግንዛቤ እንዲወስዱ እንጅ አድሎ እንዲያደርጉ አይደለም። አራተኛ የጽሑፉ ዋና ዓላማ ሕዝባዊ ትግሉን ለማገዝ  እየተደረጉ ያሉትን አካሄዶች ከአገራችን ጥቅም አኳያ እንድንመረምራቸው መጋበዝ ነውፖለቲካዊ አሰላለፎች

ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከተው ፖለቲካዊ አሰላለፎች ሁለት ትይዩና የማይገናኙ ዐበይት መስመሮችን ይዘዋል መስመሮቹ ከዚህ በፊት የሚታወቁ ቢመስሉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ገዝፈው አካል ይዘው እየታዩ ነው አንዱ መስመር ከሌላው በአንፃሩ የተሰመረ ስለሆነ ተቃርኗቸው ከባድ ቀውስ ሊያመጣ የሚችል ነው ዳሩ ግን መስመሮቹ በውስጣቸው ሌሎች ተደራቢ ንዑስ መስመሮችም አሏቸው እነዚህ ዐበይትና ንዑሳን የፖለቲካ አሰላለፎች ብዥታና ጥርጣሬ  እየፈጠሩ ስለሆነ ለሰከነ ውይይት ከዚያም መግባባት ማብቃት ይጠበቅብናል ችላ ብለናቸው ወይም አለባብሰናቸው ብንሄድ ጠልፈው ይጥሉናል ካሰብነው እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም በእጅጉ ይገቱናል    

ከዚህ ቀጥሎ በግልጽ መታየት የጀመሩትን ፖለቲካዊ አካሄዶች መነሻቸውና መድረሻቸው ምን እንደሆነ ባጫሩ ላቅርብ! ከዚያም የትኛው አካሄድ አዋጭ ወይም አክሳሪ ሊሆን እንደሚችል እጠቁማለሁ


መስመር 1 ሕብረ ብሄራዊ

ይህ መስመር መነሻውና መድረሻው ሁሉንም ብሄረሰቦች በእኩልነት አቅፋ በሰላምና በብልጽግና የምትኖር ኢትዮጵያን መመስረት ነው በሕዝቦች መካከል ያሉትን ታሪካዊና ወቅታዊ ልዩነቶች በውይይት በመፍታት ለሁሉም እኩል ተጠያቂና አገልጋይ መንግስት  መመስረት ዋና ዓላማው ነው በመሆኑም ልዩነቶችን አቻችሎ ሙሉ ሃይልን ያለውን መንግስትን መጣል ላይ ማሳረፍ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ለዚህ አሰላለፍ በዚህ መስመር ከሚጓዙ በርካታ ድርጅቶች መካከል አርበኞች ግንቦት ሰባት ሸንጎ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ  ኢሕአፓ ዋነኞቹ ናቸው    


መስመር 2 ብሄር ተኮር    

ይህ መስመር መነሻው አንድ አይነት ሲሆን መድረሻው ግን የተለያየ ነው በዚህ መስመር ስር ንዑሳን መስመሮች አሉ በሕዝቦች መካከል ያሉት ታሪካዊና ወቅታዊ ልዩነቶች ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል ያለውን መንግስትን መጣል ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት ቢያምኑም መናበብ ግን አይታይባቸውምበአንዱ መስመር የተሰለፉት በሌላው መስመር የተሰለፉትን በጥርጣሬና በስጋት ይመለከታሉ በግልጽ ቃል በቃል ባይናገሩም ፉክክር ውስጥ የገቡ ይመስላሉ በመስመር 2 እየተጓዙ ያሉት በዋናነት ኦሮሞውንና አማራውን እንደሚወክሉ የሚናገሩ ድርጅቶች ናቸው ያላቸውን ልዩነት አጥርቶ ለማየት ይረዳ ዘንድ ጥቂት ማብራሪያ ልጨምር!       


ኦሮሚያ

በውጭው ዓለም የኦሮሞን ማኅበረሰብ ከማንም ተቋም ወይም ድርጅት በላይ እያስተባበረ የሚገኘው ጃዋር ሙሐመድ በሥራ አሥኪያጅነት የሚመራው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ነው ቢባል አይጋነንም  ይህ የሚዲያ ተቋም አንድ የፖለቲካ ድርጅት ከሚሠራው ያልተናነሰ ይሠራል በውጭው ዓለምና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረውን የኦሮሞ ወገን እያገለገለና ተቀባይነትን እያተረፈ ይገኛል  

ከበርካታ ሥራዎቹ ውስጥ ክርክርና ብዥታ ያመጣው ቅርብ ጊዜ ጃዋር በሚኒሶታ ያደረገው ንግግር ነው ብዙዎች ንግግሩ ኦሮሚያን እንደ አገር ሊመሰርት የሚችል ቻርተር እየተዘጋጀ እንደሆነና ቅርብ ጊዜም በዚሁ ላይ ለመወያየት በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ የኦሮሞ ወገኖች ለስብሰባ እየተዘጋጁ እንደሆነ ተረድተዋል አንዳንዶች ደግሞ የኦሮሞው ማኅበረሰብ ትግሉን በተመለከተ በመካከሉ የጠራ መግባባት እንዲኖር ለማድረግ የተዘጋጀ ሰነድ እንደሆነ ገምተዋል ጃዋርም የሰጠው ማስተባበያ ብዥታውን የሚጨምር እንጅ የሚያብራራ አይደለም  
  
ያም ሆነ ይህ እየተዘጋጀ ያለው የስብሰባ ጥሪ ማስታወቂያ እጅግ ግልጽ የሆኑ ነጥቦችን አስቀምጧል ኦሮሚያ በቅኝ ግዛት የተያዘች አገር እንደሆነች ወዘተረፈ ያትታል ይህን በተመለከተ /ር ተድላ በጥሩ ሁኔታ ጃዋርን ሞግቷል ምንም እንኳን ባንዳንድ መድረኮች ከአንድነት ሃይሎች ጋር አብሮ  እንደሚሠራ ለማብሰር እጅ ለእጅ ቢጨባበጥም የጃዋር የፖለቲካ መስመር ከብሄር የዘለለ እንደሆነ የሚያሳይ አሳማኝ ነገር አልታየም እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ኦሮሚያ እንጅ ኢትዮጵያ ተኮር አይደለም። አዎ አንድ ጉዳይ ግን ማንሳት ይቻል ይሆናል! የጃዋር ንግግሮችና ጽሑፎች ሁሉ የራሱን ወይም የሚመራውን ሚዲያ አቋም እንደሚያንጸባርቁ  አይታወቅም።    


አማራ

ለመጀመሪያ ጊዜ ለአማራው ደኅንነት የቆመ ድርጅት የተቋቋመው በፕሮፌሰር አስራት ተጋድሎ  ነበር ዓላማውም ከሌሎች የኢትዮጵያ ነገዶች ፍጹም በተለየ መልኩ ሕወሓት በአማራው ላይ የሚያደርሰውን የተቀነባበረ ግፍ ለመቋቋም ነበር ዓላማቸውን በደንብ ሳያሳኩ ራሳቸው የግፉ ቀማሽ ሆነው ያለእድሜያቸው አርፈዋል ከዚያ በኋላ ድርጅቱ ብሄራዊ አጀንዳ እንዲይዝ ተደርጓል በአማራ ነገድ ስምም ድርጅት ማቋቋም የማይታሰብ ሆኗል   

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ስለአማራው የሚያስቡና የሚሠሩ ተቋማት ተፈጥረዋል ዓላማቸው አማራውን «ከፈጽሞ መጥፋት» ማዳን እንደሆነ ቢያብራሩም ግባቸውና አካሄዳቸው ግን ይለያያል ሞረሽ ወገኔ  የዐማራ ድርጅት የዐማራውን ደኅንነትና ጥቅም አስከብሮ ከሌሎች ነገዶች ጋር በእኩልነትና በአንድነት እንዲኖር እንደሚታገል አሳውቋል በመሆኑም ይህ ድርጅት መነሻው ነገድ ቢሆንም መድረሻው ኢትዮጵያ ናት

ቤተ ዐማራ የተባለው ድርጅት ደግሞ  መነሻውም መድረሻውም የዐማራው ነገድ ይመስላል ልክ እንደ  ሞረሽ ወገኔ ዐማራው በእውነትም በልዩ መንግስታዊ ጥቃት ውስጥ እንደሚገኝ ያምናል ተጨባጭ ማስረጃዎችንም ያቀርባል ዳሩ ግን መድረሻው የዐማራን መንግስት ማቋቋም እንደሆነ ያብራራል ዐማራው ሌት ተቀን ስለኢትዮጵያ እያሰበ ለራሱ ግን የተጠቀመው እንደሌለ ያስረዳል እንዲያውም ኢትዮጵያዊነቱ በሌሎች ዘንድ እንደ ጠላት እንዲታይ እንዳደረገው ይሞግታል እንዲሁም ባሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ እንደ አገር እንደሌለችና በጽንሰ ሀሳብ ብቻ እንደምትገኝ ይከራከራል በመሆኑም ዐማራው የራሱን እድል በራሱ መወሰን እንደሚገባው ዳሩ ግን አብረው መኖር የሚፈልጉ ነገዶች ካሉ እንደሚያስተናግድ ይጠቁማል ከዚህ ባሻገር የትግል ግባቸውና ስልታቸው ገና ፍንትው ብሎ  ያልወጣው የጎንደር ኅብረት የጎጃም ኅብረት የወሎ ኅብረት የሚባሉ ድርጅቶችም እየተንቀሳቀሱ ነው         


አዋጭው መስመር

ወደ ዋናው ነጥብ እንግባ! ከተዘረዘሩት የፖለቲካ መስመሮችና አሰላለፎች ውስጥ ዘላቂና ስኬታማ እንዲሁም ሰላማዊ ሽግግር ሊያስገኝ የሚችለው የትኛው ነው? ይህ ጥያቄ እጅግ ከባድ ቢሆንም የኢትዮጵያን ታሪክ እንዲሁም ወቅታዊ ክስተቶችን ግምት ውስጥ በማስገባት የራሴን ግንዛቤ ላቅርብ  


1ኛው ተመራጭ መስመር

የሕወሓትን አምባና ብሄር ገነን መንግስት በእውነተኛ ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ መንግስት ለመተካት እጅግ ተወዳጁና አዋጩ መስመር የመጀመሪያው ነው የብሄረሰቦችን ማንነትና ምንነት አክብሮ  አንዲት ኢትዮጵያን ዳግም መመስረት ቀጥለው ስለተዘረዘሩትና ስለሌሎችም ምክንያቶች እጅግ ማራኪ ነው
§  ኢትዮጵያዊነት እጅግ የተለመደ ጽንሰ ሀሳብ ስለሆነ የሕዝባችንን ይሁንታ ለማግኘይ እጅግ ይቀላል
§  ኢትዮጵያዊነት ሁሉም ነገዶች የሚጠለሉበት ጃንጥላ ስለሆነ ስጋትና ጥርጣሬን ያስወግዳል
§  አረመኔውን መንግስት በተባበረ ክንድ ቶሎ ለመጣል ያስችላል
§  ከድንበር ጋር በተያያዘ ሊኖር የሚችለውን አላስፈላጊ የእርስ በርስ ጦርነትን ያስቀራል
§  ከተለያዩ  ነገዶች የተመሰረቱ ቤተሰቦች በአንድነትና በፍቅር ይጸናሉ
§  ችግርን በውይይትና በአንድነት ከመፍታት አኳያ ለልጅ ልጆቻችን አርአያ እንሆናለን
§  ያለንን እምቅ ሀብት ባግባቡ ለመጠቀም ያስችለናል
§  ለምሥራቅ አፍሪካና ለመላው ዓለም የሰላምና የእድገት ተምሳሌት ሆነን እንታያለን
§  በነዚህ ሁሉ ጥቅሞች የተነሳ የሞራል ልዕልና የአእምሮ ጤንነት እናገኛለን

ይህ መስመር በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ከሌላ ከምንም መስመር ጋር አይወዳደርምምጡቅና የሚታለም ነውዳሩ ግን መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን ስንመለከት ይህ መስመር ተግባራዊ የሚሆን አይመስልምላለፉት 25 ዓመታት ኢኮኖሚው ፖለቲካው ማኅበራዊ ኑሮው ሃይማኖቱ ትምህርቱ ወዘተ በዘር መነጽር ሲታይ ቆይቷል ይህም እቅድ ወጥቶለት በጀት ተይዞለት የተሠራ ነው ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና ታላላቅ የሚባሉ ሰዎች ሳይቀሩ ዘር  መቁጠር እየቀናቸው መጥቷል ከዚህ በፊት በብሄራዊ ስሜታቸው የሚታወቁ  ድርጅቶችና ግለሰቦች ወደ ነገዳቸው ወረድ ማለት እንዳለባቸው አምነዋል በመሆኑም ብሄራዊ እንጅ ብሄረሰባዊ የሆነ አካሄድ እንዲኖረን መጠየቅ ሊከብድ ይችላል 

በመሆኑም የአንድነት ሃይሉ ታላቅ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ቢባል የከበደ አይደለም እነዶክተር ብርሃኑ ነጋና ታማኝ በየነ ያለመታከት ልመና እስኪመስል ድረስ ነገደኞችን ብሄራዊ ስሜትና አጀንዳ እንዲኖራቸው ሲወተውቱ ማየት የተለመደ ሆኗል ከነዚህ ምክንያቶች በመነሳት የመጀመሪያው የፖለቲካ መስመር እየቀጠነና ተከታዮች እያነሱበት የሄደ ጽንሰ ሀሳባዊ ብቻ ይመስላል በመሆኑም  ይበልጥ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ሁለተኛው የፖለቲካ መስመር ሳይሆን አይቀርም       


2ኛው ተመራጭ መስመር

የመጀመሪያው መስመር አባጣና ጎርባጣ የበዛበት መስሎ ስለታየ ሳንወድ በግድ ሁለተኛውን መስመር ልንከተል ነው ማለት ነው ይህም ነገድን መነሻ ኢትዮጵያን መድረሻ ያደረገ የፖለቲካ አወቃቀር ማለት ነው የማንፈልገው ቢሆንም መሬት የረገጠና ጎልቶ እየወጣ ያለ አማራጭ ይመስላል ሕወሓት ካገኛቸው ስኬቶች ውስጥ ትልቁ ሕዝብ በነገድ እንዲደራጅ እንዲተዋወቅ እንዲነጋገር ማድረጉ ነው በተቃዋሚ ጎራ ያለነው ሳንቀር በአደባባይ እያወገዝን በተግባር ግን የምንኖረው ሆኗል ነገድ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ለመናገር የሚቸግራቸው ብዙ ኦሮሞ  ወገኖቻችን አሉ ከዚህ በፊት በብሄራዊ ስሜቱ የሚታወቀው የሰሜኑ ሕዝብ ሳይቀር በነገድ መደራጀት የውዴታ ግዴታ እንደሆነ አምኗል ይባስ ብሎም የራሱን መንግስት መመስረት እንዳለበት የሚከራከሩ እየተነሱ ነው ይህ እየሆነ ባለበት ሁኔታ ብሄራዊነትን ብቻ ማዕከሉ ያደረገ ሽግግር እናድርግ ማለት ምናባዊ ይመስላል ይህ አባባል የአንድነት  ሃይሎችን እጅግ እንደሚጎዳ ይታወቃል! ግን ሃቅ ነው       

ይህ ከሆነ ከምንጠብቀውና ከምንመኘው ሁሉ በአንድ ደረጃ ዝቅ ብለን የምንወዳትንና የምንሳሳላትን ኢትዮጵያን መፈለግና ማግኘት ይጠበቅብናል ይህም ማለት ኦሮሞውም ዐማራውም ሶማሌውም ሌላውም ሕዝብ ራሱን የሚወክል ድርጅት ፈጥሮ ደኅንነቱንና ጥቅሙን እንዲያስከብር መፍቀድ ማበረታታ ሊያስፈልግ ነው ዳሩ ግን ይህ የሚሆነው ኢትዮጵያ የምትባል ልዑአላዊ አገር እንዳለች ሲያምኑና በጋራ ለሚዘጋጀው ለሕገ መንግስቷም ሲገዙ ነው የፌዴራል አይነት ሥርዓት ቢመስልም ከተለመደው ግን የተለየ ነው መሠረቱ ነገድ ነውና! ይህን መስመር የምንከተል ከሆነ ቀጥለው የተዘረዘሩትንና ሌሎችንም ጥቅሞችን እናገኛለን ግልጽነት ተጠያቂነት እኩልነትና ፍትሕ ወዳጅ የሆነ የሽግግር አካል ከተገኘ ይህ መስመር ደህና ሊያስኬድ ይችላል          
§  ይህ አይነት ፖለቲካዊ አወቃቀር ገሃዱን ዓለም ስለሚያንጸባርቅ ሁሉንም ነገዶች በቀላሉ ለማስተባበር ያስችላል
§  ሁሉም የሚሳተፍበት ሕገ መንግስትና ብሄራዊ መንግስት ስለሚመሰረት በነገዶች መካከል ስጋትንና ጥርጣሬን መፈራራትንም ያስወግዳል
§  ሁሉም ነገድ የራሱን ባህል ቋንቋውን ጨምሮ ማሳደግ ስለሚችልና ራሱንም በራሱ ስለሚያስተዳድር እርካታና አመኔታን ያገኛል ይህም በሂደት ከዘር ፖለቲካ ወጥቶ  በጠቅላላ የሰው ልጅ መብትና ግዴታ ላይ የተመሰረተ ሥርዓት እንዲገነባ ያበረታታዋል
§  የመገንጠልና የጦርነት ስጋቶች አይኖሩም
§  በቀላሉ ሊገነባ የሚችል ሥርዓት ስለሆነ ሽግግሩን ያፋጥናል ባእዳን ሃይሎች እንዳይገቡ ያደርጋል


የማይፈለገው መስመር

በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ መስመር 1 ወይም መስመር 2 ለጉዟችን ካልተመረጡ እስካሁን ስንፈራውና በለሆሳስ ስናዋጋው የነበረው መዓት ይወርድብናል ይህውም ኦሮሞው አማራውና ሌላውም ነገድ የየራሱን መንግስት መስርቶ ራሱን የቻለ አገር ይሆናል ኢትዮጵያ የሚለው ስም በታሪክ መዛግብት ብቻ ሰፍሮ ይቀራል ይህ ከሆነ በየነገዶች መካከል ያለውን ድንበር ለመወሰን እጅግ አስቸጋሪ ስለሚሆን የማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል ይህም ለውጭ ጠላቶቻችን አጋልጦ ይሰጠናል እድገትና ብልጽግና ቀርቶ በሰላም ወጥቶ  መግባት ላም አለኝ በሰማይ ይሆናል ባጠቃላይ አገራችን ከሶማሊያም የባሰች ለዓለምም ጠንቅ የሆነት የምድር ሲዖል ልትሆን ትችላለች     


ማጠቃለያ

ይህ ጽሑፍ ዲያስፖራው ኢትዮጵያዊ ወገኔ ለዘላቂና ውጤታማ ሽግግር ሊያበረክተው የሚችለውን አስተዋጽዖ ከነስጋቶቹ ባጭሩ ጠቊሟል ምንም እንኳን አገር ቤት ካለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አኳያ ሲታይ ኢምንት ቢሆንም የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ግን ቀላል አይሆንም ያካበታቸው ልዩ ልዩ ካፒታሎች ለሰላማዊ ሽግግርም ሆነ ለእድገት እንዲሁም ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የላቀ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን በተለይ የአንድነት ሃይሉ ታሪካችንን ብቻ ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን እውነታ በሚገባ ሲተነትንና አግባብ ያለው የፖለቲካ መስመር ሲከተል ነው አገር ቤት ኦሮሞውና ዐማራው አንድነቱን እያጠናከረ ባለበት ሁኔታ ዲያስፖራው ወደነገድ የወረደበት ምክንያት እምብዛም አያሳምንም። በእውነት ትግላችን ለአገራችን ለምስኪኑ ሕዝባችንም ከሆነ ነገድ ዘለል ትግልን እንከተል።የመግባቢያ ሰነድ በጋራ በማዘጋጀት የነጻነት ጉዟችንን እንያያዘው!

ይህ ካልሆነ ብዙዎች ከነገዳቸው ጋር የተያያዘ ሥራና ስም እየመረጡ የግድ ብሄራዊ የአእምሮ ቅኝት ብቻ ይኑራችሁ ብሎ ለማስገደድ መሞከር ኪሳራን ያስከትላል ይህ ፈታኝ ወቅት ነውና ሁሉም አካል በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ስር ሆኖ የራሱን እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንዲመሰርት መፍቀድና ማገዝም ጥበብ ነው ያለበለዚያ ኢትዮጵያ ወይም ሞት የምንል ከሆነ መስዋዕትነቱ ለማንም አይበጅም ይህ ሲባል ግን ነገድ ተኮር ድርጅቶች እንደፈለጉ ይሆናል ማለት አይደለም ሁሉም ነገር በሥርዓትና በሕግ ሊመራ ይገባዋልና! ያለበለዚያ ሊመጣ የሚችል ችግር ካለ ተጠያቂ የሚሆኑበት መንገድ ክፍት እንደሆነ መገንዘብ ያሻል       

በመጨረሻም በውጭው ዓለም የሚገኙ የአንድነትና የነገድ ተኮር ድርጅቶች ሰከን ብለው ሊያስቧቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ላንሳ! አንደኛ ብቻቸውን በምንም መልኩ የኢትዮጵያን ሕዝብ ስለማይወክሉ አገር ቤት ካሉ አቻዎቻቸው ጋር በሚቻልበት መንገድ ሁሉ አብሮ መምከርና መናበብ ያስፈልጋል ሁለተኛ በመካከላችሁ የቱንም ያህል የሃሳብ ልዩነት ቢመጣ ባለመግባባታችሁ ተግባቡ እንጅ እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ ሙሉ ትኩረት የጋራ ጠላትን መታገል ላይ መሆን ይገባዋል ሦስተኛ ማንም አካል በብልጣብልጥነት ማንንም ሊሸነግል የሚችልበት ዘመን ላይ አይደለንም እያንዳንዱ አካል ለሚሠራው ሙሉ ሃላፊነትና ተጠያቂነት አለበት ሕዝቡ መከራ ያስተማረው ነውና ከዚህ በኋላ ለሚደናቀፍ አብዮት  ትዕግስትና ይቅርታ ያለው አይመስልምና እንጠንቀቅ    


ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

1 comment:

 1. Hi Teklu;

  I appreciate your effort to suggest honest ideas for the steps to be taken for future Ethiopia, based on the analysis of existing and anticipated scenarios. You deserve credit for this noble effort. In a time where many scholars are terrified to speak out (for fear of social media bullying), your courage is commendable.

  However, I instead of being informed and relieved, I have bogged down in a morass of inquiries and uncertainties. I really doubt if your preferred scenario (i.e., to let every individual join his/her ethnic group and anticipate a multi ethnic based national government setup) is as rosy as you painted it.

  Primarily, your assessment is focused on few and bigger ethnic groups (Amhara, Oromo, Tigrai, ...) as if they were cleanly demarcated from one another. I'm wondering if you have prescribed such formula to be applied in over 80 ethnic groups of the country. Secondly, I wonder how people residing in other ethnic regions are factored. For instance, over 6 million Amharas resides outside of Amhara region. Are they doomed to return to the land of their ancestries (most of whom don't even have any inkling of the region) ... or…. doomed to remain voiceless and treated “foreign” in "other ethnic regions"? Thirdly, what about people of mixed heritage? Fourthly, are you suggesting people like Dr. Berhanu to initially go back to Gurage zone before the national building? The last, but the most important, is have you imagined that the country will cheerfully embrace a complete balkanization (and God knows when) before the groups stitch themselves to a miraculous country. Don't you think group (ethnic) leaders would amass a huge ego and temptation to remain the leader of a "country" irrespective of resource and relevance? I'm sure you have witnessed the mushrooming of political parties, church denominations - not because there is fundamental difference. It is because it brings several power mongers to the drivers’ seat, which is not possible if it is united. In my opinion, it is risky business. There is Amharic saying: door masaded kamareh, dorohi'n be kok keyirat.

  Daniel
  Los Angeles

  ReplyDelete

የሁለቱ ሲኖዶሶች ፈተና

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕወሓት - መሩ መንግስት ከመጣ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመጋፈጥ ላይ ትገኛለች። ኦርቶዶክስንና አማራን በተለየ መልኩ ለማዳከም ከተቻለም ለማጥፋት የትግሉ ዓላማ አድርጎ...