Sunday 7 October 2018

ኢሕአዴግ በቀጣዩ ምርጫ ያሸንፋል?


መቅድም
ሀዋሳ በተካሄደው የኢሕአዴግ 11ኛ ጉባኤ ዶ/ር ዐቢይ ከ177 ድምጾች ውስጥ 176ቱን በማግኘት የኢሕአዴግ ሊቀ መንበርነታቸውን አስጠብቀዋል። ዶ/ሩ እንደሚያሸንፉ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሲገምቱ ነበርና ውጤቱ ብዙም አላስደነቀም። የእርሳቸውን ያህል አቅምና የሞራል ልዕልና ያለው ሰው እስካሁን ድረስ ከኢሕአዴግ ውስጥ አላየንምና! ይልቁንስ ብዙ ያወያየ የምክትሉ የአቶ ደመቀ ጉዳይ ነበር። እርሳቸውም 149 ድምጽ በማግኘት ወንበራቸውን አስጠብቀዋል። ምርጫውን ተከትሎም የኢትዮጵያን ሕዝብ በላቀ ደረጃ ለማገልገል እንደተዘጋጁ ሊቀ መናብርቱ ተናግረዋል። በተለይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ካሁኑ ማንነታቸውንና ምንነታቸውን ፈትሸው ካልተደራጁ በቀጣዩ ምርጫ በኢሕአዴግ ሊሸነፉ እንደሚችሉ ዶ/ር ዐቢይ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። ይህ ትልቅ ጉዳይ ነው! በርካታ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ይጋብዘናል። ለመሆኑ ከዚህ ንግግር በስተጀርባ የተቀመጡ መላምቶች ምንድን ናቸው? በውኑ ዶ/ሩ እንዳሉት ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ በቀጣዩ ምርጫ ያሸንፋል? ይህ ጽሑፍ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። ዓላማውም ኢሕአዴግ  በቀጣዩ ምርጫ እንደሚያሸንፍ ወይም እንደማያሸንፍ በእርግጠኝነት ለመናገር ሳይሆን መሪዎች የሚናገሯቸውን ንግግሮች ሁሉ እንደወረደ ከመውሰድ ተቆጥበን ጉዳዮችን ሁሉ በአንክሮ መመርመር እንደሚገባን ለማመላከት ነው።         

የዐቢይ መላምቶች  

ለመሆኑ ዶ/ር ዐቢይ ኢሕአዴግ በመጪው ምርጫ ማሸነፍ እንደሚችል የጠቆሙት ምንን መነሻ አድርገው ይሆን?  ወይም ኢሕአዴግን አግዝፈው ተፎካካሪ ፓርቲዎችን አሳንሰው ለማየት ያስቻላቸው ምክንያት ምንድን ነው? ከንግግራቸውና ባጠቃላይ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ካሉት ለውጦች በመነሳት የሚከተሉትን ምክንያቶች ማቅረብ ይቻላል 

1ኛ ኢሕአዴግ ከምንም ጊዜ በላይ የሕዝብ ቅቡልና እንዳለው ዴሞክራሲያዊ ለውጥና ልማትም ለማምጣትም እንደሚችል ዶ/ሩ አምነዋል። በተወሰነ መልኩ ይህ ነጥብ ገዥ ይመስላል። የሕዝብን ብሶትና ትግል ከብዙ ማቅማማት በኋላ ለመቀላቀል የቻለው የእሳቸው የለውጥ ቡድን ሰላማዊ በሆነ ፖለቲካዊ ጥበብ የሕወሓትን መሠረት ከአራት ኪሎ መንቅሎ በመጣሉ ልዩና ታሪካዊ ድርሻውን ተወጥቷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከከተማ እስከ ገጠር ያለውን ድጋፍ በታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎች አሳይቷል። ከኤርትራና ከሌሎች የጎረቤት ሀገሮች ጋር የነበሩትን መፋጠጦች ባጭር ጊዜ መፍታት መቻሉም ሌላው የዐቢይ ስኬት ነው። ይህን ተከትሎም ዓለም አቀፋዊ ድጋፍና እውቅና አግኝተዋል። ይህ ሁሉ ድል የተገኘው በጥበብና በሚገርም ትዕግስት ቅቡልነትም እንደሆነ ይታመናል። እነዚህ ወሳኝ እሴቶች ግን በተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ እንዳልተገኙ እንዳልታዩ ዶ/ሩ ሳያስቡ አልቀሩም። ይሁንና እነዚህ ብርቅዬ ለውጦች የመጡት መጀመሪያ በሕዝብ ትግል ከዚያም በለውጡ ቡድን እንጅ በኢሕአዴግ አለመሆኑን በግልጽ እናውቃለን።

 2ኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እስካሁን ድረስ ያሳዩት አካሄድ እዚህ ግባ የማይባልና ኢሕአዴግ ካለው ቁመና ጋር በፍጹም የማይወዳደር እንደሆነ ዶ/ሩ ገምተዋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከሚገባው በላይ መብዛታቸው ብቻ ሳይሆን የያዟቸውም የመስመር ልዩነቶች በቀላሉ የሚታረቁ አይደለም ብለው ሳይገምቱ አልቀረም ዶ/ሩ። በመሆኑም አስተማማኝ ውህደት፣ ግንባር፣ ቅንጅት ወይም ንቅናቄ ለመፍጠር እንደማይችሉ ዶ/ሩ የገመቱ ይመስላል።

በእርግጥም ዶ/ር ዐቢይ ከተሾሙ በኋላ ፓርቲዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ሳይጋቡ አልቀረም። ጥቂቶች ልማድ በሚመስል መልኩ የዐቢይን መንግስት ልባቸው አልተቀበለውም። ኢሕአዴግ እስካለ ድረስ ሰላምና ዴሞክራሲ ልማትም እንደሌለ ይሞግታሉ። በመሆኑም ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት  እንዲቋቋም ይፈልጋሉ። እንዴትና ለምን እንደሚቋቋም ግን የጠራ ሀሳብ አላቀረቡም ወይም እንዲቋቋም  ለሚፈልጉት የሽግግር መንግስት የሚያበቃ አቅም እንዳላቸው አላስመሰከሩም። እነዚህ አይነቶቹ ተፎካካሪ ሳይሆን እንደ ድሮው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢባሉ የተሻለ ነው።     

በአንጻሩ ደግሞ የሽግግር መንግስት የሚቋቋመው ሕገ መንግስቱም ሊቀየር የሚችለው በእኛ መቃብር ላይ ብቻ ነው ብለው የሚፎክሩም አሉ። ሁሉም ጉዳይ አሁን ባለበት ደረጃ መካሄድ እንዳለበት ይከራከራሉ። ሌሎቹ ደግሞ አሁን ያለው ዘውግ መር ፌደራሊዝም ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመመስረት ፍቱን መርህ እንደሆነ ይሞግታሉ። እንዲያውም ከብሄራዊ አጀንዳዎች ይልቅ ለዘውግ አጀንዳዎች የሚጨነቁ የሚጠበቡ ናቸው። እነዚህ ሁለቱ የፓርቲ አይነቶች በዚህ አቋማቸው ከኢሕአዴግ ጋር አንድ ይመስላሉ። በመሆኑም ረዳት ወይም ከፍ ሲል ተባባሪ ፓቲዎች ቢባሉ ይመጥናል።    

ሌሎች ደግሞ የዘውግ ፖለቲካ ውሎ አድሮ እንደማያዋጣ እንዲያውም ወደ መከራ እንደሚወስድ ኢትዮጵያንም ሊበታትን እንደሚችል የሚያምኑ ለማሳመንም ጥረት የሚያደርጉ ናቸው። ቋንቋን ሳይሆን አካባቢን መሠረት ያደረገ ፌደራሊዝም እንደሚያዋጣ ያምናሉ። እነዚህን ደግሞ በዶ/ር ዐቢይ አባባል ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብንላቸው አይበዛባቸውም። ይሁንና እነዚህ ፓርቲዎች በደንብ ተደራጅተው ለምርጫ የሚያበቃ ቁመና መያዝ አለመያዛቸውን ከራሳቸው በስተቀር የሚያውቅ የለም።  
    
ከላይ ከተዘረዘሩት የፓርቲ አይነቶች የተለዩም አይጠፉም። ኢትዮጵያ ያለችበትን እጅግ ፈጣን ለውጥ ሲመለከቱ ሕዝቡ ለዶ/ር ዐቢይና ለቡድኑ የሰጠውን ድጋፍ ሲያዩ የተደናገጡ ግራ የተጋቡ የበታችነት ስሜት ያገኛቸው አሉ። እነዚህ ፓርቲዎች ስማቸውን በምርጫ ቦርድ መዝገብ ላይ ብቻ አስፍረው ባሉበት የደነዘዙ ናቸው። የሚካሄደውን ጉዳይ ከመከታተልና ከመስማት ውጭ እንቅስቃሴ አይታይባቸውም። ተፎካካሪ ከሚባሉ ታዛቢ ፓርቲዎች ቢባሉ የተሻለ ነው።     

በመሆኑም ግልጽና ነጻ ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ ከላይ የተዘረዘሩት ተፎካካሪና ተባባሪ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ ለዘመናት ይደግፉኛል ከሚላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያገኘውን ድምጽ ይጋራሉ። ሊያሸንፉም ይችላሉ። ኢሕአዴግ ድሮስ በጡጫ እንጅ በምርጫ አሸንፎ አያውቅ! ኢሕአዴግ በነጻና ገለልተኛ ምርጫ የማያሸንፍባቸው ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።        

ኢሕአዴግ በምርጫ የማያሸንፍባቸው ምክንያቶች

በመሠረቱ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚጠናከሩበትን ሁኔታ ያመቻቻል እንጅ የራሱ ፓርቲ በምርጫ እንደሚያሸንፍ ተማምኖ በተለይ በዚህ ወቅት በይፋ ባይናገር ይመረጣል። በእርግጥ ዶ/ሩ በውጭ የነበሩትንም በሀገር ውስጥ ያሉትንም ፓርቲዎች በደንብ መርምረዋቸዋል። አቅማቸውን አይተዋል። ይህም ቢሆን ትክክለኛ ተፎካካሪ መሆን የሚችሉበትን ሜዳ ማዘጋጀቱ የበለጠ ይጠቅማል። ያለበለዚያ በድሮ ስማቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብለው ሊጠሯቸው ይገባል።       

ባጠቃላይ ሲታይ ዶ/ር ዐቢይ ተፎካካሪ ብለው ለሚጠሯቸው ፓርቲዎች ያላቸው ግምት ወይም እይታ በግልቡ ሲታይ ባብዛኛው እውነታነት ያለው ቢመስልም ትንሽ ድክመት ያለበት ይመስላል። እንዲህ አይነቱን እይታ ወይም ግምት ከመስጠት በፊት መሟላት የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉና ዋናዎቹን ቀጥለን እንመልከት። በቀጣዩ ምርጫ ኢሕአዴግ ከማያሸንፍባቸው ምክንያቶች ጥቂቶቹ እኒህ ናቸው።    
§  አሁን የተገኘውን ድል ያመጣው ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ሳይሆን ሕዝቡ ነው! የሕዝብ አስጨናቂ ትግል ገዥው ፓርቲ እንዲፈረካከስ አድርጓል። /ር ዐቢይና የለውጡ ቡድን ከሕዝብ ጎን በመቆማቸው ከታሰበው በላይ ለውጡ ሰላማዊና አጭር ሊሆን ችሏል። ይህ ማለት ሕዝቡ ኢሕአዴግን እንደ ብቸኛ አማራጭ ፓርቲ አይቶ ለማሸነፍ የሚያስችለውን ድምጽ ይሰጠዋል ማለት ግን ላይሆን ይችላል። ኢሕአዴግ አሁንም ኢሕአዴግ ነው! ከጥቂት መሪዎቹ በስተቀር ድሮም ሕዝቡን የገደሉ፣ በአካልና በሥነ ልቡና ሕዝቡን ያኮላሹ፣ የሀገሪቱን ሀብት ሙጥጥ አድርገው የበሉ፣ የሃይማኖት ተቋማትን ያጎሳቆሉ፣ ባህላዊ እሴቶችን የቀበሩ ወዘተ አሁንም ያለምንም ሀፍረት ኢሕአዴግን የሙጥኝ እንዳሉ ናቸው። ከዶ/ር ዐቢይና ከለውጡ ቡድን  በስተቀር  ይቅርታ እንኳን የጠየቁ የሉም። በመደመር ሰበብ የሠሩትን ወንጀል ረስተው አሁንም መምራት ይፈልጋሉ። እንዲያውም እስካሁንም ለውጡን የሚገዳደሩ ያልተደመሩ አባላት የሞሉበት ድርጅት ነው ኢሕአዴግ! በመሆኑም የተሻለ ተፎካካሪ ፓርቲ እስከመጣ ድረስ ወይም ኢሕአዴግ ራሱን እንደገና እንደ አዲስ ፓርቲ እስካልፈጠረ ድረስ ሕዝቡ ለዶ/ር ዐቢይና ለሚመራው የለውጡ ቡድን ሲል ብቻ ኢሕአዴግን ላይመርጥ ይችላል። የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም! ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ያነሰ እንጅ የላቀ የሞራል ልዕልና እንደሌለው ግልጽ ነው።        
§  የኢንጅነር ስመኘውን ሞት እንዲሁም በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ባሉት ከተሞች የተከሰተውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተከትሎ የጸጥታና የፍትሕ አካላት የወሰዷቸው እርምጃዎች በሕዝቡ ዘንድ ግርታንና ጥርጣሬን አስከትለዋል። የምርመራ ውጤቶች እጅግ የተድበሰበሱ አንዳንዶችም ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ መስለው የታዩ ናቸው። ንጹሐንን በአደባባይ የገደሉ ሳይያዙ ሆቴል ቁጭ ብለው የሚዝናኑትን ማፈስ ተጀመረ። የሕዝብ ትችት ሲመጣ ደግሞ ሺሻ የሚያጨሱ ሀብታሞችን ነው የያዘንው የሚል መግለጫ ተሰጠ። በመንግስት የሚሰጡትም ማስፈራሪያዎች አንዳንድ ድርጅቶችንና አካላትን በድፍን የሚያወግዙ ናቸው። እኒህንና ሌሎችንም እርምጃዎች ተከትሎ ቀላል የማይባል የኅብረተሰብ ክፍል በለውጡ ቡድን አቅምና ዓላማ ላይ 2ኛ እንዲያስብ እንዲሰጋም ሆኗል። ለ27 ዓመታት ሲገድል የነበረ የሕግ አስከባሪ ኃይል ቀስ በቀስ ተመልሶ እንደመጣም የተናገሩ አሉ። ይህ በዚህ ከቀጠለ አይደለም ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ምርጫ ሊያሸንፍ የለውጡ ቡድንም የሕዝብ መሠረቱን ሊያጣ ይችላል።              
§  በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በዘውግ የተደራጁ ፓርቲዎች የዘውግ ፖለቲካን ከጀመረውና ለፍሬ ካበቃው ከኢሕአዴግ ብዙም በማይተናነስ ደረጃ ደጋፊዎች ተከታዮች አሏቸው። አንዳንዶቹ ውጭ የነበሩ ሌሎችም አዲስ የተቋቋሙ ናቸው። እነዚህ ዘውግ መራሽ ፓርቲዎች ወጣቱን በማነሳሳት ደረጃ ብዙ እየሄዱ ነው። ብሄረሰቦቻቸው በኢሕአዴግ ምን ያህል እንደተጨቆኑ ምን ያህል መብቶቻቸው እንደተሸራረፉ በስሜትና በመረጃ በማስረጃም ደግፈው ያቀርባሉ። ይህ የተጎጅነት ስሜት አባላትን በቀላሉ ለማፍራት አስችሏቸዋል። በመሆኑም ሁኔታዎች በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነ በብዙ ቦታዎች ኢሕአዴግ ለማሸነፍ የሚያስችለውን ድምጽ ላያገኝ ይችላል።     
§  ቀላል የማይባለው ኢትዮጵያዊ በዘውግ ሳይሆን በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካን ይመርጣል። በተለይ የተማረው አካል እንዲሁም አዲስ አበባን ጨምሮ በታላላቅ ከተሞች የሚኖረው ወገን ይህን አብዝቶ ይፈልጋል። በተጨማሪም ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተወለዱ ኢትዮጵያውያንም ሞልተዋል። የዜግነት ወይም የብሄር እንጅ የብሄረሰብ ቋንቋ አይገባቸውም አይዋጥላቸውም። በመሆኑም የብሄረሰብ ፖለቲካ አባት የሆነውን ኢሕአዴግን ሊመርጡ አይችሉም። ይህም በተደጋጋሚ ባለፉት ምርጫዎች ታይቷል።      
§  እንዲሁም በ97 ምርጫ ተፎካካሪው ወገን እንዲያሸንፍ ያስቻለው የቅንጅት መንፈስ አሁንም የማይደገምበት ምክንያት የለም። ቅንጅት የተቋቋመው አጭር በሚባል ጊዜ ነበር። እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ የነበረውን የዚያን ጊዜውን ኢሕአዴግን ሊዘርረው ችሏል። አሁንም የቀድሞውን ቅንጅት የፈጠሩና ለፍሬ ያበቁ መሪዎችና አባላት አሉ። ፓርቲዎቻቸውን አጋጭተው እንደገና የማይቀናጁበት ምክንያት የለም። የቅንጅት አይነት መንፈስ ከተፈጠረ ኢሕአዴግ ታሪክ የሚሆንበት ምርጫ ሊሆን ይችላል።    

ማጠቃለያ

/ር ዐቢይ በቀጣዩ ምርጫ ኢሕአዴግ እንደሚያሸንፍ ፍንጭ መስጠታቸው ብዙም አሳማኝ አይደለም። ከላይ እንደተጠቆመው ኢሕአዴግ ምርጫውን እንደማያሸንፍ የሚያመላክቱ ዐበይት ጉዳዮች አሉ። እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ ከዶ/ር ዐቢይና ከሚመሩት የለውጥ ቡድን እንጅ ከኢሕአዴግ አቅም በላይ ናቸው። ኢሕአዴግ ምርጫውን ያለማጭበርበር እንዲያሸንፍ ከፈለገ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለውጦና እውነተኛ ንስሐ ገብቶ ቀኖናውንም በሚገባ ጨርሶ እንደ አዲስ መደራጀት ይኖርበታል። ይህ ደግሞ የሚታሰብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድክመታቸውን ተቋቁመው በመጣመር ምርጫውን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ መገመት ይበልጥ አሳማኝ ነው። በመሆኑም ዶ/ሩ ያስተላለፉት የኢሕአዴግ ያሸንፋል ንግግር ከላይ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች በደንብ ካለማጤን የቀረበ ይመስላል። ማለትም በዶ/ር ዐቢይ የለውጥ ቡድን እና በኢሕአዴግ መካከል ምንም አይነት ልዩነት እንደሌለ ከማሰብ የተነሳ የተናገሩት ይመስላል። ዳሩ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያከበረውና የተከተለው ዶ/ር ዐቢይንና የሚመሩትን የለውጥ ቡድን እንጅ ኢሕአዴግን አይደለም። የእርሳቸውም ታላቅ ፈተና የፓርቲያቸውንና የሕዝቡን ጥያቄዎች እንዴት እንደሚያጫውቷቸው ግልጽ ያለ መንገድ አለመኖሩ ነው።     

ይህም ማለት ለቀጣዩ ምርጫ አብዝቶ መጨነቅና መዘጋጀት ያለበት ዶ/ሩ የሚመሩት የለውጡ ቡድን ነው። ኢሕአዴግን እንደ ፓርቲ የለውጡ ቡድን ከደረሰበት ደረጃ ማድረስ እስካልተቻለ ድረስ እንደሚያሸንፍ መተንበይ ምንም አይነት ምክንያት የለውም። ለለውጡ ቡድን ከርዕዮት አኳያ እጅግ የሚቀርበውና የሚመቸውም ከኢሕአዴግ ይልቅ በዜግነት ፖለቲካ የተሰለፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ናቸው።  ኢሕአዴግን እንደገና ለማስተካከል ከመድከም ይልቅ ዜግነት ላይ የተመሰረተ አዲስ ፓርቲ ማቋቋም ይቀላል ይሻላልም። ይህም ማለት በዜግነት ፖለቲካ የሚያምኑ ፓርቲዎች ሁሉ ጋር አንድ ላይ በመሆን አንድ ግዙፍ ብሄራዊ ድርጅት መፍጠር ይቻላል። ማለትም ዶ/ሩ የሚመሩት የለውጥ ቡድንና ለዜግነት ፖለቲካ የተሰለፉ ፓርቲዎች ሁሉ ያሉበት ቅንጅት፣ ግምባር፣ መድረክ፣ ንቅናቄ ወይም ውህደት መፍጠር ይቻላል። ይህም የሚቻለው ለፓርቲ ኅልውና በሚያናውዛቸው ሳይሆን ለኢትዮጵያ በሚያስቡ ኃይሎች ብቻ ነው። ይህም ከመደመር ዘርፎች ውስጥ አንዱ ሆኖ ሊታይ ይገባል! ይህ መስመር እውን ከሆነ ምርጫውን ለማሸነፍ ከመርዳቱም በተጨማሪ ኢትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃ ለዘላለም በክብር እንድትኖር ያስችላታል። አዴፓና ኦዴፓ የጀመሩትን የስም፣ የዓርማና የመስመር ለውጥ በማፋጠን ቶሎ ወደ አንድነት ማምጣት ይቻላል።          

ይህም ባይሆን ፓርቲዎቹ ተፎካካሪ እስከተባሉ ድረስ ከሚፎካከራቸው ከኢሕአዴግ ጋር አቻ ሊያደርጓቸው የሚያስችሏቸውን ሁኔታዎች ማሟላት ያስፈልጋል። ላለፉት ዓመታት ፓርቲዎች በደህንነት ተቋማትና በምርጫ ቦርድ የተቀነባበረ ሴራ ተበትነዋል፣ ተዳክመዋል፣ እርስ በርሳቸውም እንደ ጠላት እንዲተያዩ ተደርገዋል፣ መሪዎቻቸው በአካል በሥነ ልቡና እንዲዳከሙ ተደርገዋል። አሁንም ቢሆን መንግስትና ፓርቲ ተለይተው አልተቀመጡም። በዚህ ሁሉ ሁኔታ ፓርቲዎቹ ሁሉ በደጁ ከሆነው ከኢሕአዴግ ጋር ተፎካክረው ያሸንፉ ማለት በፍጹም አሳማኝ ፍትሐዊም አይደለም። በመሆኑም መገናኛ ብዙኃንና ምርጫ ቦርድ ገዥውን ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በፍጹም እኩልነት ማስተናገድ ይኖርባቸዋል። በተለይ ምርጫ ቦርዱ ሙሉ በሙሉ ፈርሶ ኢሕአዴግና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ ታማኝነት ያለው ተቋም አድርገው ካላቋቋሙት ምርጫው አይደለም በተፎካካሪ ፓርቲዎች በሕዝቡም ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም       
  
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!     

አስተያየት ካለዎት teklu.abate@gmail.com ይላኩልኝ!



No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...