Thursday 22 November 2018

በማጭበርበር ያልተነካካ ማንም የለም!


ካይሮ በሚገኘው የአሜሪካን ዩኒቨርስቲ የተለመደ ሥራዬን ለማከናወን ወደ መማሪያ ክፍሉ እንደገባሁ «ፕሮፌሰር እንኳን ደስ አለህ!» አለች በእድሜ ጠና ያለችው ታታሪ ተማሪዬ! «ሴት ፕሬዚደንት አገኛችሁ» አለች አከታትላ ምላሼንም እንኳን ሳትጠብቅ። «በጣም አመሰግናለሁ ብዬ ሳልጨርስ ወጣ ያለ ባህርይ ያለው ተማሪዬ «ግን እኮ ቦታው ሴረሞኒያል ብቻ ነው አለ ለስለስ ባለ ድምጽ። «ቢሆንስ? ታውቃለህ? አፍሪካ ውስጥ ሁሉም ሥልጣን ሴረሞኒያል ነው። ባይሆንማ ለውጥ በታየ ነበር» አለች ሌላዋ ተማሪ የመናደድ ምልክት እያሳየች! «ግን ሴረሞኒያል ቢሆንም ብዙ መሥራት የሚቻልበት ሥልጣን ነው! ለሴቶች ሁሉ ብዙ አንድምታዎችም አሉት በማለት ዘለግ ያለ ትንተና ሰጠች መጀመሪያ ጉዳዩን ያነሳችው። 


ብዙ ተማሪዎች ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡ ስለሆነ ሴቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ትርጉም ሰጥተው በጥሞና ይከታተላሉ። አብዛኞቹ በተነሳው ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት እንደተዘጋጁ ሳይ «ለማንኛውም ከሳምንት በፊት የተዋቀረው አዲሱ ካቢኔ ግማሹ ሴቶች ናቸው። ያውም መከላከያውንና ደህንነቱን የሚመሩት ሴቶች ናቸው። ይህ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም አሳታፊነትን በተመለከተ ትልቅ ምልክት ይሆናል። በተለይ ለሴት ልጆቻችንና ተማሪዋቻችን መልካም አርአያ ይሆናል በማለት ጉዳዩን አጠቃልየ ወደ መደበኛ ሥራዬ ገባሁ። 

በካቢኔውና በፕሬዚደንቷ ሹመት ላቅ ያለ ደስታ ተሰምቶኛል። ምንም እንኳን ማድነቅም ሆነ መደሰት ቆይቶ ሊመጣ ቢገባውም አነሳሱ ማለትም አጀማመሩ የተለየና ለዘመናት ጾታን በሚመለከት የተገነቡ ግንቦችን ያፈረሰ መዶሻ ስለሆነ እንደ ውጤት ሊቆጠር እንደሚገባ አምኛለሁ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ለዘመናት የጀርባ አጥንቱን በጉልበተኞች ተመትቶ ለመሞት ሲያጣጥር የነበረው የፍትሕ ተቋማችንን እንዲመሩ ወ/ሮ መዓዛ መሾማቸውን ሰማን። ይህም ሌላ የደስታ መነጋገሪያ ሆኖ ቆየ። እነሆ ዛሬ ደግሞ ወ/ሮ ብርቱካን ሚዴቅሳ የምርጫ ቦርድን እንድትመራ መሾሟን ሰማን! ሥራና ሠራተኛ ተገናኙ!  ብርቱካን ሚዴቅሳ ይህን የሚሊዮኖችን ድምጽ ሲሰርቅ የቆየውን ተቋም ፍጹም ነጻና ገለልተኛ በማድረግ ዘላቂነት ያለው ኢትዮጵያዊ ተቋም ማድረግ እንደምትችል ሙሉ እምነት አለኝ!  

በአጠቃላይ እስካሁን ያሉት ሹመቶች በተለይ ሴቶችን የሚመለከቱት የሚደገፉ ናቸው። ፍጹማዊነትን የምንፈልግ ካልሆነ በስተቀር ወይም ወንዶች ይልቅ ከሴቶች የተሻሉ ናቸው ብለን እስካላመንን ድረስ ጉዳዩ ለአድንቆት የተመቸ ነው። ማቃለልና ማጣጣል ብቻውን ብዙም ጠቀሜታ የለውም። በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ውዲህ መጠነኛ መነቃቃትን እያገኘ የመጣው ፓርላማችን ምስጋና ይገባቸዋል። በቀጣይነት ለተሿሚዎች እንቅፋት አለመሆን የሚሆኑትንም በጊዜ ማንሳት ሊለመድ ይገባል።    

ሌላው ትኩረትን የያዘውና ብዙዎችን ሌሊት ከእንቅልፋቸው የሚያስነሳቸው ጉዳይ በሌቦችና በገዳዮች በገፊያንና በአሰቃዮች ላይ እየተካሄደ ያለው እስር ነው! የመደመር አዲሱ ፍልስፍና ብቻውን እንደማያዋጣ ሲናገሩ የነበሩ ሁሉ ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ። ከተጠበቀው በላይ ዘመቻው ሰፋ ያለ በመረጃ የተደገፈና በቀላሉም የማያቆም ይመስላል። የሞቱትን አካለ ጎደሎ የተደረጉትን፣ የሥነ ልቡናና የሥነ አእምሮ ጠባሳ የደረሰባቸውን እንዲሁም ንብረታቸውን የተቀሙና ከሀገር እንዲሰደዱ የተደረጉትን ወገኖቻችንን ስናይ እስሩ ፍትሐዊ ነው። በሰፈሩት ቁና ሊሰፈር ይገባል! ግፈኞች ንጹሃን ኢትዮጵያውያንን ለማሰቃየት በዘመቻ ባስፋፏቸው እስር ቤቶች እራሳቸው እንዲያርፉ ማድረግ ፍትሕ ነው። ማንም ከሕግ በላይ እንዳልሆነ ማወቃቸው አግባብ ነው። አሁን ላሉትና ወደፊትም ለሚሾሙት ባለ ሥልጣናት የማይረሳ ትምህርት ይሆናቸዋል። ኢትዮጵያውያን አንድ መርሳት የሌለብን ጉዳይ ግን እነዚህ የታሰሩትና ገና የሚታሰሩት ፍጹም ገለልተኝነት ባለበት የዳኝነት ሥርዓት እንዲዳኙና ፍትሕ ምን እንደሆነ እንዲማሩ ማድረግ ላይ ነው።      

ይሁንና እስሩን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛል። ሦስቱን ብቻ ላንሳና የራሴን አተያይ ላስቀምጥ።  አንባቢም የራሱን ያስቀምጥ። 

መደመርና ማሰር እንዴት ይጣጣማሉ?  

በመሠረቱ መደመር የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ብትንትን ተደርጎ የተተነተነ አይደለም። ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ግን ሁሉንም ሰው ላያቅፍ ይችላል። መቀነስ (ሲጠብቅና ሲላላ) መልኩ ብዙ ነውና! አንዳንዱ ሰው በተፈጥሮው ማለትም ነፍስ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ራሱን ከለውጥ የቀነሰ ነው። በቤትም በጓደኛም፣ በጎረቤትም፣ በሥራ ቦታም ወዘተ ለውጥ የማይመቸው አለ ትናንትናን እየናፈቀ (ትናንትን ናፋቂዎች ከምትለዋ የሕወሓት አባባል የተወሰደች ናት) ዛሬን በጥርጣሬ የሚኖር ነገን ደግሞ አብዝቶ የሚፈራ ሰው ሞልቷል ይህ አይነት ሰው ተደመር ብትለው እስከ መስዋእትነት በሚያደርስ ኃይል ይፋለማል እንጅ አይቀበልም በተለያዩ ግላዊ ተጨባጭ ምክንያቶች የተነሳ ራሱን ከለውጡ የቀነሰም አለ መደመሩ የሚቀንስበት ነገር ሀብት ጥቅም ሥልጣን ተሰሚነት ወዘተ እንዳለ አጣርቶ የሚያውቅ ሰው ነው ይህም ይቅርታ ቢደረግለትም እንኳን ችግሩን ስለሚያውቃት ፍጹም ሊደመር አይችልም ቀድሞ የነበረውን ሀብት ወይም ሥልጣን ካገኘ ብቻ መደመር እንደሚችል አስቦ ጊዜ የሚጠብቅም አይጠፋም ይህን አይነቱን ሰው ዶ/ር ዐቢይ አልደመሩትም አይባልም ራሱን አስቀድሞ ቀንሷልና ባጠቃላይ ሲታይ ራሳቸውን በተለያዩ ምክንያቶች የቀነሱ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ!      
   
ብዙ የሚያሳስበው ግን በሥልጣን ዘመናቸው ዘግናኝ ግፍ የፈጸሙና የሀገሪቱን ካዝና የመዘበሩና በእዳ ባህር ውስጥ የከተቱ ሰዎች ጉዳይ ነው ከወንጀላቸው ግዝፈትና አሰቃቂነት የተነሳ ፍጹም ምህረት ቢደረግላቸውም እንኳ እውነት ነው ብለው የማያምኑ የማይቀበሉም ናቸው እኒህ ሰዎች ከቻሉ ለውጡን ማደናቀፍ ካልቻሉ መሰደድን ይመርጣሉ እንጅ መደመርን አይሿትም ታላላቅ የሕወሓት አባላትና የሌሎችም የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች አመራር አባላት የነበሩ ተጠቃሽ ናቸው በተለያዩ መንገዶች ለውጡን ሲያጥላሉ ለማደናቀፍም ሲሞክሩ የሚታዩት እኒህ ናቸው አነዚህ ስብስቦች አይደለም ሊደመሩ ቢተው እንኳን አርፈው የሚቀመጡ አይደሉም በመሆኑም የተሻለው ዘዴ ወደ ፍትሕ መውሰድ ብቻ ነው የሕግ በለሙያዎች እንደሚሉትም ይቅርታ ወይም ምህረት ይደረግላቸው ቢባል እንኳ ሕግ እንደማይፈቅድ ነው! ስለዚህ ሕግ ካልፈቀደ ራሳቸውም በይፋ ይቅርታ ጠይቀው የዘረፉትን መልሰው ለመደመር ካልፈለጉ ብቸኛው አማራጭ ፍትሕ መስጠት ነው በመሆኑም እስሩ ለታሳሪዎችም ለመላው ኢትዮጵያውያንም ፍትሕን የሚያሰፍን ብቸኛው መንገድ ነው! 

እስሩ ለምን ሕወሓት ላይ አነጣጠረ?

ይህ የማይረባ ጥያቄ ነው! የሚታይና የሚዳሰስ መረጃም ማስረጃም ያለው ጉዳይ ነው ከዚህ በፊት የፌደራል ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎች በሕወሓት አባላት የተያዙ እንደነበር ዓለም አቀፋዊና ኢትዮጵያዊ ጥናቶች የዘገቡት ነው እንዲሁም ባጋጣሚ ዋና ሓላፊ ከሌላ አካባቢ ከሆነ ይልቅ የሕወሓት ምክትል የሆነ ባለ ሥልጣን ወሳኝ ድምጽ አለው ከአቶ ኃይለ ማርያም ይልቅ ጀማሪው አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ የተሻለ የመወሰንና የማስፈጸም ቁመና ነበረው ባጠቃላይ ሲታይ ለይስሙላ በተወሰኑ የሥልጣን ቦታዎች የነበሩት ከሌላ አካባቢ የመጡ ሰዎች በአንድ የሕወሓት ካድሬ ይመራሉ በክልል መሥሪያ ቤቶች ሳይቀር ያለ ነው ይህ ጉድ በመሆኑም እስሩ የሕወሓት አባላትን ቢቀመጥል የሚገርም አይደለም ይሁንና የመወሰንም ይሁን የማስፈጸም አቅም የሌላቸው ባለሥልጣናት አይጠየቁ እያልኩ አይደለም እነሱም መጠየቅ አለባቸው! ደግሞም ከሁሉም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የታሰሩ አሉ ለምን ሕወሓት በዛ ብሎ መጠየቅ ገና ድሮ ሥልጣን ላይ እያሉ ነበር ያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥልጣን ሁሉ የሕወሓት እንደሆነ ሲናገር መስማትና እርምት መውሰድ ይበጅ ነበር ደግሞም እስሩ ገና ስላላለቀ የትኛው ወገን ሪኮርዱን ይዞ እንደሚቀጥል ገና አልታወቀም ግን ሕወሓትን የሚስተካከል እንደማይገኝ የተገመተ ይመስላል ለማንኛውም ሕወሓት ለሥልጣን ቦታዎች ባዋጣችው ልክ ለእስር ቤትም ማዋጣት ይጠበቅባታል እንግዲህ ሰው በሥራው እንጅ በኮታ አይታሰር!    

        በወንጀል የተነካኩ ባለሥልጣናት ሁሉም ለምን አልታሰሩም?

በጣም የሚያከራክረው ምናልባትም ክፍፍል እንዳያመጣ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ ቢኖር ይህ ነው ወንጀል ሠርተው ግን የተደመሩ የሚመስሉ አልታሰሩም ባሁኑ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ውስጥ ከሕወሓትም ከሌሎችም የኢሕአዴግ ድርጅቶች ተወክለው የሚያገለግሉ ግን ወንጀል ሢሠሩ የነበሩ ያልታሰሩበት ምክንያት ገና አልታወቀም/ር ዐቢይ ዛሬ ኅዳር 13 ለፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ እንደተመለከተው በኢሕአዴግ ዘመን ክወንጀል የጸዳ ባለሥልጣን አይገኝም ቃል በቃል ሲቀመጥ «ከትናንሽ ማጭበርበር እስከ ታላላቅ ማጭበርበር ያልተነካካ የለም» ብለዋል የተነካካው ሁሉ ቢታሰር እስር ቤቶች እንደማይበቁ ምናልባትም ለዚሁ ጉዳይ ከተማ መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ሁሉንም አስሮ መቀለብም እንደማይቻል ይልቁንም ትኩረት መደረግ ያለበት ዋና ዋና ጉዳዮችን ለይቶ ለሕግ ማቅረብና የቀረውን በመቋቋም ላይ ላለው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን መተው ላይ ነው ብለዋል /ር ዐቢይ  

ይህ ሐቅ ነው! በኢሕአዴግ ዘመን ያልተነካካ የለም እስረኛን ያላሰቃየ የደኅንነት ካድሬ አታገኝም ያልዘረፈ ባለሥልጣን አታገኝም የመሥሪያ ቤት የጽሕፈት መሣሪዎችን ያልሸጠች ጸሐፊ ላታገኝ ትችላለህ ከጽዳት እቃዎች ያልሰረቀች የጽዳት ሠራተኛ ላታገኝ ትችላለህ በመሥሪያ ቤት መኪና ያልነገደ ሾፌር አታገኝም ያላጭበረበረ እቃ ግዥ ሠራተኛ አታገኝም ጉቦ ሳይከፍል የተሾመ የቤተ ክርስቲያንና የመስኪድ አስተዳዳሪ ላታገኝ ትችላለህ ጉቦ ሰጥቶ በዘርና በዘመድ ያለ ችሎታ የተሾመ አክሊል ተሸክሞ የሚንገላወድ ክብርና ሞገስ የራቀው ጳጳስ ታገኛለህ የተገዛ ድግሪ ተሸክመው ራሳቸውን ሊቅ አድርገው የሚያዩ ደናቁርትን በየቢሮው ታገኛለህ ቤተ ክርስቲያን ወይም መስኪድ ሃጅ የሆነ አሸዋና በርበሬ ቀላቅሎ የሚሸጥ ነጋዴ እንደ ልብ ታገኛለህ የሆስፒታል መድኃኒት አውጥቶ ለግል ክሊኒክ የሚሸጥ ሀኪም በደንብ ታገኛለህ ሌባውን ሰድዶ የተሰረቀውን ሰው በዱላ የሚያበራይ ፖሊስ ታያለህ ማርክ በገንዘብ ወይም በሌላ ጥቅም የሚያድል መምህር በዩኒቨርስቲም በትምህርት ቤትም ታገኛለህ አዳዲስ ሕንጻዎችና መንገዶች ተመርቀው ዓመት ሳይሞላቸው ተፈረካክሰው ታያለህ ፍርድ ቤት ከሄድክ የሚያሸንፈው እውነት ሳይሆን የገንዘብህ መጠን ነው ማን ያልተነካካ አለ!  
         
ባጠቃላይ ሲታይ በኢሕአዴግ ዘመን የተሰረቅነው ገንዘባችንን ብቻ ሳይሆን መተማመንን ፍትሕን እውነትን ሞራልን ባጠቃላይ ሰው መሆንንም ነው! ባህላዊ ሃይማኖታዊ ብሄራዊ እሴቶቻችንንም ተዘርፈናል አንዱ ሌላውን ከመቸም ጊዜ በላይ በጥርጣሬ እንዲያይ ተደርጓል ሀገራችን ያለባት እዳ የትኛው ትውልድ ከፍሎ እንደሚጨርሰው ሲታሰብ አእምሮ ያሳጣል ይህን ሁሉ ቀውስ የጸነሰው የወለደው ማዳበሪያና ፍግ እየጨመረ ያሳደገው ያጎለመሰው አዛውንትም ያደረገው በዋናነት ሕወሓት ከዚያም ኢሕአዴግ ነው! ሕዝቡ ይቅርታ ቢያደርግላቸውም እንደ መንግስት መቀጠል የሚያስችል የሞራል ልዕልና የላቸውም ኢሕአዴግ ሙሉ በሙሉ መፍረስ ያለበት የክፍለ ዘመኑ አሳፋሪ ተቋም ነው ለዚህም ነው እንደነ ዐቢይ ያሉ ሰዎች ድርጅቱን አፍርሰው ብሔራዊ አጀንዳ ካላቸው ድርጅቶች ጋር ቢዋሃዱ የተሻለ እንደሆነ ኢሕአዴግ በቀጣዩ ምርጫ ያሸንፋል? በሚል ሌላ ጽሑፌ ላይ የጠቆምኩት!  

ዋናው ነጥብ ግን የእስሩ ዘመቻ ለምን ዘራፊዎችና ገፊያን የሆኑ የኢሕአዴግ አባላትን በሙሉ አላካተተም የሚል ነው የዶ/ር ደብረ ጽዮንም ጥያቄ ከዚህ ብዙም አይለይም መልሱን በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ዶ/ር ዐቢይ በግልጽ ነግረውታል አንደኛ ሁሉም ሌባና ገፊ እኩል አይደለም! አንዳንዶች ከሌሎች የባሰ አይናውጣ ሌቦችና ገፊዎች ናቸው ሁለተኛ ሁሉም ይታሰር ቢባል እንኳ የሀገሪቷን ንብረት ስለዘረፈ በቂ እስር ቤቶች ለመገንባትና ቀለብ ለመስፈር አይቻልም! በመሆኑም ፍትሕን የሚጋፈጧት አብዝተው የሰበሰቡ ያተረፉ ናቸው ማለት ነው ጥያቄው አብዝቶ የሰበሰበውን ያተረፈውንም እንዴት እናውቃለን ከሆነ አምስት ወራት የወሰደ የምርመራ ውጤት እንዳለ ተነግሯል

ይሁንና የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር ይህን ነጥብ በቀላሉ የሚዘለው አይመስለኝም ለሕግ የሚመሩት ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም ታላላቅ ማጭበርበሮች እንዴት እንደሚለዩ በግልጽ መታወቅ አለበት አንድን ማጭበርበር ታላቅ ወይም ታናሽ ነው ለማለት መስፈርቱ ምንድን ነው? የሚወስነውስ ማን ነው? እንደመራለን ያሉ ሰዎችስ ታላላቅ ማጭበርበራቸውን ያስረሳላቸዋል? ታላላቅ ማጭበርበር የተባሉት በፌደራል መንግስት የተፈጸሙትን እንጅ የክልል መንግስታትን አይጨምርም? የሌብነትና የግፍ ውኃ ልክ የሆኑ ባለሥልጣናት ገና ሳይያዙ አነስተኛ ዝርፊያ የፈጸሙ የሚመስሉ እንዴት ቀድመው ተያዙ? መንግስት በነዚህና መሰል ጥታቄዎች ላይ ግልጽና አሳማኝ ምክንያቶችን ማቅረብ ካልቻለ ላላስፈላጊ ትችትና ክፍፍልም ሊዳረግ ይችላል   

ማጠቃለያ

ሕወሓትና ሌሎች የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የኢትዮጵያ የሆነውን ሁሉ አዳክመዋል አጨናግፈዋል።  ከሁሉም በላይ ውድ ኢትዮጵያውያንን ገድለዋል አሳደዋል፣ ደብድበዋል። ፍትሕንና እውነትን ከማሳደዳቸው የተነሳ ተራው ሠራተኛ እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች ሳይቀሩ አጭበርባሪ ሆነዋል። አዲሱ ትውልድ የመንግስትን የሃይማኖትንና የሥልጣንን መልካም ጎኖች ሳያይ አድጓል። ዶ/ር ዐቢይ እንዳሉት ያልተነካካ የለም። ልዩነቱ አብዝቶ የተነካካና ትንሽ የተነካካ ላይ ነው። ይህ የመጠን ልዩነት ደግሞ ለመታሰርና ላለመታሰር መስፈርት ሆኗል። አላስፈላጊ ምክንያቶችንና ክርክሮችን ለማስቀረት ትንንሽና ትልልቅ ማጭበርበሮች ተለይተው መገለጽ አለባቸው። ማለትም የሚያሳስሩ ወንጀሎች ምን አይነቶቹ እንደሆነ መታወቅ አለበት። በዚህ ሂደት አስቀድመው እንደተደመሩ የተናገሩና ታላላቅ ወንጀል የፈጸሙ የሚባሉ ባለሥልጥናት እጣ ፋንታም ምን እንደሚሆን በግልጽ መነገር አለበት። ሕዝቡና የዐቢይ መንግስት ታናናሽና ታላላቅ ማጭበርበር የፈጸሙትን ባለስልጣናት እንዴት መመልከት እንዳለበት የሚያመላክት አካሄድ እስከሌለው ድረስ እንደነ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ያሉ ሰዎች አንድ ርምጃ ወደፊት ሦስት ወደኋላ መጓዛቸውን ይቀጥላሉ። ይህ ደግሞ በትግራይ ሕዝብ ሕይወት ላይ እቃ እቃ መጫወትን ሊያስከትል ስለሚችል ጉዳይ ቶሎ ሊቋጭ የሚገባው ነው እላለሁ          

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!




          
     

No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...